በዴሞክራሲያዊ ውይይት እውነት እንጂ እሳት አይነሳም

በዴሞክራሲያዊ ውይይት እውነት እንጂ እሳት አይነሳም

አሜን ተፈሪ

በዴሞክራሲያዊ ስርዓት የሐሳብ ልዩነት ህይወት እንጂ ሞት አይደለም፡፡ እርግጥ የሐሳብ ልዩነቶች በርዕዮተ ዓለም ጎራ ከወዲያ እና ከወዲህ ለመቆም እና ለመወጋገዝ ሲዳርግ አይተናል፡፡ ደምም ሲያፋስስ ተመልክተናል፡፡ የሐሳብ ልዩነት፤ የልዩነት ጎራ ፈጥሮ፤ የርዕዮተ ዓለም ባንዲራ አስይዞ፤ ይህ ‹‹ወገን›› – ያኛው ‹‹ጠላት›› ነው በሚል አስፈርጆ፤ በባላንጣነት ሲያሰላልፈን ከታሪክም ሆነ ከህይወት ልምድ መረዳት እንችላለን፡፡

የሐሳብ ልዩነቶች ለግጭት ምክንያት ተደርገው ሲያዙ ማየታችን የማይካድ ነው፡፡ ሆኖም የሐሳብ ልዩነት፤ የግድ – ሁልጊዜ የግጭት መንስዔ አይሆንም፡፡ የሐሳብ ልዩነት፤ በአንድ መድረክ ተቀምጦ ከመወያየት አያግድም፡፡ ሰዎች የተለየ ሐሳብ ይጠሉ ይሆናል እንጂ ሐሳቦች ሰዎችን አይጠሉም፡፡ ሐሳቦች ሐሳብን አይጠሉም፡፡ እንዲያውም ሐሳቦች ጥራት እና ብቃት የሚያገኙት፤ የህግ እና የቋሚ እውነት ማዕረግ የሚያገኙት በተቃራኒ ሐሳብ ድጋፍ ነው፡፡ የሐሳብ ከተማ ውይይት ነው፡፡

ሆኖም ይህ የውይይት ከተማ በጽንፈኛው ሚዲያ እና በፌስቡክ ፖለቲካ ታውኳል፡፡ ጽንፈኛው ሚዲያ የጥቃት ዒላማውን የፌዴራል ስርዓታችን ላይ አድርጎ ቀጥሏል፡፡ ታዲያ ይህ ጥቃት ውጤታማ እንዳይሆን የሚያደርገው ራሱ ፌዴራላዊው ስርዓታችን ነው፡፡ ይህ ስርዓት የስኬቶቻችን ሁሉ ምንጭ ነው፡፡ በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ፣ በኢኮኖሚ፣ በማበራዊ፣ በመሰረተ ልማት፣ እንደሁም በውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ መስኮች በሀገራችን  የተመዘገቡት ስኬቶች ሁሉ የፌዴራላዊው ሥርዓታችን ውጤቶች ናቸው፡፡

የፌዴራል ስርአቱ በፖለቲካ፣ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ስርነቀል ለውጦችን ያመጣ ነው፡፡ የሐገራችን ጭቁን ህዝቦች የዘመናት ጥያቄዎች የነበሩት ራስን በራስ የማስተዳደር፣ የፖለቲካ ስልጣን ባለቤትነት፣ የመናገር፣ የመፃፍ፣ ሃሳብን በተለያዩ መንገዶች የመግለፅ እንዲሁም የመደራጀትና የመዘዋወር ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ተግባራዊ ለማድረግ ያስቻለ ስርዓት ነው፡፡

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ-መንግስት የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦችን ጥያቄዎች የመለሰና የወደፊት የአብሮነት ቃል ኪዳናቸውን የደነገገ ሰነድ ነው፡፡ ፌዴራል ሥርዓቱ የተመሰረተው የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ለዘመናት ባካሄዱት ትግልና በከፈሉት ከፍተኛ መስዋዕትነት ነው፡፡

ሐገራችንንና ሕዝቦቿን ለጭቆና የዳረጓቸው ዘውዳዊና ወታደራዊ አገዛዞች፤ በህዝቦች የተባበረ ክንድ ተወግደው፤የኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ አንድነታቸውን፣ መፈቃቀዳቸውንና መቻቻላቸውን አጠናክረው በመቀጠል አዲሲቷን ኢትዮጵያ መገንባት ቀጥለዋል፡፡ ሆኖም ይህ ስርዓት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ዴሞክራሲያዊ ውይይት እጅግ እሰፈላጊ ነው፡፡

