የውጭ ምንዛሬ ማስተካከያን ተከትሎ የንግድ እቃዎች ዋጋን አለአግባብ በሚጨምሩ የክልሉ ነጋዴዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ የትግራይ ክልል ንግድ፣ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ አስታወቀ።

የውጭ ምንዛሬ ማስተካከያን ተከትሎ የንግድ እቃዎች ዋጋን አለአግባብ በሚጨምሩ የክልሉ ነጋዴዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ የትግራይ ክልል ንግድ፣ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው  ምክትል ኃላፊ አቶ ዳንኤል መኮንን እንደገለፁት በክልሉ የሚንቀሳቀሱ አከፋፋዮችና የችርቻሮ ነጋዴዎች  የውጭ ምንዛሪ ማስተካከያውን ተከትለው በንግድ እቃዎች ላይ  ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ማድረጋቸው ታውቋል።

በተለይም በአርማታ ብረቶች፣ቆርቆሮ፣ የወለል ንጣፍና በሌሎች የግንባታ እቃዎች ላይ እስከ 70 በመቶ ጭማሪ መታየቱን ቢሮው በጥናት ማረጋገጡን ተናግረዋል፡፡

“የዋጋ ጭማሪው ኢኮኖሚያዊ ምክንያት የሌለው ከመሆኑ ሌላ  ከውጭ ቀድሞው  በገቡ እቃዎች ላይ ጭምር በመሆኑ ተቀባይነት እንደሌለው ነው የቢሮው  ምክትል ኃላፊ የገለጹት፡፡

ከመሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች የዋጋ ጭማሪ ከተደረገባቸው መካከል ማኮሮኒ ፣ ፓስታ፣ ሽንኩርትና ቲማቲም ይገኙበታል፡፡

በዚህ ምክንያትም ህብረተሰቡ እንዲማረርና የገበያ ቀውስ እንዲፈጠር እያደረጉ ነው።

ቢሮው ያልተገባ ዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ አስተማሪ እርምጃ ለመውሰድ ጥናት አጠናቆ ግብረ ኃይል ማቋቋሙንም አስታውቀዋል፡፡

ግብረ ኃይሉ በየጊዜው የሚያጋጥሙ የዋጋ ንረቶች ላይ  ከነምክንያታቸው በማጥናትና በመለየት የማስተካከያ እርምጃ እንደሚወስድ አመልክተዋል፡፡

“እርምጃው ከጥቅል ዓመታዊ ሽያጩ እስከ 10 በመቶ የሚደርስ የገንዘብ  ቅጣት  አልያም እስከ ሶስት ዓመት የሚደርስ እስራትና ንግድ ፍቃድን እስከ መሰረዝ የሚደርስ ህግ የማስከበር ስራ ይሰራል” ብለዋል፡፡

የክልሉ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዝደንት አቶ አሰፋ ገብረስላሴ በበኩላቸው፣ ምክር ቤቱ ውድድርን መሰረት ባደረገ ነፃ ገበያ እንደሚያምን ገልጸዋል፡፡

መንግስት የውጭ ምንዛሪ  ማስተካከያ ማድረጉ ጠቀሜታው ለንግዱ ማህበረሰብ መሆኑን ጠቅሰው “የዋጋ ማስተካከያው ከአሁን በኃላ በሚገቡ ንብረቶች ላይ መጠነኛ ጭማሪ የሚያሳዩ ቢሆንም ከወራት በፊት የገቡ ንብረቶችን የሚነካ አይደለም” ብለዋል፡፡

ቀደም ብለው የገቡ ንብረቶች  መደበቅ፣ሰው ሰራሽ የገበያ እጥረትና የገበያ ቀውስ  እንዲፈጠር ማድረግ የነፃ ገበያ መርህ እንዳልሆነ ነው የክልል ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤቱ ፕሬዝደንቱ የተናገሩት።

ምክር ቤቱ  ከሁሉም በፊት ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር የንግድ ማህበረሰቡን ለማስረዳት ጥረት ያደርጋልም ብለዋል፡፡

አለአግባብ  የዋጋ ጭማሪ ማድረግ  ከሁሉም በላይ  ህብረተሰቡን የሚጎዳ በመሆኑ  ምክር ቤቱ እንደማይደግፈው ጠቅሰው  መንግስት የዋጋ ንረትን ለማስተካከል በሚወስደው እርምጃ ተቃውሞ እንደሌለውም አስታውቀዋል፡፡

Leave a Comment