የሠላም ዋጋ ስንት ደረሰ?

ethiopia

የሠላም ዋጋ ስንት ደረሰ?

አባ መላኩ

ሠላም ዋጋው ምን ያህል ነው። እንገምት እንበል። ማልዶ ወጥቶ፣ አምሽቶ ገብቶ ያለአንዳች እንከን ተግባርን ከውኖ መመለስ በምን ያህል ይለካል። በምን ይመዘናል። ልጅ ወልዶ፣ አሳድጎ፣ አስተምሮና ለወግ ማዕረግ አብቅቶ ተመስገን ብሎ አምላክን ለማመስገን መታደል ዋጋው ስንት ይሆን፣ ስንት ደረሰ? ይህ ሁሉ ሲሆን በሠላም ውስጥ ማለፍን ይጠይቃል። ቀላል መስሎ የሚታየው ይህ የየእለት ህይወት  በኃይማኖት ጽንፈኞች ሲዛነፍ፣ በጎጠኞችና በጠባብ አስተሳሰብ ምርኮኞች ሲፋለስ ያኔ ነው ለሠላም የሚገባው ዋጋ ምን ያህል ነው የሚለው የሚታሰበን።

 

የኃይማኖት ጽንፈኝነት በሉት ጠባቦች ሠላምን ለማደፍረስ ሲንቀሳቀሱ የቱን ያህል ጥፋት እየፈፀሙ ስለመሆናቸው ቆም ብለው ራሳቸውን ሊፈትሹ ይገባል። የንጹኃንን ህይወት አለአግባብ እየቀጠፉ ስለመሆናቸው ልብ ብለው ሊያጤኑ ይገባል። እዚህ ላይ የኃይማኖት አክራሪነትን ለአብነት እናንሳ። በዚህ ዙሪያ ጥቂት ማለትን ፈቀድኩ።

የአክራሪነትና የፅንፈኝነት ጫፍ የንፁኃን ዜጎችን አስተሳሰብና አመለካከታቸውን በጫና የመቀየር አካሄዱ ካልተሳካላቸው ወደ ጅምላ ግድያ የሚሸጋገሩበት ኢ ሰብዓዊ ድርጊት በማንኛውም መስፈርት ኃይማኖታዊ ተልዕኮ አለው ብሎ ለመቀበል አዳጋች ነው።

 

ማንኛውም ሰው የመረጠውን ኃይማኖት ወይም እምነት የመያዝ ወይም የመቀበል መብት አለው። ኃይማኖቱንና እምነቱን ለብቻ ወይም በግል ከሌሎች ጋር በመሆን በይፋ የማምለክ፣ የመከተል፣ የመተግበር፣ የማስተግበር ወይም የመግለፅ መብትም አለው።

 

ዜጎች በመረጡትና በያዙት ኃይማኖት ምክንያት ለማሸማቀቅ መሞከር፣ በኃይል ኃይማኖታቸውንና እምነታቸውን ለማስቀየር መንቀሳቀስ በኢትዮጵያ ሕግ መሠረት ተቀባይነት የሌለው ፀረ ሠላም ድርጊት ነው። እንዲህ ዓይነቱ ፀረ ሠላም ተግባርን የሚሸከም ኅብረተሰብ ዛሬ ላይ ይኖራል ተብሎ አይታሰብም።

 

“የእኔን ኃይማኖት ካልተከተልክ በስተቀር አማኝ አይደለህም፤ አሊያም ከሃዲ ነህ” በማለት ማሸበርም ሆነ አካላዊ ጥቃት ማድረስ፣ ግድያ መፈፀም የእምነት ተቋማትን ማፈራረስና መካነ መቃብሮችን ማውደም በእውነትም በፀረ ሠላም ኃይሎች የተጠነሰሰ ሴራ ስለመሆኑ አያጠያይቅም። ይህ ተግባር የሌሎችን ነጻነት በማፈን ድብቅ ዓላማን ለማሳካት የሚደረግ ተግባር እንደሆነ ከማንም የተሰወረ አይደለምና።   

 

እነዚህ ድርጊቶች የአክራሪነትና ፅንፈኝነት መገለጫዎች ናቸው። በአገራችን እየተፈፀመ ያለውም ከዚህ የተለየ አይደለም። እንዲህ ዓይነቱ  ሽብርተኝነት ፀረ ሠላም ብቻ ሳይሆን ፀረ ልማት በመሆኑ ይህንን መጠበቅ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት እንጂ ለመንግሥት ብቻ የሚተው አይደለም፡፡ የኃይማኖት አክራሪነት በጥቅሉ የዜጎችን የኃይማኖትና እምነት ነፃነትን በተግባር ለመናድ መንቀሳቀስ እንደሆነ ለማየት ይቻላል።

 

እነዚህ ጽንፈኛ ኃይሎች የኃይማኖት እኩልነትን በተግባር ለመናድ መንቀሳቀስ ሌላው ተግባራቸው ነው። መንግሥታዊ ኃይማኖትን ለመመሥረት የሚደረግ አፍራሽ እንቅስቃሴ በመሆኑ በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ሥርዓቱን ለመቀልበስና ህገ መንግሥቱን በህገ ወጥ መንገድ ለማፍረስ የሚጠነጠን ድርጊት እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል።

