የኢትዮጵያውያንን ጥልቅ የአብሮነት እሴት የሚሸረሽሩ ተግባራትን በጋራ መታገል እንደሚያስፈልግ አትሌቶች ገለጹ

የኢትዮጵያውያንን ጥልቅ የአብሮነት እሴት የሚሸረሽሩ ተግባራትን በጋራ መታገል እንደሚያስፈልግ አትሌቶች ገለጹ

የኢትዮጵያውያንን ጠንካራ የአብሮነት እሴት የሚሸረሽሩ ተግባራትን በጋራ መታገል እንደሚያስፈልግ አትሌቶች ገለጹ።

አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴና አትሌት ገብረእግዚአብሔር ገብረማርያም በአገሪቷ አንዳንድ አካባቢዎች በተለያዩ ጊዜያት በታዩ ግጭቶችና ሁከቶች ዙሪያ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ቆይታ አደርገዋል።

አትሌቶቹ እንደገለፁት፤ ኢትዮጵያውያን በመካከላችን ለዘመናት የዘለቀ የማይናወጥ የአብሮነትና የመቻቻል እሴቶች አሉ፤ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በተለያዩ አካባቢዎች እየታዩ ያሉት ግጭቶችና ሁከቶች ዓላማ ይሄን የአብሮነትና የመቻቻል ባህል መሸርሸር ነው።

“ኢትዮጵያ ውስጥ እየተከሰተ ያለው ግጭት ምንጩ አንድነታችን የማይፈልጉ ሓይሎች ናቸው” ብሏል አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ።

“ኢትዮጵያውያን በጠንካራ የጋራ እሴቶች የተገነባ አንድነት አለን” ያለው አትሌት ኃይሌ፤ በአሀኑ ወቅት በአገሪቷ እየተከሰቱ ያሉት ግጭቶች አገሪቷ የጀመረቻቸው ታላላቅ ፕሮጀክቶችን ለማደናቀፍ “በጠላቶች የተጠነሰሰ ነው” የሚል አስተያየቱን ሰጥቷል።

አትሌት ኃይሌ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ የጀመረችው ሥራ ‘ጥቅማችንን ይጎዳል’ በሚል “አገራችን ወደ እርስ በርስ ጦርነት ለማስገባት ያለ እረፍት የሚሰሩ አገሮች አሉ” ብሏል።

ይሄን ለማክሸፍም ኢትዮጵያውያን ከምንም ጊዜ በላይ አንድ ሆነን አገራዊ ጥቅማችንን መጠበቅና ማስጠበቅ አለብን ሲል ተናግሯል።

“ካለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ እዚህም እዚያም እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች ምንጭ ከአገር ውስጥ አለመሆኑን የምናየው ነገር አለ” ያለው አትሌት ኃይሌ፤ አሁን ይሄን መናገር ጊዜው ስላልሆነ ህዝቡ ሊጠነቀቅ እንደሚገባ ተናግሯል።

አትሌት ገብረእግዚአብሔር ገብረማርያም በበኩሉ”የኢትዮጵያውያን አብሮነት ኃይል መሆኑን የሚፈራ ኃይል ልዩነታችንን አጉልቶ ግጭት የሚቀሰቅስ በመሆኑ ነቅተን መታገል አለብን” ብሏል።

“የአብሮነት እሴቶቻችንን ሳይሆን ልዩነቶቻችን አጉልተው ወደ ነገር ከሚያስገቡን ኃይሎች ሁሉም ኢትዮጵያዊ መጠንቀቅ ይኖርበታልም” ነውያለው።

“ወጣቱ የሰላም ዋና ጠባቂ ዘብ መሆን አለበት”  ያለው አትሌት ገብረእግዚአብሔር፤ “የእኛ አብሮነት ኃይል መሆኑን ለሚፈራ አካል የጥፋት መጠቀሚያ እንዳንሆን መንቃት አለብት” ሲል አስተያየቱን ለኢዜአ ሰጥቷል።

ዜጎች የተረጋጋ ኑሮ የሚገፉትና ዓለማቸውን የሚያሳኩት የአገሪቱ ሰላም ሲረጋገጥ ብቻ ነው ያለው አትሌቱ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለሰላሙ ዘብ መሆን አለበት ብሏል።

እስካሁን በታዩት ግጭቶችና ዓመፆች የታየው ሀብትና ንብረት መውደም፣ የሰው ህይወት መጥፋትና የሰላም መደፍረስ መማር እንደሚገባ አትሌቶቹ ገልጸዋል።

ወላጆችም ለልጆቻቸው ኢትዮጵያዊነትን ማስተማር እንደሚጠበቅባቸው የገለጹት አትሌቶቹ፤ መንግስትም የዜጎችን ህይወትና ንብረት የመጠበቅ ሓላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ጠይቀዋል።

Leave a Comment