ኢህአዴግ ዛሬም እንደቀድሞው …!

ኢህአዴግ ዛሬም እንደቀድሞው …!

 

ወንድይራድ ኃብተየስ

 

ኢህአዴግ ባለፉት 27 ዓመታት ኢትዮጵያን በስኬት  ጎዳና  መርቷታል። በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ህገመንግስታዊና ጠንካራ  መንግስት ተቋቁሟል፤ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ነጻነትና እኩልነት ተረጋግጧል፣ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በመገንባት ላይ ነው፣ በተከታታይ ለ15 ዓመታት  ባለሁለት አሃዝ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ  ዕድገት በማስመዝገብ  ሁሉም  በየደረጃው ፍትሃዊ ተጠቃሚ የሚሆንበት ሁኔታ ተመቻችቷል፤ በአገራችን ድህነትን ከግማሽ በላይ መቀነስ ተችሏል፤  በስኬታማ የዲፕሎማሲ ስራዎች የአገራችን ተሰሚነት በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም ዓቀፍ ደረጃ  እጅጉን አድጓል፤ አገራችን በፖለቲካ ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚም በአፍሪካ ትኩረት የምትስብ  አገር በመሆን ላይ ነች። ኢህአዴግ ለአገራችን ስኬቶች ሁሉ  የአንበሳውን ድርሻ  አበርክቷል፤ በማበርከትም ላይ ይገኛል። ኢህአዴግ   በየጊዜው ችግሮቹን በመለየት ለማስተካከል የሚጥር  ተማሪ  ፓርቲ ነው።   

 

በአገራችን ታሪክ ኢህአዴግ በመልካም ስነ-ምግሩ በጥሩ ዓረዓያነቱ በቀዳሚነት የሚፈረጅ ብቸኛ ፓርት ነው ብል አብዛኛዎቻችንን የሚያስማማ እውነታ ነው፡፡ የድርጅቱ የውስጥ አሰራር የግለሰቦች ሃሳብ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የሚንሸራሸርበት ሃሳብ በነፃነት የሚፋጭበት፤ ሁሌም የብዙሃኑ ድምጽ የበላይነት የነገሰበት ፓርቲ  ነው፡፡ ይህ አሰራሩም ብዙሃኑን ያማከለ፣ ከአንባገነናዊነት የፀዳና በግልፅነት ላይ የተመሰረተ አሰራርን የሚተገብር በመሆኑ በርካታዎችን ወደፓርቲው  አባልነት እንዲሳቡ ያደረገ ነገር ይመስለኛል፡፡

 

በኢህአዴግ ውስጥ ግምገማ ትልቅና የቆየ ባህል ነው፡፡ ይህ የግምገማ ባህሉ ድርጅቱን ጥሩ የስነ ምግባር ምንጭ እንዲሆን፣ አባላት ተጠያቂነትን እንዲያውቁና የተጣለባቸው ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ ካደረጋቸው ምክንያቶች ቀዳሚውና ዋንኛው ጉዳይ ነው፡፡ ግምገማ ከኢህአዴግ ጋር አብሮ የኖረ ባህል በመሆኑ ዕድሜው ከድርጅቱ ዕድሜ ጋር እኩል ነው፡፡

 

ይህ ሂደት ኢህአዴግን ከትጥቅ ትግሉ ጀምሮ እስከ አገርና ህዝብ መምራት ደረጃ ውጤታማ እንዲሆን ካደረጉት አበይት ምክንያቶች ውስጥ አንዱና ቀዳሚው ነው፡፡ አሁንም ኢህአዴግን በስኬት ጎዳና እንዲጓዝ የግምገማ ባህሉ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።

 

በኢህአዴግ የውስጥ ባህል አመራሮችን የመተካካት ሂደት ዛሬም ወደፊትም የሚቀጥል ዑደት ነው፡፡ ሰሞኑን  የድርጅቱ ከፍተኛ አመራር የነበሩ አንዳንድ አባላት ከመንግስት የስራ ሃላፊነታቸው ለመሰናበት ጥያቄ አቅርበዋል። ይህን ሁኔታ የተመለከቱ አንዳንድ ጽንፈኛ የደያስፖራ ፖለቲከኞች  ኢህአዴግ እንደተከፋፈለና  እንደተዳከመ  አድርገው ለማቅረብ ሲዳዳቸው  ተመልክተናል።

 

የአንድ ፓርቲ ጥንካሬ ከሚለካባቸው  ነገሮች መካከል  ቀዳሚው  ፓርቲው በጥቂት ግለሰቦች ስብዕና ላይ  ያለመመስረቱ  ነው። ኢህአዴግን በዚህ መለኪያ ስንመለከተው  ድርጅቱ  በቡድን አሰራር ላይ መሰረት ያደረገ  ፓርቲ በመሆኑ በግለሰቦች መሄድና መምጣት ሳቢያ በድርጅቱ ላይ የሚከሰተው ተጽዕኖ እጅግም  ነው።  ይህ ሲባል ግለሰቦች በድርጅቱ ውስጥ ምንም  ፋይዳ የላቸውም  ለማለት እንዳልሆነ ይታወቅልኝ።

 

አብዛኛዎቹ በትጥቅ ትግል ወቅት የነበሩ  የድርጅቱ መሪዎች ዕድሜአቸው በሃምሳዎቹና በስድሳዎቹ ዓመታት ውስጥ በመሆኑ ማረፍ ይገባቸዋል፡፡ ስልጣንን በቃኝ በማለት፣ ድርጅቱንም ሆነ አገርን ከኔ የተሻለ ሰው ይምራው በማለት ሥልጣንን ለተተኪዎች መልቀቅ መልካም አርአያነት  ነው፡፡ ይህ አይነት አካሄድ  በሌሎች  ፓርቲዎችም  መለመድ ያለበት ተግባር ነው።

