የሀብት ምዝገባው የ«እንዳያማህ ጥራው…» አካሄድ ይብቃ

ethiopia

በተያዘው አመት መንግስት ከወሰዳቸው እርምጃዎች መካከል በቅርቡ በቁጥጥር ስር ያዋላቸውን ተሿሚዎች፣ ባለሀብቶችና ደላላዎችን ያህል ጆሮ ገብ የሆነ እርምጃ የለም ማለት ይቻላል፡፡ መንግስት በሙስና የተጠረጠሩ ግለሰቦችን ሲያስር ይህ የመጀመሪያው ባይሆንም የአሁኑን ያህል ግን ከጫፍ ጫፍ አገርን ያነጋገረና መንግስትን አበጀህ ያስባለ እርምጃ አልታየም፡፡ ለምን? መልሱ ግልጽ ነው፡፡ አንድ በህዝብ ተመርጦ አገር የሚያስተዳድር መንግስት ለህዝቡ ሊያበስር ከሚችላቸው ጉዳዮች መካከል ከልማት ስራዎች ቀጥሎ የልማት ጸሮችን በቁጥጥር ስር አውያለሁ የሚለው ሚዛኑን ይደፋልና ነው፡፡
ማሰር የመጨረሻ አማራጭ ነው፡፡ መንግስት ለረጅም ጊዜ ሲናገር የነበረው የራሱን ተሿሚዎች በህግ ለመጠየቅ ማስረጃ እንዳጣ ነበር፡፡ ለአብነት ያህል ጥር 2009 ዓ.ም ላይ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ “በስርቆት፣ በሌብነት፣ በሙስና ተሳትፎ ማስረጃ የተገኘበት በምንም መልኩ ተጠያቂ ሳይሆን ሊቀር አይችልም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ጥርጣሬዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ወደ ሕግ ተጠያቂነት ለመውሰድ በቂ ማስረጃ ሊኖር ይገባል፡፡ ጥርጣሬዎች በሚኖሩበት ጊዜ ሊወሰዱ የሚችሉ ዕርምጃዎች ሁለት ናቸው፡፡ አንደኛው አስተዳደራዊ በሆነ መንገድ ከሥልጣኑ እንዲወጣ ይደረጋል፡፡ ከሥልጣኑ ከወጣ በኋላ በቂ ማስረጃ ካለ ወደ ሕግ ቀርቦ ይጠየቃል፡፡ በቂ ማስረጃ ሳይኖር ወደ ሕግ አቅርቦ ማሸነፍ ስለማይቻል ትርጉም የለውም ማለት ነው” ማለታቸው አይዘነጋም፡፡
እነሆ መንግስት የተቸገረበትን ማስረጃ አሰባስቦ በገባው ቃል መሰረት ሙስና ፈጽመዋል ያላቸውን የራሱን ተሿሚዎችና ሸሪኮቻቸውን በቁጥጥር ስር አውሏል፡፡ ይህ እርምጃ በራሱ በልማት ወገቡን ለማጉበጥ ሌት ተቀን እየሰራ ላለ መንግስትና ህዝብ ትልቅ ድል ነው፡፡ ድሉ ዘላቂ ሊሆን የሚችለው ግን አሁን እየተወሰደ ያለወ እርምጃ የዘመቻ ስራ ሆኖ ካልቀረ ብቻ ነው፡፡ 52 ግለሰቦች እስከ አምስት ቢሊዮን ብር የሚደርስ ጉዳት በአገር ላይ አድርሰዋል ከተባለና እርምጃው በዚህ ብቻ የሚቆም ከሆነ መጪውን ጊዜ ማሰብ ያስፈራል፡፡ ምክንያቱም የዋናው ኦዲተር መስሪያ ቤት እንኳን ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ ሦስት ተከታታይ ዓመታት በመንግስት አስፈፃሚ ተቋማት ላይ ባደረገው የተለያዩ የኦዲት ስራዎች ውጤት ከ23 ቢሊዮን ብር በላይ የፋይናንስ ህጎች ከሚፈቅዱት ውጪ ስራ ላይ መዋሉን አረጋግጧልና።
በመሰረቱ መንግስት ልማት እየተፋጠና በሄደ ቁጥር በተለይም በሰፋፊ ፕሮጀክቶች ላይ የሙስና ችግር ሊኖር እንደሚችል አስቀድሞም መናገሩ አይዘነጋም፡፡ እንዲያውም በተከበረው ምክር ቤት ሳይቀር “የመንግስት ሌቦች” እየተባለ ለዘራፊ የመንግስት ተሿሚዎችና ሰራተኞች ስም ሲሰጣቸው ቆይቷል፡፡ ይሄንን ዝርፊያ ለማስቆምም አንዱ መፍትሄ ሆኖ ቀርቦ የነበረው የመንግስት ተሿሚዎችንና ሰራተኞችን ሀብት መመዝገብ ነበር፡፡ በወቅቱም አዋጁ ተግባራዊ ተደርጎ ከአገሪቷ ርዕሰ ብሄር ጀምሮ በተዋረድ ያሉ የመንግስት ሰራተኞች ሀብት ተመዝግቧል፡፡
መመዝገቡ በራሱ ግብ አልነበረምና የተመዘገበው ሀብት በአዋጁ መሰረት ለህዝብ ይፋ መደረግ ነበረበት፡፡ ነገር ግን አልሆነም፡፡ ለምን ይፋ አይደረግም? ተብሎ ሲጠየቅ የተሰጠው ምላሽም መረጃውን ለሚፈልግና በጽሁፍ ለሚጠይቅ አካለ ይሰጣል የሚል ሆኗል፡፡ ይሄንን በመቃወምም በርካታ የህግ ምሁራን የአዋጁን አንቀጽ እየጠቀሱ ቢከራከሩም ምላሹ ዛሬም ድረስ ያው “ቄሱም ዝም መጽሐፉም ዝም” ሆኗል፡፡
የተመዘገበው ሀብት ለህዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ ይፋ ቢሆን ኖሮ ህዝቡ የቀረና የተደበቀ ሀብትና ንብረት ካለ ማጋለጡ አይቀርም ነበር፡፡ ይሄ ግን እንዲሆን አልተፈለገም ወይንም መንግስት ባሰበው ልክ አዋጁን መተግበር ተቸግሯል፡፡ በዚህም ምክንያት እየተከፈለ ያለው ዋጋ ሊከፈል የግድ ሆኗል፡፡ አንድ ገቢው በታወቀ የመንግስት የስራ ሃላፊ መኖሪያ ቤት ውስጥ አይደለም በአምስትና አስር አመት ውስጥ ይቅርና እስከ ጡረታ እድሜው ቢሰራ ሊያጠራቅም የማይችለው ገንዘብና ሊያፈራ የማይችለው ሀብት ሊገኝም ችሏል፡፡ ይሄንን ይሄንን ስንመለከትም አዋጁም ሆነ ምዝገባው “እንዳያማህ ጥራው እንዳይበላ እጁን ያዘው” ሆኖ ቀርቷል ለማለት ያስደፍረናል፡፡
ስለሆነም አሁንም ቢሆን የመንግስት ተሿሚዎችንና ሰራተኞችን ሀብት መመዝገቡ ተጠናክሮ ይቀጥል፤ መመዝገብም ብቻ ሳይሆን ለህዝቡ በቀላሉ ሊመለከትና ሊረዳ በሚችልበት መንገድ ይፋ ይደረግለት፡፡

Leave a Comment