…ግን ብልህም ሁኚ»

የሰው ልጅ በኑሮው የሚመራበትን እያንዳንዱን ስርዓት ሲያወጣ ምክንያት አለው። የጎደለ ነገር ሲኖር ለማሟላት፣ ያነሰ ነገር ሲኖር ለመጨመር፣ ያስቸገረውን ለማስተካከል፤ ዝቅ ያለውን ከፍ ለማድረግና መሰል በማኅበራዊ ጉዳዮቹ እንዲስተካከል የፈለገውን በአቅሙ ለማቃናት ስርዓትን ያወጣል። ይህም ሰዎች ከህሊናቸው ባሻገር የተለያየ ሃሳብ ሊይዙባቸው በሚችሉ ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ተመሳሳይ አካሄድ እንዲኖራቸው ያደርጋል።

ህግ አንዱ የሰው ልጅ በጋራ ሲኖር ወደአንድ አኗኗር እንዲመጣ የሚያግዝ መስመር ነው። በህግ አካሄድ ይወሰናል፣ በህግ ስርዓት ይበጃል፣ በህግ የተበደለ ይካሳል፣ በህግ ለምስኪኖች ከለላ ይደረጋል ወዘተርፈ። ወዲህ መለስ ስንል ታዲያ ሴቶችን በሚመለከት የወጡ በርካታ ህግጋት አሉ። እነዚህ ህጎች ምን ያህል ሴቷን የሚጠብቁ ናቸውይህ የባለሙያ ትንታኔ የሚፈልግ ጥያቄ ነው። ከሴቷ ግን ምን ይጠበቃልሴቷስ ምን ትጠብቃለችሌላ ጥያቄ ነው።

ምንአልባት የህግ ችግር ላይኖርብን ይችል ይሆናል፤ በትክክል ግን የአፈጻጸም ጉድለቶች እንዳሉ እናውቃለን። ታዲያ በዚህ ጉድለት መካከል የሚደርሱ ብዙ በደሎች ይኖራሉ። እናም «ህግ ሴትን ልጅ ምን ያህል ይጠብቃታልብልህ መሆንስ አያዋጣትም?» የሚል ጥያቄ ይዘን ሁለት ሰዎችን ለማነጋገር ሞክረናል። እዚህ ላይ ሁሉም ችግር በብልሃት ይታለፋል ማለት እንዳልሆነ ግን ልብ ይሏል!

አምባሳደር ዶክተር ገነት ዘውዴ በጉዳዩ ላይ እንዲህ አሉ፥ «ብልሃት በአንዲት ሴት ላይ ይወሰናል፤ ህግ ግን ለሁሉም ሴት ያስፈልጋል» በዚህም ብልሃት ጥሩ መሆኑን አንስተው ግለሰባዊ ችግሮችን ለመፍታት ይበጃል ብለዋል። በጥቅሉ ግን ህግ ሁሉንም ገዢ ስለሆነ ህግ በሚገባ ያስፈልጋል ነገር ግን ብልሃትም ጠቃሚ ነው ብለዋል።

እንደ ዶክተር ገነት ገለጻ፤ ከባድ ጥቃቶች ደርሰው የምንሰማው ህጉ ስላልጠበቀ ሳይሆን በወንዶችም በሴቶችም በኩል የአመለካከት ችግር ስላለ ነው። እንደ ኅብረተሰብ አካል ግን ህግ ለሴቶች ያስፈልጋል። ምክንያቱም የአመለካከቱን ችግር ተከትሎ የሴቶች ሰብአዊ መብት ተጥሷል፣ በሴትነት የሚደርሱ ብዙ ጫናዎችም አሉ። እነዛ ሁሉ የህግ ጠበቃና ክልከላ ያስፈልጋቸዋል። «የእያንዳንዳችንን ችግር በምንፈታ ጊዜ ግን ብልሃት ጥሩ ነው» ብለዋል።

የእናት ባንክ መስራችና የቦርድ ሊቀምንበር ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ እዚህ ላይ ተመሳሳይ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። «እንደዜጋ ተማምነን የምንኖረው በህግና በህግ የበላይነት ነው። ያንን የሚተካ ነገር ያለ አይመስለኝም» ያሉ ሲሆን፤ ራስን ለመጠበቅ መደረግ ያለባቸውም ነገሮች መኖራቸውን በማንሳት ወንድም ሴትም ሳይል ሁሉም የሰው ልጅ በማንኛውም ጉዳይ ብልህ መሆን እንደሚያስ ፈልገው እምነታቸውን ገልጸዋል።

ይህም በተለይ አንዱ ከሰዎች ጋር የሚኖር ግንኙነት ነው። በሥራ፣ በዝምድና፣ በጓደኝነትና መሰል ዝምድናዎች ምን አይነት ግንኙነት እንዳለን ማወቅና መጠንቀቅ፤ ብሎም ከምንገናኛቸው ሰዎች ጋር በሚገባ መተዋወቅ ያስፈልጋል፤ እንደ ወይዘሮ መዓዛ ገለጻ። «ህግ ችግር ከደረሰ በኋላ የሚደርስ ነገር ነው፤ አስቀድሞ ለመከላከል በቅድሚያ በሴቶች በኩል ግንዛቤ መኖሩ የአኗኗር ዘዴ አካል ነው» ይላሉ።

