የሃገር ፍቅር ምን ማለት ነው?

ethiopia

የሃገር ፍቅር ምን ማለት ነው?

ስሜነህ

በሃይማኖታዊ አስተምህሮ  ፍቅር የወንጌል የመጀመሪያ ፍሬ ነገር ነው። አስረጅ ሲጠቅሱም ኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ በማድረግ ነው። ህይወቱ የፍቅር ውርስ ነው በማለትም የነገረ ፍቅርን ትንታኔ ይጀምራሉ። በሽተኞችን የፈወሰ፣ የተጨቆኑትን ከፍ ያደረገ፣ ሀጢያተኛን ያዳነ። በመጨረሻ የተናደዱት ወንበዴዎች ሕይወቱን ወሰዱት በማለትም የፍቅርን ጥግጋት ይገልጻሉ።  

የማህበራዊ ሳይንስ ትንታኔም ከሃይማኖታዊው አስተምህሮ ብዙም የራቀ አይደለም። እንደ በጎነት፣ ትግስት፣ ራስ ወዳድ አለመሆን፣ መረዳት መቻል እና ይቅር ባይነት የፍቅር መገለጫ ስለመሆናቸው የማህበራዊ ሳይንስ ምሁራኑ በአብዛኛው የተስማሙባቸው ናቸው። በሁሉም ግንኙነቶቻችን ውስጥ እነዚህና ሌሎች እነዚህን መሰል ባህሪዎች፣ በልባችን ውስጥ ያለውን ፍቅር ያረጋግጣሉም ይሉናል።በብዛት፣ እርስ በእርስ በምናደርገው የቀን ተቀን ግንኙነቶች ውስጥ ፍቅራችን ይታያል።

ሁሉም ጠቃሚ ነገር፣ የአንድን ሰው ፍላጎት የማወቁና ከዛም ምላሽ የመስጠቱ ችሎታችን ላይ ይሆናል ሲሉም ያክላሉ። ይህን ያህል እንደመነሻ ከወሰድን አጀንዳችን የሃገር ፍቅር ነውና ከላይ ከተመለከቱት የፍቅር መገለጫዎች ብዙም በትርጉም ወደማይለየውና በመገለጫዎቹ ብቻ የተለየ መልክ ስለሚኖረው የሃገር ፍቅር እናውራ።

በእኛ ሃገር ተጨባጭ ሁኔታ የሀገር ፍቅር ማለት ድህነትን በስራ መዋጋት ማለት ነው። የአዲስ አመት መቀበያ መርሀ ግብር አንዱ አካል የሆነው የሀገር ፍቅር ቀን ዛሬ ተከብሯል።እናም የሃገር ፍቅር በምነ ይገለጻል የሚለውን መገንዘብ ተገቢ ይሆናል።    የሃገር ፍቅር መገለጫ ከሆኑቱ መካከል ጀግኖች አባቶቻችን ተዋግተው ነፃ ሀገር እንዳስረከቡን ሁሉ እኛም ለመጪው ትውልድ ከድህነት ነፃ የሆነች ሀገር ለማስረከብ መትጋትን የተመለከተው አንደኛው ነው ።ይህም የሚረጋገጠው ሁላችንም በተሰማራንበት የሙያ ዘርፍ ጠንክረን በመስራት ነው።  

በእርግጥ አሁን ያለው ትውልድ የታላቁ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ እየተሰሩ ባሉ የልማት ስራዎች የራሱን አሻራ በማሳረፍ ለሀገሩ ያለውን ፍቅር በተግባር እያሳየ ነው። የሀገርን ሠላም በማስጠበቅ በኩል የሚኖረን ሚናም ስለሃገራችን ያለን ፍቅር የሚመዘንበት ነው።   ኢትዮጵያ በአባቶቻችንና እናቶቻችን ፅኑ ተጋድሎ ለረጅም ዓመታት ታፍራና ተከብራ የኖረች ሃገር ናት። የአሁኑ ትውልድም የአባቶቹን አደራ ጠብቆ ሀገሪቱን ወደ ላቀ የእድገት ደረጃ በማድረስ ለመጪው ትውልድ ስለሃገር ፍቅር ማስረከብ ይኖርበታል።

 