 

አክራሪው ኃይል እኩይ ተልዕኮውን ለማከናወን በመሣሪያነት የሚጠቀመው ወጣቶችን ነው። የዓላማው ማስፈፀሚያ አድርጎ ይንቀሳቀሳል። በመሆኑም ችግሩ ምን ያህል ፈታኝና አስከፊ እንደሆነ መረዳት ይቻላል። ፅንፈኛው ኃይል የተለያዩ ሐሰተኛ አሉባልታዎችን፣ የማደናገሪያ አጀንዳዎችንና አማላይ ዘዴዎችን በመጠቀም ወጣቶችን በዓላማው ማስፈፀሚያነት ያለ የሌለ አቅሙን በማሟጠጥ በመጠቀም እየተፍጨረጨረ ነው።

 

ዛሬ ኢትዮጵያ በሠላም፣ በልማትና በዴሞክራሲ ጎዳና ላይ በፍጥነት እየተራመደች ያለች አገር ሆናለች። የአክራሪዎች ዓላማ አልፋና ኦሜጋም ይህ በፍጥነት እየገሰገሰ ያለውን ዕድገት በእንጭጩ በመግታት አገሪቱ ለዓላማቸው የተመቸች ሆና እንድትኖር የማድረግ ፍላጎትና ውጥን ነው። በሌላ አገላለፅ የኢትዮጵያ የህዳሴ ጉዞ በማሰናከል ዜጎቿ በድህነትና በኋላ ቀርነት አረንቋ ውስጥ ተዘፍቃ በከፍተኛ መስዋዕትነት ትናንት ወዳሳለፉት ድቅድቅ ጨለማ የመመለስ ተግባር ነው።

 

ኢትዮጵያውያን ያሳለፉትን አስከፊ ድህነትና ኋላ ቀርነት  ጠንቅቀው ያውቁታል። ያ ያለፈ ታሪክ ዛሬ ተመልሶ እንዲመጣ አይፈቅዱም። በአክራሪነትና ፅንፈኝነት ላይ የሚኖረን ትግል ለአፍታም ቢሆን አይዘነጋም። በአክራሪዎችና ፅንፈኞች ላይ ኢትዮጵያውያን የሚወስዱት ርምጃም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ ሄዷል።

ጽንፈኞች በአገር ውስጥም ሆነ  በውጭ የሚገኙ ፀረ ሠላም  ኃይሎችን በማስተባበር የሞት የሽረት ትግል ያደርጋሉ። በአገር ውስጥ አንዳንድ ፅንፈኛ ተቃዋሚዎች  አንዳንድ አፍራሽ መገናኛ ብዙኃንን በማስተባበር በቅብብሎሽና በቅንጅት የሚሰሩበት ሁኔታም በስፋት እየታየ ነው።

 

ይሁንና በአገሪቱ ለረዥም ጊዜ የቆየው  የመቻቻል እና አብሮ የመኖር እሴት እንዲቀጥል የኃይማኖት ተቋማቱ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት እየሰጡ ነው። ከጥንት ጀምሮ በኃይማኖቶች መካከል ያለውን የመቻቻልና አብሮ የመኖር እሴት ለማስቀጠል እያንዳንዱ የኃይማኖት ተቋምና የእምነት ተከታዮቹ አገራዊ ኃላፊነት አለባቸው። ሁሉም ዜጋ በሠላም እምነቱን እንዲያራምድና ለፀጥታ መሰናክል የሆኑ አካላትን ቀድሞ እንዲከላከል ለማድረግ ለእምነቱ ተከታዮች በሠላም ዙሪያ ትምህርት እየተሰጠ ነው።

 

ኢትዮጵያዊያን አክራሪነትን ለመከላከልና የአገሪቱን ሠላም ለማስጠበቅ ከመንግሥት ጎን በመሰለፍ  የፀረ ሽብር ዘመቻን እየደገፈ ይገኛል። በዚህም በርካታ የሽብር ተግባራትን ማክሸፍ ተችሏል።

 

በኢትዮጵያ ለረዥም ጊዜ የተገነባው ተቻችሎና ተከባብሮ በሠላም የመኖር እሴት ለማስቀጠል በአሁኑ ወቅት የሚታዩ ኃይማኖትን ሽፋን ያደረጉ ተግባራትን ለመዋጋት የኃይማኖት ተቋማት በሥነ ምግባር የታነፀ ዜጋ ከመፍጠር አንፃር ትልቁን ድርሻ ወስደው ሊሰሩ ይገባል። መንግሥት ኃይማኖትን ሽፋን በማድረግ ህገ መንግሥታዊ መብቶችን የሚጥሱና የህዝብን ሠላም የሚነሱ አካላት ላይ በተለያየ ጊዜ ህጋዊ ርምጃ ወስዷል። ይኸው ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።

 

Leave a Comment