ኦሮሚያ ክልል በአምስት ወራት 10ሺ ፖሊሶች አስመርቋል

የኦሮሚያ ክልል ከትናንት በስቲያ በአላጌ ጊዜያዊ ማሠልጠኛ ማዕከል ፖሊሶችን ሲያስመርቅ፤

• ወቅታዊ ችግሮችን ለማቃለል ተስፋ ተጥሎባቸዋል

የኦሮሚያ ክልል ባለፉት አምስት ወራት በህገመንግሥት የበላይነትና አጠባበቅ፣ በመልካም አስተዳደር ማስፈን፣ በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና በሌሎች ፖሊሲያዊ ሙያ እና አስተምህሮ ያሰለጠናቸውን 10ሺ የፖሊስ አባላት አስመርቋል። ምሩቃኑ ለክልሉ ወቅታዊ ችግሮች እልባት እንደሚያበጁም ተስፋ ተጥሎባቸዋል።

ክልሉ ከትናንት በስቲያ በአላጌ ጊዜያዊ ማሰልጠኛ ማዕከል ለአንድ ወር በተለያዩ ፖሊሳዊ ሙያ ያሰለጠናቸው 1781 ፖሊሶችን ባስመረቀበት ወቅት የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ረዳት ኮሚሽነር አበበ ለገሰ እንደተናገሩት፤ ስልጠናው አገራዊ ተልዕኮ ያለው ሲሆን፣ የልማት እና መልካም አስተዳደር ጥያቄ አንግቦ ለተነሳ ህዝብ ምላሽ ለመስጠት የጎላ ድርሻ ይኖረዋል። የፖሊስ ሚና ሠላም ማስከበር ስለሆነ ሃቅ ሳይዛባ በቅንነት ማገልገልና በማናቸውም ገንዘብ ለማይተመንና ለህዝብ ሲባል የህይወት መስዋዕትነት ለመክፈል ለገቡት ቃል ሁሌም ታማኝ መሆን እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

እንደ ረዳት ኮሚሽነሩ ገለፃ፤ በአገሪቱ ያሉ ዜጎች ሁሉም ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በመሆናቸው ያለአንዳች አድሎ አገልግሎት መስጠት ይገባል። በክልሉ ያለውን ሠላም እና መረጋጋት በተጠናከረ ሁኔታ እንዲቀጥል፤ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ የአስተዳደራዊ ወሰን ይገባኛል እና ሌሎች ችግሮችን ለማቃለልም ሰልጣኞቹ የጎላ ሚና እንደሚኖራቸው ተናግረዋል። በስልጠናው ወቅት እርስ በርስ የቀሰሙትን እውቀት እና ልምድ በአግባቡ እንዲተገብሩም አሳስበዋል ።

በኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ የአላጌ ፖሊስ ስልጠና አቅም ግንባታ ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር መስፍን በላቸው በበኩላቸው፤ ስልጠናው በአሁኑ ወቅት በክልሉ ብሎም በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋሉ የፀጥታ ችግሮች አልባት እንዲያገኙ እና የህዝብ ሠላም እንዲጠበቅ ከፍተኛ አበርክቶ እንደሚኖረውና ስልጠናው እነዚህን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

የአላጌ ጊዜያዊ የፖሊስ ማሰልጠኛ የስልጠና ክፍል ኃላፊ ኢንስፔክተር ድሪባ ለታ እንዳሉት፤ ባለፉት አምስት ወራት አገራዊ እና ክልላዊ ጉዳዮችን በተመለከተ 10ሺ የፖሊስ አባላት የጥልቅ ተሃድሶ ስልጠና ወስደዋል። ስልጠናውም በዋናነት በሕገመንግሥት የበላይነትና አጠባበቅ፣ መልካም አስተዳደር ማስፈን፣ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ፣ ወንጀል መከላከል እና ፖሊሳዊ ሥነ ምግባርን መላበስና በታማኝነት መተግበርን ያካተተ እንደነበር አስታውሰው፤ ከትናንት በስቲያ የተመረቁት 1781 የመጨረሻው ዙር ምሩቃን 197 ሰዓታት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መሰልጠናቸውን ጠቁመዋል።

ሰልጣኞቹ በበኩላቸው፤ በክልሉ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ቀጣይነት እንዲኖራቸውና ሠላምና መረጋጋቱ እንዲሰፍን ስልጠናው ተጨማሪ እውቀት እንዳፈሩበት ጠቁመዋል። አገሪቱ በቀጣይ ሊገጥማት በሚችሉ የሠላም እንቅፋቶችና መፍትሄ ላይ ያተኮረ ሳይንሳዊ ስልጠና እንደወሰዱም ተናግረዋል። ይህም በማናቸውም ቦታ እና ጊዜ የሚሰጣቸውን ኃላፊነትና ግዳጅ በቅንነት እና ታማኝነት ለመወጣት ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥርላቸው ገልፀዋል። ስልጠናው ፖሊሳዊ ሳይንስ፣ የሥነልቦና ዝግጁነት፣ ታክቲክ እና ሥነምግባር ያካተተ እንደነበርና ለቀጣይ ተግባራት የበለጠ ጥንካሬ የሚሰጣቸው እንደሆነም ተናግረዋል።

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ባለፉት አምስት ወራት 10ሺ ለሚሆኑ ፖሊሶች በተለያዩ አገራዊ እና ህገመንግሥታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ስልጠና መስጠቱ ተገልጿል።

ክፍለዮሐንስ አንበርብር

Leave a Comment