አዲስ አበባ በሚገኙ ጤና ተቋማት የደም ዕጥረት ተከስቷል— ብሔራዊ ደም ባንክ አገልግሎት

በአዲስ አበባ በሚገኙ የህክምና ተቋማት ላጋጠመው የደም እጥረት ሕብረተሰቡ ደም በመለገስ ታካሚዎችን እንዲታደግ ጥሪ ቀረበ።

የብሔራዊ ደም ባንክ አገልግሎት ከጤና ጥበቃ ሚንስቴር ጋር በመተባበር ጉዳዩን አስመልክቶ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

የብሔራዊ ደንብ ባንክ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ብርሀኑ ሥዩም እንዳሉት ከሶስት ሳምንታት በፊት አንስቶ በአዲስ አበባ የሚገኙ የህክምና ተቋማት ያቀረቡትን የደምና የደም ተዋጽዖ ፍላጎት ማሟላት ባለመቻሉ ህሙማኑ ተገቢውን ህክምና እያገኙ አይደለም።

የደምና ደም ተዋጽዖ ለታካሚዎች የሚያስተላልፉ የእናቶችና ህጻናት፤ የካንሰር፣ የልብና የኩላሊት ንቅለ ተከላ ህክምና ማዕከላት መበራከትና የትራፊክ አደጋ አለመቀነስ የደም ፍላጎቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲጨመር ምክንያት መሆናቸው ተጠቅሷል።

በጾም ወቅት ከሚያጋጥመው የደም እጥረት በተጨማሪ በከተማዋ የደምና ደም ተዋጽዖ አቅርቦትን እየሰጠ የሚገኘው አንድ የደንብ ባንክ ብቻ መሆኑ በመዲናዋ አቅርቦቱና ፍላጎቱ እንዳይጣጣም ምክንያት መሆኑ ተጠቁሟል።

በአሁኑ ወቅት የተከሰተው እጥረት በዋናነት በትምህርት ቤቶች መዝጊያና መከፈቻ ወራት የሚከሰተው እጥረት አካል መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

ባሳለፍነው ክረምት ከ4 ሺህ 500 በላይ ዩኒት ደም መሰብሰቡን የተናገሩት ዶክተር ብርሃኑ በክረምት ወቅት ደም ለጋሾች ዳግም ለመለገስ ሶስት ወራት መጠበቅ ስላለባቸው ለተከሰተው እጥረት አንዱ ምክንያት መሆኑንም አንስተዋል።

በዋናው ማዕከል በቀን በአማካይ ከ60 እስከ 70 እንዲሁም በተንቀሳቃሽ ጣቢያዎች ከ100 እስከ 150 ዩኒት ደም መሰብሰብ ይቻል የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ግን መጠኑ ቀንሷል፡፡

በዚህም ጥቁር አንበሳ፣ዳግማዊ ምኒልክ፣የካቲት 12፣ ቅዱስ ጳውሎስና ሌሎች ሆስፒታሎች የጠየቁትን የደም ፍላጎት ማቅረብ አለመቻሉን ገልጸዋል።

በመሆኑም የደም እጦት ችግሩን ለመቅረፍና የዜጎችን ሕይወት ለመታደግ እድሜያቸው ከ18 እስከ 65 ዓመት የሆኑ በጎ ፈቃደኞች በማዕከሉና በተንቀሳቃሽ ደም መሰብሰቢያ ጣቢያዎች ደም እንዲለግሱ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

ብሔራዊ ደም ባንክ አገልግሎት አዲስ አበባን ጨምሮ በመላ አገሪቱ 25 የደም ባንኮች ያሉት ሲሆን የደም እጥረቱን ለመፍታት ተቋሙ የሰው ኃይሉን ከማሟላት ጀምሮ የደም ልገሳ ማዕከላትን በ10 ክፍለ ከተሞች ለማቋቋም ጥናት እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

በትምህርት ተቋማት የደም ጠብታ ክብባት እንዲቋቋሙ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር እየሰሩ መሆኑንም ዶክተር ብርሃኑ ተናግረዋል።

Leave a Comment