ታዲያ በዴሞክራሲያዊ ስርዓት የሚደረግ ውይይት በነጻ መንፈስ የሚመራ እና ድሁር ከሚያደርግ የነገር ጓዝ የጸዳ ውይይት መሆን ይኖርበታል፡፡ ውይይቱም ችግርን በመፍታት ፍላጎት የሚመሩ የተጻራሪ ሐሳቦች ጉባዔ መሆን ይኖርበታል፡፡ ነገሩ እንዲህ ከሆነ፤ ከልዩነቶች እውነት እንጂ እሣት አይነሳም፡፡  

እውነተኛ ውይይት እንደ ጽጌረዳ አበባ ነው፡፡ የጽጌረዳ አበባ እሾህ እና በቀለም የተዋቡ ቅጠሎች ያሉት ነው፡፡ አበባው ጽጌረዳ ከሆነ እሾህ እና ቅጠል ይኖረዋል፡፡ ውብ ቅጠሎች ወይም እሾህ ብቻ የምናይ ከሆነ፤ ጽጌረዳ አበባ እያየን አይደለም፡፡ እውነት ተሸፍጧል፡፡ እውነቱ፤ ውብ ቅጠሎች እና እሾህም ያለበት ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ውይይት እንደ ጽጌረዳ አበባ ነው፡፡

ተወያዮቹ እሾሁን የሚያነሱት ስሜት ለመጉዳት አይደለም፡፡ አበባውን ሲጠቅሱ ለመሸንገል አይሆንም፡፡ በሌላ አገላለጽ፤ እሾሁ በመጎዳዳት ስሌት አይነሳም፡፡ ባለ ቀለሙ ውብ ቅጠልም በአድርባይነት መንፈስ አይሽሞነሞንም፡፡ አስቀያሚ እውነቶችን በውብ ቅጠሎች ጉዝጓዝ ለመሸፈን የሚደረግ ሙከራ አይኖርም፡፡ በቃ፤ ጽጌረዳ እንዲህ ነች፡፡ እሾህ እና ውብ ቅጠሎች አሏት፡፡

የአንድ ተናጋሪ ሰው መልዕክት፤ በሚናገረው ነገር ብቻ አይወሰንም፡፡ መልዕክቱ በአነጋገር ዘይቤውም ይወሰናል፡፡ ተወያዮቹ ከሚናገሩት ነገር እኩል፤ ለአነጋገራቸው (ለአቀራረባቸው) ዋጋ መስጠት ይኖርባቸዋል፡፡ ውይይት ትክክለኛ መልኩን ሲይዝ፤ ሁሉም ተናጋሪዎች በየራሳቸው የአመለካከት፣ የትንታኔ ወይም የእይታ ዛቢያ ይሽከረከራሉ፡፡ ግን የሐሳባቸው ዑደት በአንድ ፀሐይ ዙሪያ ነው፡፡ በራሳቸው የሐሳብ ዛቢያ እየተሸከረከሩ፤ ዑደታቸው ሐገራችን የገጠማትን ችግር በመፍታት ዓላማ ዙሪያ የሚመላለስ ይሆናል፡፡ ታዲያ በአንድ ጸሐይ ዙሪያ የሚሽከረከሩ የተለያዩ (ተቃራኒ) ሐሳቦች፤ የተለያዩ ቢሆኑ እንኳን ህቡር እና ስሙር ይሆናሉ፡፡

በተለይ ተናጋሪዎቹ፤ የሚናገሩትን የሚያውቁ ሰዎች ሲሆኑና በደንብ የሚያውቁትን ነገር በደንብ የሚናገሩ በሆኑ ጊዜ ውይይቱ ያማረ ይሆናል፡፡ የሐገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ በደንብ የተረዱ ሰዎች ንግግራቸው ለመወቃቀስ አይሆንም፡፡ ይልቅስ ዓይን ለዓይን ለመተያየት ነው፡፡ እንዲህ ያለ የውይይት መንፈስ፤ ውይይታቸውን በሚያዳምጠው ሰው ዘንድ ልዩ ስሜትን ያሳድራል፡፡ ሁሉም አንድን ችግር ለመፍታት በመተጋገዝ የሚሰሩ እና በአንድነት መንፈስ ጥረት የሚያደርጉ የአንድ ቡድን ተሰላፊዎች እንጂ፤ ለመሸናነፍ የሚጫወቱ ተቀናቃኞች አይሆኑም፡፡

