ጉዞ ወደታላቂቷ አገር – ኢትዮጵያ

ጉዞ ወደታላቂቷ አገር – ኢትዮጵያ

አባ መላኩ

በኢፌዴሪ ህገ መንግሥት ላይ በግልጽ እንደተደነገገው አገሪቱ የገበያ መር ኢኮኖሚ ሥርዓትን ተከትላ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ በመንደፍ በሥራ ላይ አውላለች። በኢኮኖሚው ውስጥ የመንግሥት ሚና የተለያዩ የልማት ኃይሎችን በማቀናጀት መምራት፣ መሠረተ ልማት ማቅረብና የሰው ሃብት ልማትን ማካሄድ፣ ፈጣንና ውጤታማ የመንግሥት አገልግሎት መስጠትና መደገፍ ቁልፍ ተግባራት ሆነው በመከናወን ላይ ናቸው።  በተጨማሪም የኪራይ ሰብሳቢነት ምንጮች እየተዘጉ ነው። በግሉ ሴክተር የማይተገበሩ የልማት ሥራዎች መንግሥት ገቢራዊ እንዲያደርጋቸው የሚያስችሉ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል፡፡

ባለፉት ሥርዓቶች የወጡና የግሉን ዘርፍ ቀጥተኛ ተሳትፎ የሚገቱ ህጎችና ደንቦች ዛሬ ላይ ተወግደው በልማታዊ መስመር ራዕይዎች ተተክተዋል። በዚህም ለውስጥም ሆነ ለውጭ ባለሃብቶች ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል። በዚህም መሠረት በአሁኑ ወቅት አገሪቱ ለኢቨስትመንት የምትመች አገር ሆናለች። እርግጥ ለዚህ አባባሌ ከሰሞኑ ስለ ኢትዮጵያ ምቹ የኢንቨስትመንት አገርነት ከዳር ዳር መጠቃቀስ መጀመሩ ነው።

እስካ ዛሬ ድረስ ጎረቤት አገር ኬንያ በአበባ ምርት ቀዳሚ ነበረች፤ በአሁኑ ወቅት ግን ኢትዮጵያ ዋነኛ ተፎካካሪ አገር ሆናለች። ሌላ ማሣያ ልጨምር። ኢትዮጵያ የመጓጓዣና ኃይል ማመንጫ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን እያስፋፋች ትገኛለች። ወደ አፍሪካ ለመምጣት የሚሹ ታላላቆቹን የማኑፋክቸሪንግ ኩባንያዎች ቀልብ ገዝታለች። በተለይም ኢትዮጵያ የቻይና ኩባንያዎችን በመሳብ ረገድ የሚያበረታታ ተግባር በማከናወን ላይ ናት።

ምን ይህ ብቻ! የኢትዮጵያ የቆዳ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ጥራት ያለው ጫማዎች እና ምርቶች በማቅረብ በዓለም ገበያ ተፈላጊነቱ ጨምሮ ተወዳዳሪ እየሆነ መጥቷል። በተለይም አገሪቱ ባላት አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ምንጭ፣ በተመጣጣኝ የሰው ሀብት ጉልበት ዋጋ እና እያስመዘገበችው ባለው ፈጣን ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት ዓለም አቀፍ ኩባንያዎችን ትኩረት ስባለች።  

በተለይም ተቢ የመሠረተ ልማት በማሟላት እና አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት በማዘጋጀት በኩል የተለያዩ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ዝቅተኛ የማምረቻ ወጪ ወደሚጠይቃቸውና ምቹ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ ወዳላት ኢትዮጵያ ተስበው እንዲመጡ አድርጓቸዋል። ሌላም ማሣያ ልጥቀስ። ለመሆኑ አገራችን ለምን ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ሆነች?  

ቀደም ሲል የተጠቃቀሱት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንትን የመሳብ ብቃት የመነጨው እንዲያው ዝም ብሎ ከባዶ ነገር ተነስቶ አይደለም፤ ይልቁን አገሪቱ ካለት ተመራጭ የኢንቨስትመንት አሠራር እንጂ። የኢፌዴሪ መንግሥት በአገሪቱ መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ፣ በኢንቨስትመንት ለመሰማራት ፍላጎት ለሚያሳድሩ የውጭ ባለሃብቶች የተለያዩ ማበረታቻዎችን ያመቻቻል። በሩን ከፍት አድርጎም በተለያዩ አለም ዓቀፋዊ መድረኮች ላይ ተጨባጭ ሁኔታውን ያስረዳል። በርካታ ባለሃብቶችንም መሳብ ችሏል።  

ኢትዮጵያ ከምትከተለው ፖለቲካል ኢኮኖሚ ሥርዓት አኳያ የውጭ ባለሃብቶች በመንግሥት ከተያዙ የምጣኔ ሃብት ዘርፎች ውጪ እንዲሁም በህግ ከተደነገጉ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች በስተቀር ኢንቨስተሮቹ ወደአገሪቱ ገብተው በኢንቨስትመንት መስክ እንዲሳተፉ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል።

ኢትዮጵያ ያላት የተረጋጋ ሥርዓት፣ ርካሽ የጉልበት ክፍያ እንዲሁም አገሪቱ ያዘጋጀችው  የተሻለ የታክስ ድጎማና የእፎይታ ጊዜ ለውጭ ባለሀብቶች ተመራጭነት ምክንያት ከሆኑት መካከል ናቸው። ታዋቂው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የዓለም ገበያን በቀላሉ መድረስ መቻሉ አገሪቱ ለኢንቨስትመንት ምቹነት አስመርጧታል።  

