እኩል ተጠያቂነት ሊነግስ ይገባል!

እኩል ተጠያቂነት ሊነግስ ይገባል!

ዳዊት ምትኩ

በህገ መንግስቱ መሰረት በክልልም ይሁን በፌዴራል መንግስት ደረጃ የተጠያቂነት መንፈስ መንገስ ይኖርበታል። የሚከሰቱት ችግሮች ስፋትና ጥበታቸው የሚለያይ ካልሆነ በስተቀር ለሁሉም እኩል ተጠያቂነት መንገስ መቻል አለበት። ተጠያቂነትን ለማንገስ በሁሉም ክልሎች ውስጥ አንድም ሰው መሞትና መፈናቀል የለበትም። በየደረጃው የሚገኝ አመራር ‘ሁሉም ህዝብ የእኔ ነው’ የሚል አስተሳሰብን ሊይዝ ይገባል። በክልልም ይሁን በማዕከላዊ መንግስት ደረጃ የህዝባዊነት መንፈስ መኖር አለበት።

እኩል ተጠያቀነትን ማንገስ መቻል የአንድ ሀገር ዴሞክራሲን የመተግበር ግዴታ ነው። እኩል ተጠያቂነትን ለማንገስ ግልፀኝነት ያስፈልጋል። ግልፀኝነትና የተጠያቂነት አሰራርን ለመተግበር የህግ የበላይነት መረጋገጥ አለበት።

በህገ መንግስታችን ላይ ማናቸውም የመንግስት ስራዎች ግልፀኝነትን ማዕከል አድርገው መከናወን እንዳለባቸው ተደንግጓል። ህገ መንግስቱ የህግ የበላይነትን ለማስጠበቅ ሲል ከህግ አግባብ ውጪ ስልጣን መያዝ የተከለከለ መሆኑን ደንግጓል።

ይህ አሰራር በህገ መንግስቱ አንቀፅ 56 ላይ የተገለፀ ጉዳይ ነው። በዚህ አንቀፅ መሰረት በምክር ቤተ አብላጫ መቀመጫ ያገኘ የፖለቲካ ድርጅት ወይም ጣምራ ድርጅት የፌዴራሉን መንግስት የህግ አስፈፃሚ አካል እንደሚያደራጁና እንደሚመሩ ተገልጿል።

የህግ የበላይነት መከበር ለሀገር ሰላምና መረጋጋት ብሎም ልማትን ለማሳለጥ ቁልፍ ሚና ይኖረዋል። የህግ የበላይነት ከሌለ ሰላም የሚባልን ነገር ማሰብ አይቻልም። ሰላም ከጠፋ ደግሞ ስለ ልማትና ዴሞክራሲ ማሰብ አይቻልም። ፀረ-ልማትዊነትና ፀረ-ዴሞክራሲያዊነት ቦታውን ይረከባሉ። ይህ ሁኔታ ደግሞ እንደ እኛ ሰላምን፣ ልማትንና ዴሞክራሲን የህልውናው ጉዳይ ላደረገ ሀገር አሜኬላ እሾህ መሆኑ አያጠያይቅም።

ፌዴራላዊ ስርዓቱ የህግ የበላይነትን በሚገባ የሚያስከብር ነው። የህግ የበላይነትን ተላልፎ የሚገኝ ማንኛውም ዜጋ ተጠያቂ ይሆናል። ሁሉም ሰው በህግ ፊት እኩል እንደመሆኑ መጠን፤ በመረጃና በማስረጃ በተረጋገጠበት ጥፋት ልክ ተጠያቂ ይሆናል። ይህ በማንም ላይ የሚሰራ ተግባር ነው።

አንዱን ዜጋ ከሌላው በማበላለጥ የሚከናወን የህግ አሰራር በፌዴራላዊ ስርዓቱ ውስጥ ፈፅሞ ሊኖር አይችልም፤ መቼም ቢሆን። እናም የህግ የበላይነትን ኢትዮጵያ ውስጥ ማስከበር ማለት የህገ መንግስቱን መንፈስ በሁሉም መስኮች ማስፈፀም ማለት መሆኑን የትኛውም ዜጋ ግንዛቤ መያዝ ያለበት ይመስለኛል። ይህም የህገ መንግስቱን የግልፀኝነት አሰራር የሚደግፍ ነው።

የህግ የበላይነትን አለማረጋገጥ ህገ መንግስቱን መፃረር ነው። ምክንያቱም ህገ መንግሰቱ የህጎች ሁሉ የበላይ እንደመሆኑ መጠን፤ እርሱን ተከትለው የሚወጡ አዋጆችን ተፈፃሚ አለማድረግ መልሶ ህገ መንግስቱን መቃወም ነው። ይህ እንዲሆን ደግሞ አስፈፃሚውም አካል ሆነ ማንኛውም ዜጋ መፍቀድ ያለበት አይመስለኝም።

የህግ የበላይነትን መፃረር ስርዓት አልበኝነትን የሚፈጥር ከመሆኑም ባሻገር፤ ህጎች ለሁሉም ዜጎች እኩል እንዳይሰሩ ያደርጋል። እናም ‘ሁሉም ሰው በህግ ፊት እኩል ነው’ የሚለውን ህገ መንግስታዊ መርህ ገቢራዊ ለማድረግ የህግ የበላይነት በማያሻማ ሁኔታ መረጋገጥ ይኖርበታል። ይህ ሲሆንም ግልፀኝነት ይጎለብታል።