ለምሣሌ በገዢው ፓርቲ ላይ የሰላ ወቀሳዎችን የሚያቀርቡ ተወያዮች የሚያሷቸው ወቀሳዎች፤ ገዢው ፓርቲ ራሱን መርምሮ ችግሮቹን ነቅሶ እንዲያወጣ ታስበው የሚሰነዘሩ ወቀሳዎች ሲሆኑ፤ ራሱ ድርጅቱ የሚጸየፋቸው የገዛ ችግሮቹ በሌላ አንደበት ሲቀርቡ እንደመስማት ሊቆጥረው ይችላል፡፡ ቋንቋው ወይም አቀራረቡ ይለይ ይሆናል እንጂ ይዘቱ አንድ ይሆናል፡፡ በዚህ ጊዜ ሁሉም የአንድ ቡድን ተጫዋጮች ሊባሉ ይችላሉ፡፡ የሁሉም ዓይኖች በችግሮቹ ላይ ናቸው፡፡ ልዩነት ቢኖር የችግሩ አፈታት ላይ እንጂ በችግሮቹና በችግሮቹ አተያይ ላይ አይሆንም፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚደረጉትን መልካም ውይይቶች ስመለከት ሁሉም ሰዎች ለችግሮቻችን መፍትሔ አድርገው የሚያቀርቡት ነገር በተቋማት ጉዳዮች የሚያጠነጥን ነው፡፡ በሰላም፣ በልማት፣ በዴሞክራሲ እና በመልካም አስተዳደር ወዘተ. ለተጠቀሱ ችግሮች መፍትሔ ብለው የሚያቀርቡት ነገር፤ በትክክለኛ መርህ እና እውነተኛ እምነት ላይ የተመሠረቱ ተቋማትን በመፍጠር፣ በማደስ፣ በማጎልበት ዙሪያ የሚሽከረከር ነው፡፡

እውነት ነው፤ በዓለም ሐገራት መካከል በዴሞክራሲያዊ አስተዳደር እና በሐብት ረገድ የሚታየው ልዩነት መነሻው፤ የህገ መንግስት አንቀጾች መለያየት፤ የቴክኖሎጂ፣ የካፒታል፣ የሰው ኃይል፣ የመሬት፣ የተፈጥሮ ሐብት ወይም የማዕድናት ወዘተ. ልዩነት አይደለም፡፡ ሐገራት የኢኮኖሚ ልማት ሊቀዳጁ የሚችሉት፤ ትክክለኛ የሆነ ወይም ዕድገት አሳላጭ (Pro-growth) ፖለቲካዊ ተቋማት ሲኖሩ ነው፡፡ ዕድገት አሳላጭ የኢኮኖሚ ተቋማት የሚፈጠሩትም፤ ዕድገት አሳላጭ የፖለቲካ አስተሳሰብ (ተቋማት) ሲኖር ነው፡፡ በአጭሩ፤ የኢኮኖሚ፣ የፍትሕ፣ የማህበራዊ ወዘተ. ተቋማቱ ዕድግት አሳላጭ በሆነ መንገድ ሊፈጠሩ የሚችሉት፤ ዕድገት አሳላጭ የፖለቲካ ተቋማት ሲኖሩ ነው፡፡

ዕድገት አሳላጭ ፖለቲካዊ ተቋማት ሲፈጠሩ እና ሲጠናከሩ ሐገራት የዕድገት ጎዳና ተከትለው ብድግ ይላሉ፡፡ እነዚህ ፖለቲካዊ ተቋማት ከሁኔታዎች ጋር ራሳቸውን እያስተካከሉ እና እየቃኙ መጓዝ አቅቷቸው ሲቸከሉ ወይም አቅማቸው በተለያየ ምክንያት ሲዳከም ወይም ጨርሶ ሲወድቅ፤ ሐገራት የገነቡት ስርዓት ተርገድግዶ ይፈራርሳል፡፡ ሐገራቱም አይወድቁ አወዳደቅ ይወድቃሉ፡፡

