አመኔታችን እየጨመረ መጥቷል!

አመኔታችን እየጨመረ መጥቷል!

                                                          ታዬ ከበደ

ኢትዮጵያ በጤና፣ በትምህርት፣ በግብርና፣ በንፁህ የመጠጥ ውሃ እንዲሁም በመንገድ መሰረተ ልማቶች ያስገኘቻቸው ውጤቶች በዓለም ኢኮኖሚ ላይ በተጽዕኖ ፈጣሪነታቸው የሚታወቁት ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማትን ጨምሮ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ያላት አመኔታ እየጨመረ መጥቷል። ከመሰንበቻው የዓለም ባንክ እነዚህ የልማት አውታሮች ይበልጥ ጎልብተው ተደራሽ እንዲሆኑ የሰጠው ድጋፍና እርዳታ የአመኔታችን መገለጫ ነው ማለት ይቻላል። ይህን መነሻ ባድረግ ታዲያ ስኬቶቻችንን በመጠኑም ቢሆን መዳሰስ ይገባል።

የኢፌዴሪ መንግስት የሚከተለው ፖሊሲና ስትራቴጂ ግብርና መር ነው፡፡ ይህ ማለት ግብርና አርሶ አደሩን ማዕከል ያደረገ የልማት ስትራቴጂ ነው፡፡ መንግስት ይህ እንዲሆን የፈለገበት ዋነኛ ምክንያት አብዛኛውን የሀገራችን ህዝብ አርሶ አደር ስለሆነ ነው፡፡ በቁጥር ሲሰላም ከኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር ሰማንያ አምስት በመቶ በላይ በገጠር አካባቢ የሚኖርና በግብርና ዘርፍ የሚተዳደር በመሆኑ ነው፡፡

ግብርና ታዲያ የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ መተዳደሪያ ከሆነ የሀገሪቱ ዋነኛ የኢኮኖሚ መሰረት ነው ብሎ መደምደም ይቻላል፡፡ እናም መንግስት ይህንን ከግንዛቤ በማስገባት የሀገሪቱን የኢኮኖሚ አውታር ግብርናን ማዕከል ያደረገ ፖሊሲና ስትራቴጂ እንዲከተል የግድ ይለዋል፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን ለዘርፉ ልዩ ትኩረት መሰጠቱ ላለፉት ተከታታይ ዓመታት ትርጉም ያለው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማስመዝገብ ችሏል፡፡

እርግጥ ዘርፉ በኢኮኖሚና በማህበራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ካለው መጠነ ሰፊ ድርሻ ብሎም የሀገሪቱን ዕድገት ከማሳለጥ አኳያ ግብርናን የዘነጋ የልማት ፖሊሲና ስትራቴጂ የተሳሳተ መሆኑ እሙን ነው፡፡

በመሆኑም መንግስት የነደፈውን የግብርና መር የልማት ስትራቴጂ ተግባራዊ ለማድረግ በቅድሚያ በምግብ ራስን መቻልና ከዚያም ለኢንዱስትሪው ግብዓት የሚሆኑ የግብርና ምርቶችን በማስፋፋት በኢንዱስትሪውና በግብርናው መካከል ያለውን ትስስር ይበልጥ ለማጎልበት የሚያስችል አቅጣጫ እየተከተለ ነው፡፡

የግብርናው ዘርፍ ከሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ጋር በግብርና ሰብል ልማት እንዲሁም በእንስሳትና በተፈጥሮ ሃብት ልማትና አስተዳደር ብሎም በአደጋ መከላከልና በምግብ ዋስትና ዘርፎች ላይ ተመስርቶ በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡

በመሆኑም የሰብል ምርትን ለማሳደግ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥና የምግብ ኢንዱስትሪውን ዘርፍ መደገፍ በአምስት ዓመቱ የትራንስፎርሜሸን እና ዕድገት ዕቅድ ውስጥ ከተካተቱት ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ሲሆን፣ በዚህም ከፍተኛ ለውጦች ተገኝተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሰብል ምርትን ማሳደግ ቅድሚያ ተሰጥቶታል፡፡ በዚህም አርሶ አደሩ ምርቱን እና ምርታማነቱን ለማሳደግ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀም ማድረግ ተችሏል፡፡

እንደሚታወቀው ሁሉ ከግብርና አኳያ የዕድገቱ ምንጭ በአነስተኛ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ቤተሰቦች በሚካሄድ ልማት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ አሁን ባለን አቅም የምንጠቀምባቸውን ቴክኖሎጂዎች በአግባቡ ጥቅም ላይ በማዋልና የኤክስቴሽን ስርዓቱን በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ተግባራዊ ቢደረግ እንኳን እጅግ የላቀ የምርታማነትና የምርት መጠን መድረሳችን አይርም፡፡

ስለሆነም ከግብርና አኳያ በሰብል ልማትም ሆነ በእንስሳት ሃብት ልማት እንዲሁም የተፈጥሮ ሃብት ልማትና የመስኖ ሥራን ጨምሮ የማምረት አቅማቸው ከፍተኛ እንዳይሆኑ ያሉትን ችግሮች በመፍታት ልማቱን ለማሳዐጥ ታስቧል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን አሁን ባለው ቴክኖሎጂ የማምረት አቅማቸው ደረጃ ለተቃረቡ ሞዴሎች ተጨማሪ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የማዘጋጀት የማባዛትና የማሰራጨት ሥራ በተጨማሪነት እየተሰራ ነው፡፡