 

አንድ ድርጅት ወይም ፓርቲ ታማኝና ጠንካራ ከሚያደርገው ባህሪያት ቀዳሚው አባላቱ ለግል ስብእናና ጥቅም ከመሯሯጥ ይልቅ ለድርጅቱ ወይም ለፓርቲው ዓላማና መርሆ ተገዥ መሆን መቻላቸው ነው፡፡ “ወርቅ በእሳት እንደሚፈተን” ሁሉ ኢህአዴግም ህዝባዊ ወገንተኝነቱን በረጅምና መራራ የትጥቅ ትግል ተፈትኖ እዚህ የደረሰ፣ በቁርጠኛ የህዝብ ልጆች የተገነባና ለብዙሃኑ ጥቅም የሚታገል ድርጅት መሆኑን በተግባር አስመስክሯል፡፡

 

ኢህአዴግ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ የደረሰው ከትጥቅ ትግሉ ጀምሮ በአመራር ላይ ያሉትን ግለሰቦች በተለያየ ምክንያት እየተካ ነው። የድርጅቱ ቀደምት መስራች የነበሩ ግለሰቦች ጥቂቱ እስካሁን ያሉ ቢሆንም ከፊሉ ግን  በትጥቅ ትግሉ ወቅት ውድ ህይወታቸው ሰውተዋል፡፡ አንዳንዶቹም ከትጥቅ ትግሉ ብኋላ  በተለያየ ምክንያት ድርጅቱን ተሰናብተዋል። ኢህአዴግ ግን በስኬት ጎዳና  በመጓዝ ላይ ነው። አሁን ላይ በርካታዎቹ  አንጋፋ  የድርጅቱ  አመራሮች  በአዲሱ ትውልድ በመተካት ላይ ናቸው።

 

አንጋፋ የኢህአዴግ  አመራሮች የአዲሲቷ ኢትዮጵያ አባቶች ናቸው።  የመፈቃቀድና የመቻቻል ፖለቲካን አስተምረዋል፤ ህዝቦች ባህላቸውን እንዲያውቁና በማንነታቸው እንዲኮሩ እንዲሁም በቋንቋቸው እንዲማሩና እንዲዳኙ የበኩላቸውን አስተዋጽዖ ተወጥተዋል፡፡ እነዚህ  አንጋፋ ታጋዮች  የዴሞክራሲ ባህል በአገራችን እንዲሰርጽ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡  ከዚህም ባሻገር አገራችን በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም ዓቀፍ ድርጃም  ተሰሚነት እንዲኖራት በማድረግ ብቃታቸውን አስመስክረዋል፡፡ ይህ እውነታ ማንም ጤነኛ አስተሳሰብ ያለውን ኢትዮጵያዊ  ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን በቅርብ የሚያውቃት ሊመሰክረው የሚችል ሃቅ ነው፡፡

 

በምጣኔ ሀብትና በማህበራዊው ዘርፍም ብንመለከት ከዜሮ በታች የነበረውን አመታዊ የአገሪቱን የኢኮኖሚ እድገት ለተከታታይ ለ15 ዓመታት በዓማካይ  ከ1ዐ በመቶ  በላይ በማሳደግ የአብዛኛውን ኢትዮጵያዊ የኑሮ ሁኔታ ወደ ተሻለ ደረጃ አሳድገውታል፡፡ ይህ አሌ የማይባል ሃቅ ነው፡፡ እየተመዘገበው ካለው የኢኮኖሚ ዕድገት ሁሉም በየደረጃው ፍትሃዊ  ተጠቃሚ  ለማድረግ ጥረት አድርገዋል።

 

እነዚህ አንጋፋ የድርጅትና የመንግስት መሪዎች የስልጣን ጥመኞች ቢሆኑ ኖሮ ነገ የሚተካቸውን ብቃት ያለውን አመራር በድርጅት ውስጥ ባላሰባሰቡ ነበር፡፡ አሁን ላይ ድርጅቱ በርካታ  ብቃት ያላቸውን ምሁራንን በውስጡ እንዲያቅፍ እነዚህ የአመራር ጓዶች ጠንክረው ሰርተዋል፡፡ ዛሬ ኢህአዴግ ከሰባት ሚሊዮን በላይ አባላትና በአስርት ሚሊዮን የሚቆጠር ደጋፊዎችን ማፍራት የቻለ በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም  ግዙፍ ፓርቲ ነው። ኢህአዴግ ራዕይ ያለው ድርጅት ነው፡፡

 

የድርጅቱን  ቀጣይነት አስተማማኝና የተሻለ እንዲሆን የአመራር መተካካት  አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ ድርጅቱ እጅግ በርካታ ምሁራንን  ያቀፈ  በመሆኑ  የግለሰቦች መሄድና መምጣት በድርጅቱ ህልውና  ላይ የሚያመጣው ተጽዕኖ ኢመንት ነው፡፡ ኢህአዴግ ትላንት ለህዝብና ለአገር ሰንቆ የተነሰውን የህዝብ አለኝታነቱን ለማጎልበት  እንዲችል  በቀጣይም ይህን   የአመራር ቅብብሎሹን አጠናክሮ  መቀጠል ይኖርበታል።  

Leave a Comment