በእርግጥ፤ በማናቸውም ዘመን እና በትኛውም ሐገር፤ የመንግስት ስልጣንን ለመቆጣጠር እና በራሳቸው ፍላጎት ልጓም የተለጎመ መንግስት ለመፍጠር የሚሹ ይኖራሉ፡፡ መንግስትን የጠባብ ቡድናዊ ወይም ግላዊ ፍላጎታቸው መሣሪያ ሊያደርጉ የሚፈልጉ ወገኖች ይኖራሉ፡፡ የእነርሱን መሻት ተከትሎ የሚንቀሳቀስ ቅይድ መንግስት እንዲኖር የሚጥሩ ወገኖች መኖራቸው አይቀርም፡፡ እነዚህ ወገኖች ያላቸውን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የባህል ወዘተ. ሃይል በመጠቀም የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ እነዚህ ኃያል ቡድኖች ወይም ግለሰቦች ሰፊ ማህበራዊ ልማት የሚያደናቅፍ ፍላጎት ይዘው ሊንቀሳቀሱ የሚችሉ ናቸው፡፡ የእነርሱ ፍላጎት ይሳካ እንጂ የሚሊዮኖችን ዕድል የሚያሰናክል ወይም ሐገር የሚያፈርስ ነገር መያዛቸው ጨርሶ አያሳስባቸውም፡፡ ስለዚህ የፈለጉት እንዲፈጸምላቸው ከመጣጣር ወደ ኋላ አይሉም፡፡ ሐገር የሚያጠፋ ተግባር ቢሆንም ፍላጎታቸውን ለማስፈጸም አያመነቱም፡፡ እንዲህ ያለ አስተሳሰብ ያላቸው ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ምንጊዜም ይኖራሉ፡፡

ታዲያ እነዚህን የፖለቲካ ወይም የኢኮኖሚ ሥልጣን ያላቸው ኃያል ግለሰቦች ወይም ቡድኖች አደብ እንዲገዙ ማድረግ የሚቻለው፤ ፍላጎታቸውን ተረድቶ አንቅስቃሴአቸውን መቆጣጠር የሚችል ህይወት ያለው እና ብቁ-ንቁ የዴሞክራሲ ስርዓት በመፍጠር ብቻ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ያለው አማራጭ ሁለት ነው፡፡ እነዚህ ቡድኖች እንዳሻቸው የማድረግ ዕድል እንዳያገኙ በሩን ጥርቅም አድርጎ የሚዘጋ የዴሞክራሲ ስርዓት  መገንባት ወይም ሐገር ሲፈራርስ ቁጭ ብሎ መመልከት ብቻ ነው፡፡

ይህን ማድረግ የሚቻለውም ጠንካራ የፍትህ ወይም የፖለቲካ ተቋማት በመፍጠር ነው፡፡ ጠንካራ የፍትህ ወይም የፖለቲካ ተቋማት ሳይመሰረቱ ዕድገት ወይም ብልጽግና የሚታሰብ አይደለም፡፡ የዕድገት ምስጢር ነጻነት ነው፡፡ ያለ ነጻነት (በሁሉም ገጽታ) ዕድገት እና ልማት የህልም እንጀራ ነው፡፡

የዓለምን የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ታሪክ መፈተሽ ይቻላል፡፡ ሐገራትን ሐብታም ወይም ድሃ የሚያደርጋቸው፤ የፖለቲካ መዋቅራቸው ልዩነት ነው፡፡ አንዳንዶቹ የዓለም ሐገራት ባለጸጋ ለመሆን የቻሉት፤ ሁሉን አካታች፣ ሳይዛነፍ የሚሰራ፣ የስልጣንን ክፍፍል የሚያረጋግጥ የፖለቲካ ተቋማትን መፍጠር መቻላቸው ነው፡፡ መሠረታዊ የፖለቲካ ተቋማት ለውጥ ሳንፈጥር፤ ጥሩ የኢኮኖሚ ሐሳቦችን መያዝ እና ምርጥ ፖሊሲዎችን መንደፍ ለውጥ አያመጣም፡፡ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ተቋማቱ ተደጋግፈው እና ተሳስረው ካልሰሩ ልማት አይገኝም፡፡ በመሆኑም፤ ለተቋማት መጠናከር በርትተን መሥራት ይኖርብል፡፡

 

Leave a Comment