ታላቁ የህዳሴ ግድብ እና  ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታው!

ታላቁ የህዳሴ ግድብ እና  ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታው!

ወንድያራድ ኃብተየስ

የኢፌዴሪ መንግስት  አገሪቱን ከድህነት ለማውጣት ከሚያከናውናቸው አያሌ ተግባራቶች መካከል   የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ አንዱ ነው። አንዳንዶች ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከአድዋ ጦርነት በመቀጠል በኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች  አንድነትና ትብብር  የታየበት ሲሉ ይገልጹታል። በአድዋ ጦርነት ወቅት አባቶቻችን ልዩነታቸውን ወደ ጎን ብለው አንድነታቸውን አጠናክረው  የውጭ ወራሪን በመመከት ጊዜ የማይሽረው ታሪክ ሰርተዋል። የእኛ ትውልድ ደግሞ ያንን ወርቃማ የአንድነት መንፈስ በመላበስ ታሪክን  በልማት ለመድገም  በመስራት ላይ ነው። የሁለቱም ትውልዶች ግብሩ ይለያይ እንጂ ውጤቱ ተመሳሳይ ነው።  ኢትዮጵያን ታላቅነት ማረጋገጥ ነው።  ልዩነቱ  አባቶቻችን  ደም ማፍሰስ አጥንት መከስከስ  ሲጠበቅባቸው  የእኛ ትውልድ ደግሞ   ላቡን ማንጠፍጠፍ  ነው  የሚጠበቅበት። የህዳሴ ግድብ በአገራችን ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የሁሉንም ህዝቦች ቀልብ መግዛት የቻለ፣ ሁሉን በአንድ ያሰባሰበና ያስተባበረ  ፕሮጀክት ነው።  ለግድቡ ግንባታ ከጫፍ እስከጫፍ የዘለቀ ሰፊ ህዝባዊ ንቅናቄ ተፈጥሯል።

አገራችን ከድህነት ለመውጣት ታላላቅ ልማቶችን ማካሄድ የግድ ይላታል። በተለይ የአገሪቱ  የሃይል አቅርቦት በየዓመቱ በ25 በመቶ አካባቢ እያደገ በመሆኑ  ትላልቅ የሃይል ማመንጫዎችን መገንባት  ካልቻለች  ዕድገቷ ቀጣይነት አይኖረውም። መንግስት ይህን በመረዳት ግዙፍ የሆኑ የሃይለ ማመንጫዎችን በመገንባት ላይ ነው። ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ትውልድ ተሻጋሪ የልማት ቱርፋት ነው።  ይህ ትውልድ  እድለኛ ነው እንዲህ  ያለ ዘመን ተሻጋሪ  ሃብት  መገንባት  በመቻሉ።  አዎ ይህ ትውልድ  እንደታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ያለ ለመጪው ትውልድ የሚተላለፍ ፕሮጀክት ላይ አሻራውን  ማሳረፍ የሚችልበት   አጋጣሚ ተፈጥሮለታል።  በዛሬው  አጭር መጣጥፌ ታላቁ የኢትዮጵያ  የህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ህዝቦች ከሚያስገኘው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባሻገር  ሌሎች   ጎላ ጎላ የሚሉትን ፋይዳዎችን ለማንሳት ሞክራለሁ።  

በመጀመሪያ ደረጃ ይህ ግድብ በኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መካከል አገራዊ መግባባትን እንዲጎለብት አድርጓል። የህዳሴው ግድብ  የሁሉን ድጋፍ ያተረፈ ፕሮጀክት ነው። ይህ ፕሮጀክት  ሁሉም አገር ወዳድ ዜጋ የፖለቲካ አመለካከት፣ የሃይማኖት ልዩነት፣ የመኖሪያ ቦታ (ከአገር ውስጥም ይሁን ከውጭ) ርቀት ሳይገደበው፣ የብሄር፣ የዕድሜ ወይም የጾታ  ልዩነት ሳይታይበት  ሁሉም  በአንድነት ድጋፉን ችሮታል። አንድ አባት ሲናገሩ እንዳደመጥኩት ለዚህ ግድብ ድጋፍ ያላደረጉት ኢትዮጵያዊያን   “በማህጸን ያሉ ህጻናት እና በመቃብር  ያሉ ሙታኖች ብቻ ናቸው”  ብለው ነበር።  ይህ ባለብዙ ቢሊዮን ዶላር ወጪን የሚጠይቅ ፕሮጀክት  በአሁኑ  ሰዓት ግድቡን ከ60 በመቶ በላይ ማድረስ ተችሏል። ይህን ግድብ በተመለከተ ሁሉም አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ አንድ አቋም ማራመድ የቻለው መንግስት ህብረተሰቡን በትክክልኛ መንገድ መምራት በመቻሉ  ነው። በዚህ ግድብ ሳቢያ ጽንፈኛው የዳያስፖራ ፖለቲከኞች ከህብረተሰቡ የተነጠሉበት፤ የጸረ-ህዝብ አቋማቸው በግልጽ የታየበት ነው።