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በጋራ ሊያኖራቸው የሚችለውን ህገ-መንግስት ቀርፀው የብሔር፣ የባህልና የሃይማኖት ልዩነቶቻችንን በሙሉ ልብና በፍቅር የሚቀበል፣ በልዩነት ውስጥ ያለውን አንድነትና ውበት ለማጎልበት የሚተጋና መፃኢ ሃገራዊ ዕጣ ፈንታችንን በአስተማማኝ ሁኔታ መወሰን የሚችል ማህበረሰብ በመፍጠር የኢኮኖሚ እድገታችን በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲቀጥል ያላሰለሰ ጥረት አድርገዋል።የሃገር ፍቅር ማለት ይህንን ማስቀጠል ነው።

 

መጪው 2010 ዓ.ም መላው የሃገራችን ህዝቦች በብሩህተስፋ፣ በአንድነት፣ በፍቅር፣ በመተሳሰብና በሃገር ፍቅር ስሜት እንዲቀበሉት የዛሬው ቀን የሃገር ፍቅር ቀን ነውና ላባችንን ጠብ አድርገን መስራት ኢትዮጵያን እንወዳታለን ከሚሉ ወገኖች በሙሉ የሚጠበቅ ይሆናል ማለት ነው።

 

የዛሬው ቀን የምንወዳት የአገራችን ፍቅር ቀን ነው፤ስለሆነም እያንዳንዱ የኢትዮጵያ ዜጋ ለአገሩ ያለው ፍቅር በትክክልና በተግባር የሚገልጽበት ቀን መሆኑን መዘንጋት አይገባም። አገር ማለት ግምት የማይወጣለት፣ ትልቅ ዋጋ ያለው ትልቅ ትርጉም ያለው እንደሆነ አውቀን፤ ለአገራችን ፍቅር ደግሞ በትክክል የራሳችንን እውቀት በመጠቀም አገራችን እንድታድግ መሥራት  ማለት ነው የሃገር ፍቅር። ይህ ማለት ግን ከመንግስት በኩል የሚጠበቅ ነገር የለም ማለት እንዳልሆነ ግንዛቤ ሊያዝ ይገባል።

 

ከሰሞኑ የአዲሱን አመት ዋዜማ፤ በተለይም የሁለተኛውን ሚሊኒየም አስረኛ አመት መነሻ በማድረግ በመንግስት በኩል የተዘጋጀውን የ10 ቀናት ሁነቶች በተመለከተ ሸገር ኤፍኤም ሬዲዮ በእለተ ሰንበት የሸገር ካፌ ፕሮግራሙ ስለሃገር ፍቅር ሁነቶቹን የተመለከተ ውይይት አድርጎ ነበር። በዚሁ ውይይት ላይ የህግ ባለሙያው አቶ አብዱ አሊ ሂጅራ የሰጧቸው አስተያየቶች ስለአጀንዳችን ገዥ ይመስላሉና እዚህች ጋር ብናነሳው ተገቢ ይሆናል።

 

የመከባበርን ቀን መነሻ በማድረግ የሃገር ፍቅርን ያሄሱት አቶ አብዱ፤ መከባበር ኖር ብሎ ለታላቆቻችን ቦታ ከመልቀቅና ጤና ይስጥልኝ ብሎ ሰላምታ ከማቅረብ የዘለለ ሚስጥር እንዳለው ያወሳል። እንደሃገር ልንከባበርና በዚህም ፍቅርን ልናደረጅ የምንችለው በመንግስት ተቋማት አገልግሎት ተቀባዩ ሲከበር፤ የሃገሪቱ የሰብአዊ መብት አያያዝ ሲያምር፤ ሁሉም ሰው በህግ ፊት እኩል መሆኑ በተግባር ሲረጋገጥ፤ ከሃገሪቱ ልማት ሁሉም በየደረጃው እኩል ተጠቃሚ ሲሆን ወዘተ መሆኑን ይገልጻል።

 

