በአማራ ክልልና በሱዳን የገዳሪፍ ግዛት መካከል ያለው ግንኙነት እያደገ መምጣቱ ተገለፀ

በአማራ ክልል እና በሱዳን የገዳሪፍ ግዛት መካከል ያለው የህዝብ ለህዝብ እና የመንግሥት ለመንግሥት ግንኙነት እያደገ መምጣቱ ተገለፀ።

የአማራ ክልል ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣኖች ከገዳሪፍ ግዛት የልዑካን ቡድን ጋር ዛሬ በባህር ዳር ከተማ በመገናኘት የምክክር መድረክ አካሂደዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በምክክር መድረኩ እንደተናገሩት፥ የገዳሪፍ ከፍተኛ የልኡካን ቡድን እና የአማራ ክልል አቻው ከሁለቱ ጎረቤት ሀገሮች አልፎ በዓለም አጀንዳዎች ሊመክር የሚገባው መሆኑን ገልጸዋል።

በዋናዋና ጉዳዮች ላይ ግልጽና አጭር ውይይት በማድረግ ሁለቱን ቀጠናዎች የሚጠቅሙ የቀጣይ አቅጣጫዎችን ጭምር ማስቀመጥ ይገባልም ብለዋል።

አቶ ገዱ አያይዘውም፥ የሁለቱ ሀገሮች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ረጅም ጊዜ ያስቆጠረና የቆየ ወዳጅነት ያለው በመሆኑ አልፎ አልፎ የሚፈጠሩ ችግሮች የሁለቱም ግዛቶች አመራሮች በውይይት ሊፈቱት የሚገባ መሆኑንም ገልፀዋል።

የገዳሪፍ ግዛት ዋና አስተዳዳሪ ኢንጅነር ምርቃኔ ሷሊህ በበኩላቸው፥ ለተመሳሳይ ውይይት እዚህ ቦታ የተገኙት ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑን ገልጸው፤ ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረው ግንኙነቱ ወደ ተሻለ ደረጃ እያደገ የመጣ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ኢንጅነር ምርቃኔ አክለውም “ዛሬ እዚህ የተገኘነው በፀጥታና በተለያዩ ግንኙነቶቻችን ዙሪያ ለመምከርና አልፎ አልፎ በደንበር አካባቢ የሚፈጠሩትን ትንንሽ ግጭቶች ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት ነው” ብለዋል።

እንዲሁም በባህል ልውውጥ፣ በንግድ ትስስርና የደንበር ልማቱን ሥራ ከዚህም የላቀ ደረጃ የሚያደርስ ውይይቶችን ለማድረግ መሆኑንም መግለፃቸውን ከአማራ ክልል መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

Leave a Comment