አምባሳደር ዶክተር ገነት ዘውዴ ሊሠራ የሚገባው አመለካከት ላይ መሆኑን አጥብቀው ይናገራሉ። ህግ መኖሩ ብቻ ሳይሆን ሴት ልጅ ላይ ጥቃት ማድረስ ለቤተሰብ፣ ለማኅበረሰብ ብሎም ለአገር ልማት ጉዳት እንዳለው በዝርዝር ማሳወቅ ያስፈልጋል። ይህም የሴቶች ቀን ላይ ወይ የሚከበሩ በዓላትን ተንተርሶ የሚደረግ ሳይሆን ተከታታይ ሥራ ሊሠራበት የሚገባው ጉዳይ ነው። በጎ ያልሆነውን አስተሳሰብ ለመቅረፍም ብልህ መሆን፣ ባለመታከት መሥራት ያስፈልጋል። በሴት ላይ ያለው አመለካከት ትናንት የተፈጠረ ሳይሆን ለዘመናት የቆየ ነውና ።

እነዚህ በየመስካቸው ውጤታማ የሆኑና በአርአያነት የሚታዩ ሴቶች ሴት ልጅ ልትመራበት ይገባል ያሉትን መርህ ነግረውኛል። ወይዘሮ መዓዛ እንዲህ ነበር ያሉት፤ «በራስ የመተማመን እና በራስ የመቆም ነገር ለሴት ልጅ በጣም አስፈላጊ ነው። ባለችበት ቦታ በራስ መተማመንን እያዳበሩ፣ ከማንም ይሁንታና ፈቃድ ውጪ መቆም እንደምትችል ለራስ ማረጋገጥ ትልቅ ነገር ነው። ከዛ በተረፈ ደግሞ ከሰዎች ጋር ባለ ግንኙነት ስለሰው ማወቅና የራስንም ስሜት ማወቅ ያስፈልጋል» ብለዋል።

ዶክተር አምባሳደር ገነት ዘውዴ የሚከተለውን አሉ፥ «እኔም ሰው ነኝ ብላ ማሰብ አለባት። ከዛ በመነሳት እኔ ጥሩ ሚስት እሆናለሁ ትላለች፤ ጥሩ ሚስት መሆን ጥሩ ነው። ጥሩ እናት እሆናለው ትላለች፤ ጥሩ እናት መሆን ተገቢ ነው። ከዛ ባሻገር ጥሩ ሠራተኛ እሆናለሁ፣ በራሴ እተማመናለሁ፣ በራሴ የማሸንፍ እሆናለሁ፣ ጥገኛ አልሆንም፤ ራሴን እችላለሁ፤ ራሴን አወጣለሁ ማለት ያስፈልጋል። የመጫወቻ ሜዳው ሙሉ ለሙሉ ባይስተካከልም ዕድሉ ግን አለ። የዛ ዕድል ተጠቃሚ እሆናለሁ በማለት ራሷን ማጠንከር አለባት» ሲሉ ከሴቷ የሚጠበቁ ያሏቸውን ሀሳቦች ነግረውናል።

ዶክተር ገነት አያይዘውም እናቶች ሴት ልጆችን ማጠንከርና ደጋፊ መሆን እንዳለባቸው ሃሳባቸውን አቅርበዋል። ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን ከሴት ልጆች ጋር በግልጽነት መወያየት ጠቃሚ ነው ብለዋል። «ህግ ቢኖርም ብልጥ መሆን እንዳለባቸው ለልጆች መምከር ያስፈልጋል፤ ልናስፈራራቸውና ተሳቀው እንዲኖሩ ሳይሆን ነገሩን አውቀው ግን መጋፈጥ እንዲችሉ ማድረግ አለብን። እኔ በዚህ በጣም አምናለሁ።»

ሁሉም ታዲያ በንግግራቸው መካከል አንድ ጥቅል ሃሳብ አስተላልፈዋል። እንደአገር በእርግጥ ህግ ማስፈለጉ ላይ ጥርጥር የለም። ምንም እንኳን በርካታ የአፈጻጸም ችግሮችን ነቅሶ ማውጣት ቢቻልም በህግ አስፈላጊነት ላይ ድርድርም ክርክር አይነሳም። ከዛ በተጓዳኝ ግን እናቶቻችን እንደሚሉት«ለክፉም ለደጉ ፌጦ መድኃኒት ነው»

እያንዳንዷ ሴት የሚገጥማትን ችግር በብልሃት ለመፍታት ዝግጁ መሆን አለባት። እያንዳንዷ ሴት ድምር ነው አገር የሚያህለው። ልክ የአንዷ ጥቃት ገዝፎ ህመሟ እንደሚሰማን፣ ድሏም ለብዙዎቻችን አርአያ እንደሚሆን፤ የአንዷ ትግልም በኋላ የአገርን ምስል ያመጣል። አስከፊ ጥቃት ባደረሱት ላይ ህግ የራሱ እርምጃ ይኖረዋል፤ ጥቃቱ ሳይደርስ በፊት ግን ለመከላከል መጣሩ ሁሉንም ያተርፋል።

ብልሃት ለሴት ልጅ በተፈጥሮ የታደለ እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ። ሴት ልጅ ብልህ ናት። ይህንን በህይወት እርምጃዋ ሁሉ ልትጠቀመው ይገባል። ታዲያ እናትም ልጇን ስትመክር ትላለች፣ «ልጄበእርግጥ በአገርሽ ላይ ህግ አለ፤ ግን ብልህም ሁኚ» ሰላም!

ሊድያ ተስፋዬ

Leave a Comment