የጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫ ከፖለቲካዊ ጉዳዩች አኳያ

የጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫ ከፖለቲካዊ ጉዳዩች አኳያ

                                                  ቶሎሳ ኡርጌሳ

የኢፌደሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በቅርቡ በወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተው ነበር። በዚህ መግለጫቸው ላይ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዩች በስፋት ተዳስሰዋል። በዚህ ፅሑፌ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፖለቲካ ጉዳዩች ዙሪያ የገለጿውን ጉዳዩች መነሻ በማድረግ ሃቆችን ለመተንተን እሞክራለሁ። በዋነኛነትም አቶ ኃይለማርያም የፌዴራል መንግስትንና የክልሎችን የስልጣን ወሰን አስመልክተው የገለፁት ላይ አተኩራለሁ።

እንደሚታወቀው ሀገራችን የምትመራበት ፌዴራላዊ ስርዓት ለፌዴራሉም ይሁን ለክልል መንግስታት የስልጣን ወሰን ያለው ነው። ክልሎች ከስልጣናቸው ላይ ቆርሰው ለፌዴራል መንግስቱ የሰጡትን ውክልና ያከብራሉ። ፌዴራል መንግስቱም የክልሎችን የስልጣን ወሰን ያከብራል።

እንደሚታወቀው የህዝቦችን የዘመናት የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ጥያቄዎችን አፍኖ ከነበረው አምባገነናዊው የደርግ ሥርዓት ውድቀት በኋላ፤ በሀገራችን የነበረው ሁኔታ በጥልቀት መፈተሹ የግድ ነበር፡፡ በመሆኑም የዛሬ 26 ዓመታት በቅድሚያ የተወሰደው ርምጃ የአገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ብረት አንስተው ያለፉት ሥርዓቶችን ያስወገዱበት መነሻ ጥያቄዎቻቸው በአግባቡ እንዲመለሱ ማድረግ ቀዳሚ አጀንዳ ሆነ፡፡

ከ1983 ዓ.ም እስከ 1987 ዓ.ም ድረስ የዘለቀው የሽግግር መንግስቱ ቻርተር ለእነዚህ የዘመናት የህዝቦች ጥያቄዎቹ ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ቻርተሩ ተጨባጭ ለሆኑና አፍጥጠው ለመጡት የህዝብ ሉዓላዊነት እንዲሁም ለብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የማንነትና እንዲሁም የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ጥያቄዎች ብሎም ሰር ሰደው ለቆዩት የዴሞክራሲ ጥያቄዎች መሰረታዊ መፍትሔ ሊሰጥ ችሏል፡፡

ቀደምት አሃዳዊ ሥርዓቶች ለእነዚህን ቁልፍ የህዝቦች ጥያቄዎች መልስ የማይሰጡ በመሆናቸው፤ የህዝቦች የዘመናት ጥያቄዎች ምላሽ ያገኙት በቻርተሩና ኋላ ላይም በ1987 ዓ.ም በህዝቦች ውይይትና ሙሉ ፈቃደኝነት በፀደቀው ህገ መንግሥት ነው፡፡

በወቅቱ በራሳቸው የትግል ፍሬ ምላሽ ያገኙት የአገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ከ80 በላይ ስለሆኑ እነዚህን የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ልዩነታቸውን አቻችሎ በጋራ እንዲኖሩ ለማድረግ ፌዴራሊዝም አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነበር፡፡ እናም ሀገራችን የፌዴራል የመንግስት አወቃቀርን ለመከተል ችላለች፡፡ ብዝሃነታችን ሥርዓቱን እንድንመርጥ ምክንያት ሆኗል፡፡

በእኔ እምነት በወቅቱ የሀገራችን ህዝቦች ይህን የመንግሥት አወቃቀር ባይመርጡ ኖሮ፤ በወቅቱ ከነበሩት የታጠቁ የብሔር ሃይሎች አኳያ ዛሬ ፌዴራላዊት ኢትዮጵያ የምትባል አገር ለመኖሯ ማንም በርግጠኝነት መናገር የሚችል አይመስለኝም።

እዚህ አገር እየተገነባ ያለው ፌዴራላዊ ሥርዓት የአገሪቱን ፖቲካዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊና ማህበራዊ ተጨባጭ ሁኔታዎችን መነሻ ያደረገ እንጂ እንዲሁ ዝብ ብሎ የተመረጠ አለመሆኑን መገንዘብ የሚገባ ይመስለኛል፡፡ እነዚህ መነሻ ሁኔታዎችም በህገ መንግስቱ ላይ በግልፅ ስፍረዋል፡፡ ላለፉት 23 ህገ መንግስታዊ ዓመታትም በተግባር ውለዋል፡፡

የኢፌዴሪ ህገ መንግስት በሀገራችን ለዘመናት ምላሽ ሳይሰጣቸው ለኖሩት ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ስፋት ባለው ህዝብ ተሳትፎ ምላሽ እንዲሰጣቸው ያደረገ በመሆኑ የፌዴራል ሥርዓቱ መገለጫ ነው፡፡

