ኢትዮጵያ በውጭ መገናኛ ብዙኃን እይታ

ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች እያከናወነች ያለውን ስኬታማ ተግባራት የተለያዩ ዓለምአቀፍ መገናኛ ብዙኃን በድረገጾቻቸው ለንባብ አብቅተዋል። በተለይም በኢኮኖሚው መስክ እየታየ ያለው ለውጥ፣ የውጭም ሆነ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በማከናወን ላይ ያሉት ተግባራት በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ሆነው ለመውጣት የሚያስችላቸውን አቅጣጫ እንደያዙ ዘገባዎቹ የዳሰሷቸው እውነታዎች ናቸው። ባለፈው ሳምንት መልካም ገጽታዎችን አጉልተው ካስነበቡት መካከል የተወሰኑትን እንዳስሳለን።

 ለአፍሪካ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ወሳኝ ነው ተመራማሪዎች

የአፍሪካን ግብርና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ማገዝ ለዜጎቿ ዘላቂ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እንደሚያስችል ዴይሊ ኔሽን ዘገበ፡፡ ከአፍሪካ አገራት የተውጣጡ የግብርና ባለሙያዎች አዲስ አበባ ተሰባስበው የመከሩ ሲሆን፣ የአህጉሪቱ የሰብል ምርት በዕድሜ በገፉ ሰዎች እየተሰራ እንደሆነና አዲሱ ትውልድ ከግብርና ሥራ ይልቅ ወደ ቢሮ ሥራ እንደሚያተኩር በጥናት ተረጋግጧል፡፡ አዲሱ ትውልድ የአባቶቹን የግብርና ሥራ ለማስቀጠል ካልቻለ ትውልድ ሲተካ ምርታማ መሬቶች ጾም የሚያድሩበት አደገኛ ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችልም ባለሙያዎቹ አስታውቀዋል፡፡

የምሥራቅና ደቡብ አፍሪካ የጋራ ገበያ፤ በባዮ ቴክኖሎጂና በባዮ ሴፍቲኔት ላይ ለመወያየት ባዘጋጀው መድረክ ከአፍሪካ አገራት የተውጣጡ ባለሙያዎችና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ ግብርናን ለሁሉም የዕድሜ ክልልና ፆታ ተስማሚ በማድረግ እንዲሁም በቴክኖሎጂ መደገፍ እንደሚያስፈልግ ተገልጿል፡፡

ባዮ ቴክኖሎጂን መጠቀም እንደ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሱዳን፣ ኡጋንዳና ግብፅ ያሉ አገራት በተለይ በምግብ ደህንነት፣ በማህበራዊ ምጣኔ ሀብት እና በአካባቢ ደህንነት ላይ ባለው ተፅእኖ ሙሉ ለሙሉ ተቀባይነት አላገኙም፡፡ የግብርና ምርትን ለማሳደግ ጥቅም ላይ የሚውሉ የቴክኖሎጂ ግብአቶች ሲጠቀሙ በተፈጥሮ ደህንነት ጉዳት እንዳይደርስ ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ እንደሚገባም ተጠቁሟል፡፡ በተመራማሪዎችና በሚዲያ ተቋማት በኩል መልካም ግንኙነት መፍጠር ባዮቴክኖሎጂን ከባዮሴፍቲ ጋር በማቀናጀት የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲፈጠር ከፍተኛ ሚና እንዳላቸውም ተገልጿል፡፡

(Daily nation 12 March 2017)

 ሴቶችን ከጥቃት ለመታደግ ማህበሩ ዓይነተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል

በኢትዮጵያ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጾታዊና አካላዊ ጥቃቶችን ለማስቀረትና የሴቶችን ክብርና ሕይወት ለማስጠበቅ የተቋቋመ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ነው። (opriss) ይሰኛል። ድርጅቱ ተቀማጭነቱን በአዲስ አበባ ከተማ አድርጎ ከተመሰረተበት ጀምሮ በ17 ዓመት ታሪኩ የጎዳና ተዳዳሪ ሴት ሕፃናት ከጥቃት በመከላከል የበርካታ ሴቶችን ሕይወት አስተካክሏል፡፡ ድርጅቱ አካላዊ ጥቃት የተፈጸመባቸው፣ አሳዳጊ ያጡ ሴት ሕፃናት፣ ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸው እና መሰል ሴቶችን በመቀበል እንደሚንከባከብ ዢንዋ ድረገጽ አስነብቧል፡፡