ሌላው የዚህ ፕሮጀክት ጠቀሜታ በኢትዮጵያዊያን ውስጥ የይቻላል መንፈስ እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል። ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ያለምንም የውጭ አገራት ብድር እና ዕርዳታ የሚከናወን  አገራዊ  ፕሮጀክት ነው።  ይህ ፕሮጀክት ከ4 ነጥብ 7 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ የሚጠይቅና በምንም ተዓምር በታዳጊ አገር አቅም የማይታሰብ ፕሮጀክት ነው። የላንጣዎቻችን እጀ ረጃጅሞች በመሆናቸው  አባይን ለመገንባት ዕርዳታም ሆነ ብድር ማግኘት የማይሞከር  መሆኑ በኢትዮጵያ ህዝቦች መካከል ቁጭት እንዲፈጠር አድርጓል። በመሆኑም ኢትዮጵያዊያን በራሳችን ወጪ ይህን ግዙፍ ፕሮጀክት ለመገንባት ተነስተን፤ ስኬታማ መሆን ችለናል።  መተባበር  ከቻልን አንድ የህዳሴ ግድብ ሳይሆን አስር ፕሮጀክቶችን መገንባት እንደምችል በተግባር አረጋግጠናል። ይህ ፕሮጀክት በህብረተሰቡ ውስጥ የእንችላለን ስሜት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል የተባለውም ለዚህ ነው።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሌላው ጠቀሜታ ደግሞ በህዝቦች መካከል የቁጠባ ባህልን እንዲዳብር እድል ፈጥሯል። ቁጠባ ለአንድ አገር ኢኮኖሚ ማደግ አንዱ አመላካች ሲሆን ህዝቦች የመቆጠብ አቅማቸው እያደገ በመጣ ቁጥር  የአገር ውስጥ ኢንቨስትመንት ይስፋፋል። በዚህም የስራ ዕድል ይፈጠራል። ግድቡ ሲጀመር አካባቢ የአገራችን የቁጠባ ባህል 5 በመቶ ብቻ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ አገራዊ ቁጠባችን ወደ 22 በመቶ አካባቢ ደርሷል። እዚህ ላይ የህዳሴው ግድብ ቦንድ ሽያጭ ትልቅ አስተዋጽዖ አበርክቷል። መንግስትም  ለቦንድ 5 ነጥብ 5 ወለድ እንዲከፈል ማድረጉ  ህብረተሰቡ በቦንድ ሳቢያ ቁጠባ እንዲለምድ  አግዞታል። የመጀመሪያው የቦንድ ሽያጭ አምስት ዓመት የሚሞላው በመጪው ዓመት አጋማሽ በመሆኑ ህብረተሰቡ  ገንዘቡን መውሰድ እንደሚችል መንግስት አስታውቋል።

የዚህ ፕሮጀክት ሌላው ጥቅም የስራ ዕድል ፈጠራ ነው።  ታላቁ የህዳሴ ግድባችን  ለበርካታ  ዜጎቻችን የስራ ዕድል ይዞ የመጣ ፕሮጀክት ነው። ከከፍተኛ ባለሙያዎች ጀምሮ እስከ ቀን ሰራተኛ ድረስ በግንባታው ስራ በመሳተፍ በአጠቃላይ ከ11ሺ በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያዊያኖች እንዲሁም ከ300 በላይ ለሚሆኑ የውጭ ዜጎች  የስራ ዕድል  ፈጥሯል። በቀጥታ የስራ ዕድል ከተፈጠረላቸው ዜጎች ባሻገር  እጅግ በርካታ ዜጎች ደግሞ ለእነዚህ ሰራተኞች የተለያዩ   አገልግሎቶች በማቅረብ፤  ለአብነት  በሸቀጣሸቀጥ ፣ ምግብ፣ ትራንስፖርት  በማቅረብ ተጠቃሚ ሆነዋል።  

በታላቁ ግድባችን ሳቢያ  በበርካታ አካባቢዎች ህብረተሰቡን ለአካባቢ ጥበቃ ስራ እንዲነሳሳ ምክንያት ሆኗል። ህብረተሰቡ የግድቡ ዕድሜ እንዲጨምር  በየአካባቢው  የአካባቢ ጥበቃ ስራዎችን በተለይ በችግኝ ተከላና አፈር ጥበቃ ስራዎች በከፍተኛ ሁኔታ እየተረባረበ ይገኛል። አርሶና አርብቶ አደሩ እንዲሁም  የከተማ ነዋሪዎች በ2008 ዓ. ም ብቻ  ያከናወኑት  የአካባቢ ጥበቃ ስራ በገንዘብ ሲሰላ ከ47 ቢሊዮን ብር በላይ ሊተመን የሚችል ነው። ይህም ለተያያዝነው አረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ሰፊ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል። የአገራችንም ስነ ምህዳር በከፍተኛ ሁኔታ መሻሻል በማሳየት ላይ ነው።

