ኢትዮጵያና ግብፅ በጋራ ተጠቃሚ የሚሆኑባቸው በርካታ ዕድሎች አሏቸው – ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ

ኢትዮጵያና ግብጽ ተጠቃሚ መሆን የሚችሉባቸው በርካታ እድሎች እንዳሏቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ተናገሩ።

ሚኒስትሩ ይህን ያሉት በ6ኛው የኢትዮ-ግብፅ የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።

ሁለቱ አገራት በርካታ ዘመናትን የተሻገረ ግንኙነት፤ ህዝቦቻቸውም በባህል፣ በታሪክና በኢኮኖሚ መስኮች የጋራ ትሩፋቶች እንዳሏቸው ገልጸዋል።

“በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያና ግብፅ መካከል ያለው ግንኙነት ከዓመታት በፊት ከነበረበት ረጅም መንገድ መጥቷል” ያሉት ዶክተር ወርቅነህ በመካከላቸው የሚደረገውን ቋሚ ምክክር ለአብነት አንስተዋል።

የሚኒስትሮቹን የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ በመሪዎች ደረጃ ለማካሄድ መወሰኑም የሁለቱ አገራት ግንኙነት በትክክለኛው መስመር እየተጓዘ ስለመሆኑ ማሳያ ነው ብለዋል።

በቀጠናው ሠላምና መረጋጋትን በዘላቂነት ለማስፈን የብጥብጥ መንስኤ የሆኑትን እንደ ሽብርተኝነት፣ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና የሃይማኖት አክራሪነትን መዋጋት እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።

የህዳሴውን ግድብ አስመልክተው ሲናገሩም “አሁንም በድጋሚ ግልጽ ለማድረግ የምፈልገው የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት በግብፃውያን ወንድሞቻቸው ጥቅም ላይ ጉልህ ተጽእኖ የማድረግ ምንም አይነት ዓላማ እንደሌላቸው ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ መካከል የሚኖር አግባብ የሆነ ጥያቄ በወንድማማችነት በሚደረግ ውይይትና ድርድር ብቻ መፈታት እንዳለበትም ነው ዶክተር ወርቅነህ ያመለከቱት።

የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሽኩሪ በበኩላቸው ሁለቱ አገራት በአፍሪካ ቀዳሚና ታሪካዊ ግንኙነት የመሰረቱ መሆናቸውን አስረድተዋል፤ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩት እ.ኤ.አ በ1927 መሆኑን በመጥቀስ።

በመሪዎች ደረጃ እየተካሄደ ያለው 6ኛው የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ ለአገራቱ ቀጣይ ግንኙነት መዳበር ገንቢ ሚና እንደሚኖረውም ተናግረዋል።

ግብፅ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ለማሳደግ ትልቅ ውሳኔ ማሳለፏንና ይህም የሁለቱን አገራት ህዝቦች ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

Leave a Comment