ተሃድሶውና የመልካም አስዳደር ችግሮች አፈታቱ

ተሃድሶውና የመልካም አስዳደር ችግሮች አፈታቱ

ዳዊት ምትኩ

ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግና መንግስት በአገራችን የተፈጠረውን የመልካም አስተዳደር ችግር ለመቅረፍ እርምጃዎችን እየወሰዱ ናቸው። እስካሁን ድረስ በገዥው ፓርቲ አባል ድርጅቶች ውስጥ የመልካም አስተዳደር ህፀፆችን ለመቅረፍ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል። በተለያዩ ወቅቶች በኦህዴድ፣ በብአዴንና በደኢህዴንና በህወሓት እንዲሁም በአጋር ድርጅቶችና በሚመሯቸው ክልላዊ መንግስታት ውስጥ የተከናወኑ የጥልቅ ተሃድሶ ስራዎች ተጠቃሽ ናቸው። በእነዚህ የጥልቅ ተሃድሶ ስራዎች ከህዝበቡ ጋር በመሆን ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ እርምጃዎች ተወስደዋል። አጥጋቢ ውጤቶችም ተገኝተዋል።

መንግስት በጥልቅ ተሃድሶ ሂደት ውስጥ ራሱንና አሰራሮቹን ሲፈትሽ ዋነኛው ጉዳይ ስር ነቀል ለውጥን ማዕከል ያደረገ መሆኑ ግልፅ ነው። አንዳንድ ወገኖች እንደሚሉት ለይስሙላ የሚደረግ አሊያም ያለበትን ችግር ለመሸፋፈን አይደለም። በእኔ እምነት መንግስት ከህዝቡ ጋር እያደረገያለው ኪራይ ሰብሳቢነትን የመዋጋት ተግባር የዚህ አባባሌ ማረጋገጫ ነው።

ጥልቅ ተሃድሶው መንግስትንና ህዝቡን በቀጥታ ፊት ለፊት የሚያገናኝ እንዲሁም ያሉትን ችግሮች ከዋነኛ ተዋናዩ ማግኘት የሚያስችል ነው። ችግሮቹ ሁሉ በጥልቅ ተሃድሶው በግልፅ ታይተዋል። ታዲያ የችግሮቹን ትክክለኛ መንስኤዎች በተገቢው መንገድ ለማወቅ፣ አውቆም ለመረዳትና የህዝቡን ፍላጎት ለማርካት አሁንም ጥልቅ ተሃድሶው አሁንም ቢሆን ወደ ህብተሰቡ ውስጥ ተጠናክሮ መዝለቅ የሚኖርበት ይመስለኛል።

የኢፌዴሪ ህገ መንግስት የመንግስት አሰራር ለህዝብ ግልፅ መሆን እንዳለበት፣ ማንኛውም የመንግስት ባለስልጣን ለህዝብ ተጠያቂ እንደሚሆን፣ ህዝቡም በማንኛውም ተወካዩ ላይ አመኔታ ሲያጣ በማንኛውም ወቅት ከቦታው የማንሳት መብት እንዳለው ያስቀምጣል። መነሻው የህዝብ የስልጣን ሉዓላዊነት መከበር ነው።

ህዝቡ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤት እንደመሆኑ መጠን ሿሚና ሻሪ የሚሆነው እርሱ ነው። እዚህ ሀገር ውስጥ ስልጣን የሚመነጨው ከህዝብ እንጂ ከማንም አይደለም። ተሿሚው በህዝብ በጎ ፈቃድ ወንበሩ ላይ የሚቀመጥና የሚነሳ መሆኑን ግንዛቤ መያዝ ይገባል። ተሿሚው በራሱ ፈቃድ አይደለም ስልጣን ላይ የተቀመጠው። ጥሩ ሲሰራ ጥንካሬውን እንዲያጎለብት፣ ሲደክምም ድክመቱን የሚያሳየውና ከዚያ በላይም በገሃድ በምዝበራ ውስጥ ገብቶ ሲገኝ ካለበት ቦታ የሚያነሳው ህዝብ ነው። እዚህ ሀገር ውስጥ ፈላጭና ቆራጩ ህዝብ እንጂ ባለስልጣን አይደለም። ሊሆንም አይችልም። እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ የኢትዮጵያ ህዝቦች በከፈሉት መስዋዕትነት ባለፉት ስርዓቶች እንዲቀር ያደረጉት ነው።

እናም በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ ህዝብ ያላመነበትና ያልመከረበት ነገር አይከናወንም። ሰሞነኛው የፀረ ሙስናው ጉዳይ በጥልቅ ተሃድሶው ጅማሮ ወቅት መንግስት ኪራይ ሰብሳቢነትን ከህዝቡ ጋር በመሆን እንደሚዋጋ የገባው ቃል አንዱ ክፍል ነው ማለት ይቻላል። ህዝቡም ቢሆን ይህ የመንግስትን ቃል በተግባር ተተርጉሞ ማየት ይፈልግ ነበር።

የኪራይ ሰብሳቢነትን የፖለቲካል ኢኮኖሚ በአንድ ጊዜ መናድ ቀላል ላይሆን ይችላል። ሆኖም ኪራይ ሰብሳቢነት የበላይነቱን እንዳይዝ ሁሌም ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። ኪራይ ሰብሳቢነት በገነነበት ኢኮኖሚ ውስጥ ልማታዊ የፖለቲካል ኢኮኖሚ መንገድን መገንባት አይቻልም። ኪራይ ሰብሳቢነት ማነቆ ይሆናል። ተግባሩን ማስወገድ የሚገባው ለአዚሁ ነው።