ከስትራቴጂክ የምግብ ሰብሎች ምርታማነት መጨመር በተጓዳኝ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ የማምረት አቅምን ለማሻሻል በሆርቲካልቸርና በእንስሳት ሃብት ልማት እንዲሁም ሌሎች የኢንዱስትሪ ግብዓቶችና የኤክስፖርት ምርቶች ላይ ለማተኮር ዕቅድ ተይዟል፡፡

እንደሚታወቀው ሁሉ የአንድ ሀገር ህዝብ በምግብ ሰብል ራሱን ችሏል የሚባለው በሀገሪቱ ከተመረተው አጠቃላይ ምርት የሚኖረው የነፍስ ወፍ ድርሻ ተሰልቶ ነው። ከዚህ አኳያ የሀገራችን ህዝብ የነፍስ ወከፍ የምግብ ሰብል ድርሻ ሲሰላ በወር ሶስት ኩንታል መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።

ይህም በምግብ ሰብል በአብዛኛው ራሳችንን መቻላችንን የሚያመላት ነው። በመሆኑም በምስራቅ አፍሪካ በተደጋጋሚ በሚከሰተው የድርቅና የረሃብ አደጋ ማንም ሰው እንዳይሞት ዋስትና ሆኗል ማለት ይቻላል።

የግብርና ልማት መዋቅራዊ ለውጥ ማምጣት ይችል ዘንድ በበሁለተኛው አምስት ዓመቱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ትኩረት ተሰጥቶት ስራው እየተከናወነ ነው። እንደሚታወቀው አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ለእርሻ ሊውል የሚችል ሰፊና ለም መሬት እንዲሁም የአርሶ አደሩ ጉልበት አለ።

በአገሪቱ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ታዲያ ይህ ግብርናው ውጭ ከፍተኛ እምቅ ሃብት ነው። ይህ ሃብት ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል እየፈጠረ ሲሆን፤ ገና ምንም ያልተነካ እምቅ ሃብት በመሆኑም ውጤት ሊያመጣ የሚችል ነው።

በመሰረተ ልማትና በማህበራዊ ዘርፎች በኩልም ውጤት ተገኝቷል። እነዚህ ውጤቶች የህዝቡን ተጠቃሚነት ከፍ ያደረጉ ናቸው። እንደሚታወቀው ሁሉ በመሰረተ ልማት ዙሪያ ግዙፍ ኢንቨስትመንት በመመደብ ሕዝቡ የመሠረተ -ልማት አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ እና የኢኮኖሚያችን ተወዳዳሪነት አሳድገን ለተጨማሪ ዕድገት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ርብርብ እየተደረገ ነው፡፡ ሆኖም ዘርፉ ከሚጠይቀው ግዙፍ ካፒታል አኳያ ችግሮች መስተዋላቸው አልቀረም፡፡ በተለይ በኤሌክትሪክ እና በቴሌኮም አገልግሎት የተስተዋሉት ችግሮች ሕዝቡን ያማረሩ ነበሩ፡፡

በትራንስፖርት ዘርፍም የፋይናንስና የኘሮጀክት ማኔጅመንት አቅማችን ውሱን በመሆኑ ምክንያት ሰፋፊ ሥራዎች በማከናወን ላይ እያለንም ቢሆን የሕዝቡን ሰፊ ፍላጐት ሙሉ በሙሉ ማርካት አልቻልንም፡፡ ስለሆነም በቀጣይም ቀደም ሲል የለየናቸው ሦስት ዋና ዋና ማነቆዎች ለማቃለል ጥረት እየተደረገ ነው፡፡

የመሠረተ-ልማት ኘሮግራሞቻችን የሚፈልጉት ግዙፍ የፋይናንስና የውጪ ምንዛሪ አቅም ለማሟላት ቁጠባ፣ ኤክስፖርት፣ የአገር ውስጥ የግንባታና የማምረት አቅም ማሳደግ ይኖርብናል፡፡ ሌላው የኘሮጀክት ማስፈፀምና ማስተዳደር አቅም ማነስ ጋር ተያይዞ የቅድመ ግንባታ ዕቅድና ዝግጅት፣ ጥናትና ዲዛይን፣ ግዢና ኮንትራት አስተዳደር፣ ክትትልና ቁጥጥር፣ የግንባታና ማማከር አቅም፣ ወዘተ… ያጠቃልላል፡፡

ታዲያ በዚህ ዙሪያ ያለን አቅም እያደገ የመጣ ቢሆንም በዛው ልክ የምንገነባቸው የመሠረተ ልማት ኘሮጀክቶች ግዙፍና ውስብስብ እየሆኑ የመጡ በመሆናቸው እስካሁን የፈጠርነው አቅም ክፍተቶች ቢታዩባቸውም ስኬቶቹ ግን አመርቂዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ስኬቶቻችን በዓለም የፋይናንስ ተቋማት ዘንድ አመኔታን አትርፈውልናል፡፡ በራሳቸው መገምገሚያ ድጋፍ የሚያደርጉልን ለዚሁ ነው፡፡

 

Leave a Comment