ስለሃገር ፍቅር የሴቶች ቀን ብለን ስናከብር ሲል ያነሳው ነጥብም ወሳኝ ይመስላል። የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉሙሩክ ባለስልጣን ለሴቶች ንጽህና መጠበቂያ የሚውለውን ሞዴስ 30 ከመቶ  ከሌሎች የምቾት እና ተጨማሪ ቁሳቁሶች በላይ በመቅረጥ በገጠር የሚኖሩ እናቶች ዛሬም እንደቀድሞው ንጽህናቸውን ለመጠበቅ ወሳኝ የሆነውን ንጽህና መጠበቂያ ገድቦ፤ ይልቁንም በሌሎች ተመሳሳይ ሃገራት በተለይም በጋና ይህ ጉዳይ ከቀረጥ ነጻ መሆኑን በማውሳት እንደመንግስት የእናቶች ቀን ብሎ መደስኮር ስለሃገር ፍቅር እንደማያስማማ ይገልጻል።

አቶ አብዱ ሲቀጥሉም የሰላም መሰረቱ ፍቅር እንደሆነ፤ ፍቅር ደግሞ አለመወሻሸት እንደሆነ አጽንኦት በመስጠት ያብራራሉ። መንግስት ለህዝቡ የሚገባውን ቃል ሳያከብር ሲቀርና ሲዋሽ ፍቅርን ውሃ እንደሚበላው በውይይቱ ላይ አስጠንቅቋል። በሃገር ውስጥም ሆነ በውጭ በሚፈጠር ድንገተኛ አደጋ ዜጎቹ የጠፉበት መንግስት ሃዘን በመቀመጥ የሃዘን መግለጫ በማውጣትና የአበባ ጉንጉን በማስቀመጥ መንግስት ለዜጎቹ ያለውን ፍቅር ሲያረጋግጥ በዚያው ልክ የሃገር ፍቅር ይደረጃል የሚሉት አቶ አብዱ ሂጂራ የፍቅር ቀን ብሎ የመንግስት ባለስልጣናት የአበባ ስጦታ መለዋወጥ ከተራ ፕሮፖጋንዳነት የዘለለ ፋይዳ እንደሌለው በማውሳት ስለሃገር ፍቅር በመንግስትም በኩል ሆነ በህዝቡ ሊደረጉ የሚገባቸውን ነጥቦች በዝርዝር ጠቅሰዋልና ስለጉዳያችን ቀሪውን አንባብያን እና የሚመለከታቸው አካላት ከጣብያው ድረ-ገጽ አውርደው ቢያዳምጡት ጠቃሚ ይሆናል።

 

በዚሁ አግባብ መንግስትም ሆነ ህዝቡ ሃገር ማለት ክብራችን እንደሆነ ሊገነዘቡ ይገባልና የየድርሻቸውን እንዲወጡ እንሻለን። አገር የሌለው ክብር የለውም። ስለሆነም አገራችን ክብራችን እንደሆነች  አውቀን የምንሠራቸው ሥራዎች ሁሉ አገርን የሚያስከብር መሆኑን ማረጋገጥ ማለት ነው የሃገር ፍቅር። በየጊዜው የምንሠራቸው ሥራዎች የአገርን ስም የሚያስጠሩ መሆናቸውንም ማረጋገጥ ማለት ነው የሃገር ፍቅር።  

 

እርስ በእርሳችን ያለን ፍቅር ለአገራችንም ያለን ፍቅር ማንፀባረቂያ ነውና ዓለም እንዲያውቀው ማድረግ ሌላኛው የሃገር ፍቅር መገለጫ ነው። በተለይም ደግሞ አገራችንን የምንወድ ከሆነ ስለሃገር ፍቅር እያንዳንዱ ዜጋ የሚጠበቅበትን ሥራ በመሥራት ካለንበት ድህነት፣ ካለንበት ችግር እንድንላቀቅ እና ይች አገር ክብራችን ስለሆነች ስትከበር ስለምንከበር ሁላችን አገር የሚያስከብር ተግባር መፈፀም አለብን ።

 

በአጠቃላይ 2010 በአገር ውስጥና በውጭ ላሉ ዜጎቻችን የፍቅር ዓመት፣ አገራችን የምትከበርበት፣ የበለጠ የምትታወቅበት፣ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የአገሪቱ አምባሳደር ሆኖ ፍቅር የሚያሳይበትና፤ ዘመኑም የከፍታ ዘመን እንዲሆን ሁሉም ሊተጋ ይገባል ማለት ነው።

 

Leave a Comment