ምንም እንኳ በሀገሪቱ በሴቶች ከፍተኛ ጥቃት የሚደርሱ ቢሆንም ጉዳዩ የሚመለከታቸውና ድርጅቱ እያደረጉ ባለው ጥረት ከፍተኛ ለውጥ መምጣቱን ጠቅሷል፡፡ ያለ ዕድሜ ጋብቻ በማስቀረት፣ ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶች በማስተማር መልካም ተመክሮ እንዳለውም ዘገባው ጠቁሟል፡፡ ድርጅቱ ከ3 ሺ በላይ ሴት ወጣቶችን በመያዝ መኖሪያ ሰጥቶ ከተፈጸመባቸው ጾታዊ ጉዳት ለማገገም እየረዳቸው እንደሚገኝም ተጠቁሟል፡፡

በድርጅቱ የሚገኙ ቀደም ሲል ጉዳት የደረሰባቸው ሴቶች አሁን በሚሰጣቸው አገልግሎት ትምህር ታቸውንም እንዲከታተሉ መደረጋቸው ወደ አዲስ ሕይወት እንደሚመለሱ አመላካች መሆኑም ተጠቅሷል፡፡ በገዛ ቤተሰቦቿ ጥቃት የተፈጸመባት አንዲት ወጣት እንደገለጸችው ድርጅቱ ባደረገላት ድጋፍ የደረሰባትን ሥነ ልቦናዊና አካላዊ ጥቃት በማገገም ትምህርቷን እንድትከታተል እየረዳት መሆኑን ገልጻለች፡፡ ጾታዊ ጥቃቶች በዓለም ደረጃ በተለያዩ አገሮች የሚፈጸሙ ሲሆን፣ እንደነዚህ የመሳሰሉ ድርጅቶች የሴቶችን ሕይወት ለመታደግና ከጥቃት ለመንከባከብ እጅግ አስፈላጊ መሆናቸው ድረገጹ ይጠቁማል፡፡

(Xinhua 16 March 2017)

 30 ሺ በላይ የሥራ ዕድል መፍጠር የሚያስችል ኢንዱስትሪያል ፓርክ ሊገነባ ነው

ኢትዮጵያ ሦስተኛው የተቀናጀ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ በይርጋዓለም ከተማ ለመክፈት መዘጋጀቷን አፍሪካ ቢዝነስ ኮሙኒቲስ ድረገጽ አስነብቧል። ኢንዱስትሪ ፓርኩ በግብርና ዘርፍ ትኩረት በማድረግ የገጠር ኢንዱስትሪያል በማንቀሳቀስ እንዲሁም እስከ 134 ሺ የሚሆኑ የሥራ ዕድሎች ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የተቀናጀ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኩ ዘመናዊ መሠረተ ልማቶችን ለማቅረብ እንዲሁም ኩባንያዎች ለማገዝ እንደሚያገለግል እና ለሀገር ውስጥና ውጭ ባለሀብቶች ትኩረት በመሳብ የተሻለ የልማት ክህሎት እንደሚቀመርበት ይታመናል፡፡

በመሠረተ ድንጋይ ማስቀመጡ ሥነሥርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት የተባበሩት መንግሥታት ዓለም አቀፍ ልማት ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሊ ዮንግ የኢትዮጵያ መንግሥት የተባበሩት መንግሥታት ልማት ድርጅቱ በጋራና ከሌሎች አጋሮች በመተባበር የፓርኩ ዋና ማዕከል የት መሆን እንዳለበት መክሯል። ድርጅቱ ከመንግሥት ጋር በቅርብ በመስራት በሌሎች ክልሎች የሚገነቡ እህት ኢንዱስትሪዎች ማለትም በአማራ፣ ኦሮሚያና ትግራይ እንደሚከታተልና አስፈላጊ ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡ የፓርኩ ግንባታ የመሠረተ ድንጋይ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ተቀምጧል፡፡

(Africa Business Communities 16 March 2017)

 ዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ሰፊ የገበያ አማራጭ ማግኘቱ ተሰማ

የናይጄሪያው ባለሀብት የሲሚንቶ ፋብሪካ ዳንጎቴ፣ እአአ በ2016 አዲስ ሪፖርቱ ላይ እንደገለጸው፣ በኢትዮጵያ ገበያው እንደደራለት አስታውቋል፡፡ ፋብሪካው በኢትዮጵያ እስከ 2 ሚሊዮን የሚሆን ሲሚንቶ መሸጡን ጠቅሷል፡፡

