የኦሮሚያና የአማራ ክልሎች ኮንፍረንስን በጨረፍታ

የኦሮሚያና የአማራ ክልሎች ኮንፍረንስን በጨረፍታ

                                                         ደስታ ኃይሉ

ሰሞኑን የኦሮሚያና የአማራ ክልል ተወካዩች በባህር ዳር ኮንፈረንስ አካሂደዋል። ኮንፈረንሱ የህዝቦችን ለዘመናት የዘለቀ አንድነታቸውን የሚያጠናክር ነው። የሁለቱ ክልል ህዝቦች አንድነት አገራችን አንድ የጋራ ፖለቲካል-ኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመገንባት የምታደርገውን ከፍተኛ ጥረት ያግዛል።

ሁለቱ ህዝቦች ልክ እንደ ሌላው የአገራችን ህዝብ በልዩነታቸው ውስጥ ያለውን አንድነት በማጠናከር የጋራ ቤታቸው የሆነችውን አገራቸውን የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ አውድማ ለማድረግ የሚያደርጉት ጥረት አካል ተደርጎም የሚወሰድ ነው።

ኮንፈረንሱ “አብሮነታችን ለሰላማችን፤ ሰላማችን ለአብሮነታችን!” በሚል መሪ መልዕክት የተካሄደ ነው። በኮንፍረንሉ ላይ የተሳተፉት ከ20 የኦሮሚያ ዞኖች እና ከ18 ከተሞች የተወጣጡ ከ250 በላይ የሚሆኑ የኦሮሞ አባ ገዳዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ ምሁራን እና አርቲስቶች ናቸው።

ከኮንፍረንሱ ጅማሮ በፊት በጉዞው ላይ ለኦሮሚያ ክልል ልኡካን ከዓባይ ህዳሴ ድልድይ ጀምሮ በደጀን፣ በፍኖተ ሰላም፣ በእንጀባራ ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል። ኮንፍረንሱን በማስልከት በተሰጠው መግለጫ የምክክር መድረኩ የሁለቱን ወንድማማች ህዝቦች አንድነት፣ ለሀገራችን ሰላምና ሉዓላዊነት ስለከፈሉት የጋራ መስዋዕትነትና ስለፈፀሙት አኩሪ ገድሎች ተነስተው ውይይት ተደርጎበታል።

ከዚህ በተጨማሪ የሁለቱን ህዝቦች ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኦኮኖሚያዊ መስተጋብር የሚያሳዩ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ ተግዳሮቶች እና ቀጣይ እቅጣጫዎችን የሚያመላክቱ የውይይት መነሻ ፅሁፎች በምሁራን ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

ኮንፍረንሱን የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ርእሰ መስተዳደር አቶ ለማ መገርሳ እና የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋችው በጋራ መርተውታል። በኮንፈረንሱ ላይ የአማራ ክልል በ2ዐ1ዐ ዓ.ም የስራ ዘመን ከሁሉም አጐራባች ክልሎችና ከመላ የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር በመሆን የህዝብ ለህዝብ ስራዎችን በስፋት ለመስራት አቅዶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ተገልጿል።

ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ልኡካን ጋር በሁለቱ ህዝቦች መካከል ስላለው ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ የትስስር መድረክ ከ1 ሺህ 500 በላይ ተሳታፊዎች ተገኝተው በርካታ ውይይቶች ተካሂደዋል። ውይይቶቹ የህዝቦችን አንድነት ከማጠናከር አኳያ የራሳቸው ፋይዳ ነበራቸው።

እርግጥ የአማራ እና የኦሮሞ ህዝቦች ከጋብቻ እስከ ጉዲፈቻ በደም እና በባህል የተሳሰሩ ህዝቦች ናቸው። በወቅቱ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው “የኢትዮጵያውያን አብሮነት እና አንድነት እያበበ እና እየጠነከረ የሚሄድ እንጂ እንደ እንፋሎት የሚተን፣ እንደጉም የሚበን አይደለም” በማለት ለታዳሚዎቹ ገልፀዋል።

አቶ ገዱ “የሁለቱን ህዝቦች የጠበቀ አንድነት ለመሸርሸር እና በመካከላቸው ግጭት ለመፍጠር የሚጥሩ ሃይሎች በሁለቱ ህዝቦች ትብብር ክፉ ድርጊታቸው ይመክናል፤ እየመከነም ነው” በማለትም አክለዋል።