ግለፀኝነት ለተጠያቂነትን ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል። ተጠያቂነት ደግሞ እኩልነትን ያሰፍናል። እኩልነት ደግሞ ህገ መንግስታዊ መሰረት ያለው ነው። የአገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ማንነቶች አዲስ የእኩልነት መንፈስ መክፈቱንና እንደ ማረጋገጫ መሣሪያ ስለተወሰደም በዚህ አወቃቀር አዲስ የእኩልነት ግንኙነትና የጋር ህልውና እንዲመሠረት ተደርጓል፡፡

በዚህም የአዲሲቷን ኢትዮጵያ የወደፊት ዕድል የመወሰን ሥልጣን ባለቤት መሆን እንዳለባቸው በወኪሎቻቸው አማካይነት ይፋ አድርገዋል፡፡ በፌዴሬሽኑ ምሥረታ ወቅት የገቡትን ቃል በአፈፃፀም ሂደት እንዳይዛነፍ የመጠበቅ ኃላፊነት የሚሰጣቸውን ህገ መንግሥት የመተርጎም ሥልጣን ህዝቦች እውን አድርገዋል፡፡ ይህም በመከባበር፤ በመተማመንና በመተባበር በእኩልነት አብሮ ለመኖር የሰላም ዋስትና ሆኗል፡፡

በፌደራል ስርዓቱ አመሰራረት ወቅትም እነዚህን የተራራቁ ፍላጎቶች የነበሯቸው የፖለቲካ ኃይሎች ተቀራርበውና ተሰባስበው በህብረቱ እንዲቀጥሉ በመስማማታቸው፤ ለቁርሾ የሚያበቃ ነገር እንዳይኖር ሰርተዋል፡፡

በተለይም ሃይማኖቶችና እምነቶች ተቻችለውና ተከባብረው ለመኖር የነበራቸው ፍላጐት የሚጫኑ የአክራሪነት ድርጊቶችን በመቃወም እኩልነታቸውን ማረጋገጥ ችለዋል፡፡ ይህ ሁኔታ ብዙ ፈተና ተግዳሮቶችን ያለፈ ቢሆንም ሁሉም የአገራችን ህዝቦች በእኩልነት መንፈስ በጋራ ሆነው አዲሲቷን ኢትዮጵያ እውን እያደረጉ ነው፡፡

የእኩልነት መብቶች ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ላይ የሚያተኩሩ ናቸው። በአሁኑ ሰዓት ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት በብሔሮች መካከል የአመለካከት ዝምድና መፍጠር ችሏል፡፡ በመሆኑም ሀገሪቱን ወደ ላቀ ደረጃ ያደረሰ እሴት ነው፡፡ የትምክትና ጠባብነት ፈተናዎች በአገሪቱ ቢኖሩም በዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት መሸነፋቸው አይቀሬ ነው።

ባለፉት ዓመታት ትምክህትና ጠባብነትን ለመዋጋት በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል። ሆኖም አመለካከቱ አልፎ አልፎ የሚያንሰራራው በኪራይ ሰብሳቢነትና ባልተገባ ጥቅም በሚሹት አካላት አማካኝነት በመሆኑ ሁለቱን ማነቆዎች ከሕዝቡ ጋር በመታገል ለውጡን ማምጣት ይቻላል። እኩል ተጠያቂነትንም ለማስፈን ያግዛል።

እኩል ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥም የጋራ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በመብለጥም ሆነ በማነስ ስሜት ውስጥ ሳይገባ በጋራ መጠቀምን ያካትታል። አካባቢን ከማልማት አኳያም ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ከባቢን በተገቢው መንገድ ለልማት የማዋል ሁኔታን የሚያካትት ነው።

ብዙ ህዝቦች ባሉበት እንደ ኢትዮጵያ ባለ አገር የሕዝቦች የእርስ በርስ ግንኙነትን በጤናማ አስተሳሰብ በመምራት በመካከላቸው ፍቅር፣ መከባበርና መተሳሰብ እንዲዳብር ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ነው። ይህ ግንኙነት ጤናማ ባልሆነ አስተሳሰብ በሚመራበት ጊዜ ግጭት መከሰቱ አይቀርም። እናም ጤናማ ግንኙነትን ለመፍጠር እኩል ተጠያቂነትን ማንገስ ያስፈልጋል።

እርግጥ የትምክህትና የጥበት ሃይሎች ያለፉትን የተዛቡ ታሪካዊ ግንኙነቶችን በማንሳት አንድን ህዝብ ለመኮነን ይሞክራሉ።  ይህ ፍፁም ከዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት እሳቤ ጋር የሚሄድ አይደለም። እነዚህ ኃይሎችን ለይቶ ማወቅ ያስፈልጋል። ኃይሎቹ ከህዝቦች ግጭት ለማትረፍ የሚፈልጉ ጥገኞች በመሆናቸው በእነርሱና በተከታተዩቻቸው ላይ የእኩል ተጠያቂነትን አሰራር ማንገስ ያስፈልጋል። ይገባልም።

 

 

 

Leave a Comment