ጥልቅ ተሃድሶው እስካሁን በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ውጤት አምጥቷል። በተለይም የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት በኩል ተገቢ ሊባል የሚያስችል ተግባር ተፈፅሟል ማለት ይቻላል። በጥልቅ ተሃድሶው ድርጅቶቹ ወደ ውጭ ሳይሆን ወደ ውስጣቸው በመመልከት ችግሮቻቸውን ፈትተዋል። በተለይ በቅርቡ የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ደረጃ ያደረገው ግምገማ የዚህ አባባል ማሳያ ነው።

ህወሓት ለ35 ቀናት ያካሄደውን ገምገማ ሲፈፅም ባወጣው የአቋም መግለጫ ላይ እንዳስታወቀው፤ ድርጅቱ ህዝባዊ ወገንተኝነቱ አስተማማኝ የሆነ፣ ፈተናዎች በገጠሙት ቁጥር ራሱን በሚገባ እየፈተሸና ወቅቱ የሚጠብቀውን፤ ማንኛውንም የእርምት እርምጃ እየወሰደ ጥንካሬዎቹን የሚያጎለብት ድክመቶቹ ያለምህረት በማስወገድ በመስዋእትነት የደመቀ ታሪክ መስራት የቻለ ኣመራር ባለቤት መሆኑን ገልጿል።

ድርጅቱ ወደ ግምገማ ሲገባ አሁን በስራ ላይ ያለውና ተተኪው አመራር በጋራ ትኩረት ሰጥቶ ያየው ጉዳይ ከገባበት የአመራር አዙሪት ውስጥ ለመውጣት በተለመደው መንገድ መሄድ በፍፁም የማይዋጣ መሆኑን ተገንዝቧል። በመሆኑም ከተለመደው ግምገማ ለመውጣት ያስችላል ተብሎ የታመነበትና ስፋትና ጥልቀት ያለው ክርክር የጋበዘ የድርጅቱን አጠቃላይ ሁኔታና የአመራሩን ድክመት በሚገባ የፈተሻ ሰነድ ለአመራሩ ቀርቦ ሰፊ ውይይትና ክርክር አድርጓል።

የድርጅቱ መግለጫ ወጣቶች ፣ ምሁራን፣ ሴቶችና ሌሎችም የሞያ የማሕበራትና መሰል ኣደረጃጀቶች የለውጥ ባለቤት ሆነው የሚውጡበትን ዕድል በማምከን ድርጅቱን በቀጣይነት የሚመራ ብቁ ሃይል እንዳይፈጠር እንቅፋት የሆነ አመራር እንደነበር መረዳቱንና ይህም ህዝቡ በድርጅቱ ላይ የነበረውን እምነት እንዲሸረሸርም ትልቅ አስተዋፅኦ ማድረጉን አልሸሸገም።

በአመራሩ ዘንድ የታየው ድክመት በህዝብ ዘንድ ካስከተለው ከፍተኛ የአመኔታ መሸርሸር ችግር በተጨማሪ በከተማም በገጠርም የተጀመሩ ትራንስፎርሜሽንና ዘላቂ ልማትን የማረጋገጥ ሰራዎችን ለአደጋ ማጋለጡን ገልጿል።

በእኔ እምነት ይህ የድርጅቱ ራስን በጥልቀት ወደ ውስጥ የመመልከት ሂደት እጅግ አስመስጋኝ ነው። ትልቅ ትምህርትን የሰጠ ነው ብዬም አስባለሁ። ምክንያቱም ራስን ወደ ውስጥ መመልከት ለአንድ የፖለቲካ ድርጅት የጥንካሬ ምንጩ፣ ችግሮችን በፍጥነት ለመፍታት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይና ሌሎችንም ለመደገፍ አስቀድሞ ከችግር መውጣት ስለሚያስፈልገው ነው። እናም ድርጅቱ ችግሮችን ወደ ውጭ ሳያመካኝ በቅድሚያ ራሴን መፈተሽ አለብኝ ብሎ መነሳቱ ተገቢና ትክክል መስሎ ይሰማኛል።

ይህ ሁኔታም ጥልቅ ተሃድሶው በኢህአዴግና በአባል ድርጅቶቹ ውሰጥ ስር እየሰደደ መምጣቱን የሚያሳይ ነው። ከዚህ አጠቃላይ ሁኔታም በአሁኑ ወቅት በሁሉም ድርጅቶችና የመንገሰት መዋቅሮች የሚካሄደው ጥልቅ ተሃድሶ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የሚፈቱ ናቸው። እየተካሄደ ያለው የተሃድሶ ሂደት የመንግስት መዋቅሮችን የህዝቡን እርካታ በሚፈጥሩ መንገድ እየፈተሸ ነው። ይህ ሁኔታም ከዚህ ቀደም በነበሩ የተሃድሶ መንገዶች የተከናወኑ ተግባራትን የሚያጠናክርና ይበልጥ የሚያሰርፅ ነው። ታዲያ ገዥው ፓርቲና መንግስት መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ለያዙት ቁርጠኛ አቋም ሁሉም ድጋፉን ሊሰጥ ይገባል።

 

Leave a Comment