ታላቁ የህዳሴ  ግድባችን  ለቴክኖሎጂም ሽግግር አግዞናል።  ከላይ ለማንሳት እንደሞከርኩት ከ300 በላይ ከተለያየ የዓለም ክፍሎች የተሰባሰቡ ባለሙያዎች በግድቡ ግንባታና ማማከር ስራ ላይ በመሳተፍ  ላይ ናቸው። በመሆኑም  ዜጎቻችን  በተግባር የተደገፈ ሰፊ የክህሎት እና ቴክኖሎጂ ልምድ መቅሰም ዕድል ተፈጥሮላቸዋል። በዚህም ሳቢያ የአገር ልጆች  የግድቡን ዲዛየን በማሻሻል እና የተርባይኖች አቅም  በማሳደግ  አሀን ላይ  የግድቡ ኃይል የማመንጨት አቅም  ከ5250 ወደ 6450 ማሳደግ ችለዋል። ይህ ነው ክህሎት ማሳደግ ማለት።  የቴክኖሎጂ ሽግግርና የክህሎት ማሳደግ ከአገራዊ ፋይዳው  ባሻገር በርካታ ዜጎቻችን ለቀጣይ ገቢያቸው ማደግ ምክንያት  እንደሚሆን በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል።  

ይህ ግድብ ከሁሉም ፕሮጀክቶቻችን በበርካታ ነገሩ  የተለየ ነው። ምክንያቱም  የሁሉም ኢትዮጵያዊ  አሻራ  ያረፈበት በመሆኑ  ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊጎበኘ  የሚችል  ነው።  በመሆኑም በቀጣይ  የአገር ውስጥ  ቱሪዝምን  የሚያበረታታ ነው።  እስካሁን ባለው ሁኔታ እንኳን  ከ250ሺ በላይ ዜጎች ጎብኝተውታል። ሰራተኞች በመስሪያ ቤታቸው ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች በቡድን በመሆን በራሳቸው ወጪ ግድቡን

ሌላው የግድቡ ጠቀሜታ  ፍተሃዊ የሃብት ክፍፍል በተፋሰሱ አገራት መካከል እንዲነግስ በማድረጉ ከአገራት ጋር የመተማመንና የመተባበር ዲፕሎማሲን እንዲፈጠር  አስገድዷል።  የግድቡ መጀመር ለእኛ ኢትዮጵያን ፍትሃዊ አመለካከታችንን ለዓለም ለማሳወቅ ጥሩ ጋጣሚን ፈጥሮልናል። ኢትዮጵያ ምን ያህል ፍትሃዊ እንደሆነች የዓለም ህዝቦች የተረዱበት ሁኔታ ተፈጥሯል። የአገራችንንም  የመደራደር አቅም አሳድጓል። የአገራችንን  ገጽታም እጅጉን ቀይሮታል። የታችኛው ተፋሰስ አገራት በተለይ ግብጻዊያንን ለውይይት እና ምክክር በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲቀመጡ አድርጓቸዋል።

ታላቁ የህዳሴ ግድባችን  የአገራችንን  የኤሌክትሪክ አቅርቦት  ከ70 በመቶ በላይ ከማሳደጉም ባሻገር  አገራችን  ከፍተኛ  የአሳ ምርት እንድታገኝ  ዕድል ይፈጥራል።  ግድቡ ሲጠናቀቅ 74 ቢሊዮን ሜትር ኩዩብ ውኃ የሚይዝ ከ 1680 ኪሎሜትር ስኩዌር በላይ ስፋት  ስለሚኖረው  በዚህ  ሰፊ ሰው ሰራሽ ሀይቅ  ከፍተኛ የሆነ  የአሳ ሃብት ማፍራት የሚያስችል ይሆናል።  ጥናቶች እንዳመላከቱት በዓይነታቸው ለየት ያሉ ከ 9 በላይ የኣሳ ዝርዎችን ለማርባት  በጣም ምቹ እንደሚሆን እና በዓመት ከ10ሺ ቶን በላይ ኣሳ የማምረት  አቅም ይኖረዋል።

በአጠቃላይ  ታላቁ የኢትዮጵ ህዳሴ ግድብ በአገሪቱ እየጎለበተ ላለው ጠንካራ ህብረ-ብሄራዊ አንድነት አንድ ማሳያ ከመሆኑም ባሻገር  ለአገራችን  የገጽታ ግንባታ እጅግ ከፍተኛ  አስተዋጽዖ  ያበረክቷል። ይህ ፕሮጀክት በአገራችን ህዝቦች መካከል የይቻላል መንፈስ እንዲፈጠር ሲያደርግ  ለሌሎች  ታዳጊ አገራት ደግሞ በተፈጥሮ ሃብታቸው እንዴት መጠቀም እንደሚችሉ መንገድን አመላክቷል።  ታላቁ  የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድባችን  የህዝባችንንና መንግስታችንን  ፍትሃዊነት ለዓለም ያሳወቅንበት አንዱ  ነገር  ነው።  የተፋሰሱ አገራት የጋራ ሃብታቸውን  በትብብር እና በመደጋገፍ  ከመጠቀም ውጪ ሌላ  አማራጭ እንደማይኖራቸው የኢትዮጵያ ህዝብና  መንግስት  ተግባር አሳይተዋል።  

 

Leave a Comment