በሁለቱ ህዝቦች መካካል ያለው ትስስር የትኛውም የፖለቲካ አካል ከሚያውቀውና ከሚገምተው በላይ ጥብቅ እና ጥልቅ ነው” በማለት የገለፁት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ በክልሎቹ የአማራ እና የኦሮሞ ህዝቦች ተከባብሮ እና ተዋዶ የመኖር እሴት እንዳላቸውም አብራርተዋል።

“ወጣቱ ትውልድ ንፋስ አመጣሽ በሆነው የልጅነት ሃሳብና የፈጠራ አጥፊ ቅስቀሳን ወደ ጎን በማለት የኖረና የነበረ አባቶቹን ያወረሱትን አንድነት እንዲሁም አብሮነት ሊጠብቅ እንደሚገባው በመድረኩ ላይ ተገልጿል።

የአማራ ክልል ህዝብ በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ዴሞክራስያዊ አንድነት፣ ሁሉም ዜጎች እኩል የሚኖሩባት አዲሲቷ ኢትዮጵያን የመገንባት ጥረት ከሌሎች የአገሪቱ ብሄር ብሄረሰቦች ህዝቦች ጋር ተባብሮ ከዳር ለማድረስ ቁርጠኛ መሆኑም ተመልክቷል። ኩራት የሆነ ኢትዮጵያዊ ማንነት ሊጠበቅ እንደሚገባም እንዲሁ ተወስቷል።

በዚህ የትስስር መድረክ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል። የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ ለታዳሚዎቹ ያደረጉት ሰፋ ያለ ንግግር የኮንፈረንሱን ተሳታፊዎች ያስደመመ ነበር።

ሁለቱም ርዕሳነ መስተዳድሮች ስለ ኢትዮጵያዊነትና የህዝቦች አንድነት ሲያደርጉት የነበረው ንግግሮች መሳጭና የአገራችንን ብሄሮችና ብሔረሰቦች በልዩነታቸው ውስጥ ያለውን ጠንካራ አንድነት ብሎም ኢትዮጵያ መንፈስን የሚያሳዩ ነበሩ።

እርግጥ ዛሬ የኢትዮጵያ ህዝቦች አንድነት በጠንካራ መሰረተ ላይ የተገነባ ነው። ማንም ሊሸረሽረው አይችልም። ዴሞክራሲያዊ አንድነታቸው ጠንክሯል። ዴሞክራሲያዊ አንድነቱ የተጠበቀ የየትኛውም ሀገር ህዝብ ያለመውን ሁለንተናዊ ዕድገት ዕውን ማድረጉ አይቀርም።

ከእኛ አገር አኳያም በሀገራችን ውስጥ እየተፈጠረ ባለው ዴሞክራሲያዊ አንድነት ሳቢያ የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ወደ ህዳሴያቸውን ለማረጋገጥ የሰነቁትን አገራዊ ራዕይ ገቢራዊ እያደረጉ ነው።

የአገራችን ህዝቦች የሚከተሉት የፌዴራሊዝም ሥርዓት በማህበራዊ ምንነት ምክንያት የሚፈጠር ልዩነቶችን ለማቻቻል አብሮ ለመጓዝ ብሎም በማህበራዊ ምንነት ወይም በሌላ የማንነት ልዩነቶችን መሠረት ያደረጉ ግጭቶችን ለማስተንፈስ አግባብነት ያለው የፖለቲካ መሣሪያ መሆኑን የመስኩ ተመራማሪዎች ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያ የምትከተለው ፌዴራላዊ ሥርዓት በሂደት ራሱን በራሱ እያረመ ለዛሬው የህዝቦች መፈቃቀድና አንድነት መጠናከር ጉልህ ሚና መጫወቱና አንድነትን ከማጠናከር አኳያም ረጅም ርቀት የሚጓዝ ነው።

እርግጥ ሥርዓቱ ራሱን እያረመና እንደ ማንኛውም ጀማሪ የፌዴራል ስርዓት ያሉበትን ችግሮች እየነቀሰ እንዲሁም ካለፉት ክስተቶች እየተማረ በሀገሪቱ ህዝቦች በመታገዝ በአስተማማኝ ቁመና ላይ ይገኛል። ይህ ዕውነታም አሁን የተገኘውን የህዝቦችን አንድነት ይበልጥ በፅኑ መሰረት ላይ የሚያኖር ነው። የባህር ዳሩ የአማራና የኦሮሚያ ክልሎች ኮንፍረንስ የዚህ እውነታ ነፀብራቅ ነው። እንዲህ ዓይነቶች ህዝብን ከህዝብ የሚያስተሳስሩ ኮንፈረንሶች ሊበራከቱ ይገባል እላለሁ።

 

    

Leave a Comment