በፌዴራል ሥርዓቱ የአገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤት ሆነዋል፡፡ ይህም የመንግስት ቅርፀ- መንግስትነት ከሀገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የመነጨ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ይህ ዕውነታም ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤቶች የሆኑት የአገራችን ህዘቦች የፌዴራሉን ስርዓት በራሳቸው ይሁንታና ስምምነት መፍጠራቸውን እንድንገነዘብ ያደርገናል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ካላቸው ስልጣን ቆርሰው ለፌዴራል መንግስቱ በመስጠት የሀገሪቱ አስተዳደር በመረጧቸው ተወካዮች አማካኝነት እንዲንቀሳቀስ ፈቅደው ተስማምተዋል፡፡ ለዚህ አንዱና ዋነኛው ማስረጃ ህገ መንግስቱ በመግቢያው ላይ “እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች …”  በሚል ሐረግ መጀመሩ ነው፡፡

የእኛ አገር ፌዴራላዊ ሥርዓት በህብረ ብሔራዊነት ቀለም ያሸበረቀ ነው፡፡ ቀደም ሲል እንዳልኩት የየትኛውም ዓይነት ፌዴራሊዝም ዋነኛ ዓላማ በአንድ ሀገር ውስጥ ያሉ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በልዩነታቸው ውስጥ ያለውን አንድነት አቻችሎ በጋራ እንዲኖሩ ማድረግ በመሆኑ፤ በውስጧ ከ80 በላይ የተለያዩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችን የያዘችው ኢትዮጵያ ከፌዴራላዊ ሥርዓት ውጭ ሌላ አማራጭ ሊኖራት የሚችል አይመስለኝም፡፡

ይህ በመሆኑም እነዚህ ህዝቦች በራሳቸው ቋንቋ እየተጠቀሙና እየተዳኙ ብሎም ባህላቸውን እያሳደጉ ከፌዴራሉ አንድነት የሚገኘውን የጋራ ጥቅም በመቋደስ የአብሮነት ጉዟቸውን ምቹ አድርገዋል፤ ውጤታማም ሆነዋል፡፡ ፌዴራላዊ ሥርዓቱ የአብሮነት ዋስትናቸው ሆኖ እነሆ ላለፉት 26 ዓመታት እጅ ለእጅ ተያይዘው እንዲያድጉ ምክንያት ሆኗቸዋል።

ርግጥ አገራችን ለምን ፌዴራሊዝምን እንደምትከተል ምላሽ ለመስጠት ሲታሰብ፤ የህገ መንግሥቱ አንቀፅ 39 ሳይወሳ የሚታለፍ አይደለም፡፡ ይህ አንቀፅ አገራችን እንድትበተን የሚሹ ወገኖች በተዛባ ትርጓሜ የሚያራግቡት በመሆኑ አብሮ በምራራት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡

እንደ እውነቱ ከሆነ ይህ አንቀፅ ከአገር ብተና ጋር የሚያገናኘው ጉዳይ የለም፡፡ እንዲያውም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በመፈቃቀድና በአንድነት መኖር የሚያስችላቸውን ዴሞክራሲያዊ የአንድነት ዕድልን የሚሰጥ አንቀፅ ነው፡፡ ለዴሞክራሲያዊ አንድነት ቅድሚያ በመስጠት ህዝቦች የእኩልነት መብታቸው ተረጋግጦ ተጠቃሚ እንዲሆኑም ያደርጋል፡፡

እናም በአንቀጹ አማካኝነት የእኩልነት መብት ማረጋገጫ የሆኑት የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቋንቋዎች፣ ባህሎች፣ ታሪኮች ወዘተ ተከብረዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ በፖለቲካዊ አስተዳደር በኩል እኩል የመሳተፍ መብት ያገኙ ሲሆን፤ በልማት ስራው ላይም እኩል ዕድል እዲያገኙና በውጤታቸው መሰረት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ተችሏል፡፡

ማንም ሰው እነዚህን መብቶች ያረጋገጡ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሊበታተኑ ይችላሉ ብሎ ማሰብ የሚችል አይመስለኝም። የትኛውም ህዝብ እነዚህ መብቶች እስከተሰጡት ድረስ ጥቅሞቹን እያጣጣመ የፌዴራል ሥርዓቱን ያጠናክራል እንጂ ለመበተን ይፈልጋል ብሎ ማሰብ የዋህነት ይመስለኛል፡፡

እንዲያውም በእኔ እምነት በግጭት ውስጥ እየታመሱ ያሉት አንዳንድ አገራት ይህን መሰሉ ዴሞክራሲያዊ አንድነትን የሚያጠናክር አንቀፅ ቢኖራቸው ኖሮ እስካሁን ድረስ የተከሰተው ሰብዓዊና ማቴሪያላዊ ቀውስ ባልተፈጠረ ነበር፡፡

እናም የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ያለምንም ገደብ ያረጋገጠ ቢሆንም ዓላማው በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ አንድነትን በሀገሪቱ ላይ ለማምጣት መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ የምንከተለው ፌዴራላዊ ሥርዓት አባሎቹ የሚናቆሩበትና የሚባሉበት ሳይሆን አብረው በፈቃዳቸው በጋራ የሚያድጉበት መሆኑም እንዲሁ፡፡ ይህ ሁኔታም ፌዴራል መንግስቱና ክልሎች ላለፉት 26 ዓመታት በራሳቸው የስልጣን ወሰን ተግባራቸውን በብቃት እንዲወጡ አድርጓቸዋል፡፡ ለዚህም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው ላይ ፌደራል መንግስትና ክልሎች በህገ መንግስቱ ላይ በተቀመጠው መሰረት ተግባራቸውን እያከናወኑ ነው በማለት የገለፁት፡፡  

 

COMMENTS

Leave a Comment