በመሆኑም ይህንን ለኢንቨስትመንት ምቹ የሆነን ግብዓት አገሪቱ በተገቢው መንገድ ልትጠቀምበት ይገባል። ለዚህ ደግሞ ከሁሉም በፊት በአገሪቱ አስተማማኝ ሠላም የመስፈኑ ሁኔታ ወሣኝ ጉዳይ ነው። ከሁሉ በፊት ሠላም ከሌለ ስለ ልማት ማሰብ ከቶ አይቻልም። ስለ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መጎልበት መነጋገርም እንዲሁ። ያለ ሠላም እንኳን የውጭ ባለሀብቶችን መሳብ ቀርቶ፣ ከሥፍራ ሥፍራ መዘዋወር፣ እንደልብ ከቤት ወጥቶ መግባት አይሞከርም። በመሆኑም የአገሪቱን ሠላም አስተማማኝ ማድረግ ለመንግሥት ብቻ የሚተው ሳይሆን ከሁሉም ዜጋ የሚጠበቅ ወቅታዊ ተግባር መሆኑን እዚህ ላይ ልብ ማለት ተገቢ ይሆናል።

እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት ቁም ነገር ቢኖር ዛሬ ኢትዮጵያ በፈጣን የኢኮኖሚ ዑደት ውስጥ የመገኘቷ ጉዳይ ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ የፋይናንስ፣ የቴሌኮም እና የጅምላ ንግድን ጨምሮ ሌሎች ዋና ዋና የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለውጭ ባለሃብቶች የተከለከሉ ናቸው።

ሌላው በአገሪቱ ውስጥ እያደገ የመጣው ተጠቃሚ እንዲሁም መካከለኛ ገቢ ያለው የህዝብ ቁጥር መጨመር፣ የከተሞች በፈጣን እድገት ላይ መሆንና ሣቢ የኢንቨስትመንት አሠራር መኖር የውጭ ባለሃብቶችን ቀልብ ስቧል። በተለይ ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ፈጣን ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉ አገራት ውስጥ መጠቀሷ ብሎም እያደገ የመጣውን ፍላጎት ለማሟላት አቅም ያላት መሆኗ ባለሃብቶቹ ለሚሳተፉበት የኢንቨስትመንት ዘርፍ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል።

የኢትዮጵያ የፋይናንስና ሌሎች ተቋማት ራሳቸውን በሁሉም መስክ እስኪያጎለብቱና በአስተማማኝ ሁኔታ ላይ ተገኝተው ተወዳዳሪ እስኪሆኑ ድረስ መንግሥት በተመረጠ አኳኋን በልማት ሥራው መሳተፈየ የግድ ይሆናል። ሆኖም የውጭ ባለሃብቶቹ በሲሚንቶ፣ በቡና፣ በወይን እና በብስኩት ማምረት ዘርፎች ውስጥ በመሳተፍ እንቅስቃሴ ማድረግ ይችላሉ። በዚህም የተነሳ ኢትዮጵያ የውጭ ባለሃብቶችን ወደአገር ውስጥ ለመሳብ የሚያበረታታ አካሄድ እየተከተለች መሆኗን በቀላሉ መረዳት ይቻላል።  

በኢትዮጵያ ዛሬ ላይ በተለይ በኢንዱስትሪ ዘርፎች የተሰማሩ የውጭ ባለሀብቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል። አገሪቱ ለኢንቨስትመንት ያላትን ምቹነት የተገነዘቡ ታላላቅ ኩባንያዎች መዋዕለ ንዋያቸውን እያፈሰሱ ይገኛሉ። ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠርም ችለዋል።

ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያ እየተከተለች ባለው ምቹ የኢንቨስትመንት ምህዳር ነፃ የመሬት አቅርቦት ታዘጋጃለች፤ የአበባ ማምረቻ ሥፍራዎች በመንገድ እና በኤሌክትሪክ ኃይል  እንዲተሳሰሩ ታደርጋለች። በዚያ ላይ የታክስ እፎይታ ጊዜ አለ። ይህም ሁኔታ በርካታ የውጭ ባለሃብቶችን ወደ አገሪቱ ለመሳብ ዋነኛው ምክንያት ሆኗል። እዚህ ላይ ብዙዎችን ሊያግባባ የሚችል ቁም ነገር አለ። ይኸውም አገሪቱ የምትከተለው የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመር አሁን ለተመዘገበው የኢንቨስትመንት አመቺነት ምህዳሩ ወሣኙን ሚና መጫወቱን ነው።

የኢፌዴሪ መንግሥት አገሪቷንና ህዝቦቿን ከድህነትና ከኋላ ቀርነት ለማላቀቅ የነደፈው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመር ተስፋ ሰጪ እድገት በማስመዝገብ ላይ እንደሚገኝ ይታመናል። ይህንንም የውጪው ዓለምና ባለሃብቶቻቸው ሳይቀሩ እየመሰከሩ ይገኛሉ። በቃል ምስክርነታቸውን ከመስጠት ባለፈም የአገሪቱን መፃዒ ዕድል ከወዲሁ በአንክሮ በማጤን በኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመሳተፍ ወደ ኢትዮጵያ መትመም ይዘዋል። ለዚህም ነው የውጪ ባለሀብቶች ጉዟቸውን ወደ ታላቂቷ ኢትዮጵያ ማድረግን መርጠዋል የሚሉትን ቃላት ያለሀፍረት በአደባባይ መናገር የሚቻለው።

 

Leave a Comment