በድርቁ ምክንያት ከተከሰተው የሽያጭ መቀነስ፣ በተለያዩ አካባቢዎች በሀገሪቱ በተነሱ ብጥብጦች ባሻገር ኩባንያው በሰባት ወራት ውስጥ ከፍተኛ ምርት መሸጡን አስታወቀ፡፡ በኢትዮጵያ የሲሚንቶ ዋጋ በቶን ከ80 እስከ 82 ዶላር እንደሚሸጥም የወርልድ ሰሜንት ድረገጽ ዘገባ አስታውቋል፡፡

በዝቅተኛ የነፍሰ ወከፍ ተጠቃሚነት ማለትም 60 ኪሎግራም ሲሚንቶ በአንድ ሰው ጥቅም ላይ ከመዋሉ እና ከአገሪቷ ኢኮኖሚያዊ እድገት ጋር አያይዞ በኢትዮጵያ ያለው የሲሚንቶ ኢንዱስትሪ በጣም አዋጭ እንደመሆኑ፤ እንዲሁም ፋብሪካው በሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ ከሚያደርገው የማስፋፋት ሥራው በእጥፍ በመጨመር ለመንቀሳቀስ እንደሚፈልግም ጠቁሟል፡፡

ዳንጎቴ በአገር ውስጥ ከሚያደርገው የምርት አቅርቦት በተጨማሪ ለውጭ ገበያ የሲሚንቶ ምርት መላክም ጀምሯል፡፡ ፋብሪካው እአአ በ2016 .ም ለውጭ አገር ከላካቸው ምርቱ በኬንያ ገበያ በቶን በ74 ዶላር በማቅረብ የኬንያ የሲሚንቶ አምራቾችና አቅራቢዎች በመወዳደር ዓይነተኛ ውጤት አስመዝግቧል፡፡ በተጨማሪም ፋብሪካው ምርቱ ወደ ሶማሊያና ደቡብ ሱዳን ገበያ አቅርቧል፡፡

(World cement 14 March 2017)

 ለፖታሽ ማዕድን አምራች ኩባንያው የማዕድን ሥራ ፍቃድ ተሰጠው

የእንግሊዙ የማዕድን አውጪ ኩባንያ በኢትዮጵያ አፋር ክልል ደናክል ላይ በሚያደርገው የፖታሽ ማዕድን የማምረት ፕሮጀክት ሥራው በኢትዮጵያ መንግሥት የሚኒስትሮች ምክር ቤት የፖታሽ ማምረት ፍቃድ ተሰጠው፡፡ ኩባንያው የተሰጠውን ፍቃድ ፖታሽየም አመንጪ ማዕድናትን ትኩረት በማድረግ ለመፈለግ የሚያስችለው ሲሆን፣ ማዕድኑን የማጣሪያ ማሽን በመታገዝ የማጣራት ሥራም ያከናውናል፡፡ የማዕድን አውጪ ኩባንያው «ሲርከም ሚነራልስ» የመጀመሪያ ደረጃ የማምረት እቅዱ በቶን እስከ 940 ዶላር እንደሚደርስና ከካናዳና ቤላሩስ ጋር በቶን 2000 ዶላር ሲነጻጸር ከፍተኛ አዋጪነት እንደሚኖረው ተጠቁሟል፡፡

በዓመት እስከ 2 ሚሊዮን ሙሪያት ፖታሽ እንዲሁም 750 ሺ በዓመት የፖታሽ ሰልፌት ከዝቅተኛ ዋጋና ዝቅተኛ የአደጋ ተጋላጭነት ለማምረት ይችላል፡፡ የመጀመሪያ የማምረት ሥራው በ2ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር የጀመረ ሲሆን፣ 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር እንደሚፈለግና ከመጀመሪያ የማዕድኑ ምርት ለመሸፈን መታቀዱን ማይኒግ ዊክሊ ድረገጽ አስነብቧል፡፡ የማምረቻ ዋጋው በዓለም ዝቅተኛ ሲሆን ይህም ለሙሪያት ፖታሽ 38 ዶላር በቶን እንዲሁም ለሳልፌት ፖታሽ 112 ዶላር በቶን ነው፡:

(Mining weekly 14 March 2017)

 

Leave a Comment