ስትራቴጂው ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች ይደግፋል!

ስትራቴጂው ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች ይደግፋል!

                                                                 ደስታ ኃይሉ

አገራችን ተግባራዊ ያደረገችው የብሄራዊ ፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂ በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች የሚደርስና ፋይናንስን በፍትሃዊነት መጠቀም እንዲችሉ እንደሚያደርግ ነው። ይህም እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች የቁጠባ ባህላቸውን ይበልጥ በማሳደግ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ላይ የተያዘውን ግብ ለማሳካት የሚያስችል ነው።

ባፋይናንስ አሰራር እንደሚታወቀው በቴክኖሎጂ የተደገፈ የፋይናንስ ስራ እየሰፋ ከሄደ የፋይናንሱን ዘርፍ ተደራሽነት በዚያው መጠን እየሰፋ እንዲሄድ ያደርገዋል። ይህም የገንዘብ ሽክርክሪቱን ፍጥነት በመጨመር የኢኮኖሚው እድገት እንዲፋጠን ያደርገዋል። ሁሉን አካታች በሆነ የፋይናስ ስርዓት (All Inclusive Fainance System) እንዲፈጠር በማድረግ የኢኮኖሚውን መሰረት ማስፋት ይቻላል።

ለዚህ ደግሞ የግድ የባንክ ቅርንጫፎችን በየቦታው እየከፈቱ መሄድ አይቻልም። ወሳኝ የሚሆነው የኤጀንት ባንኪንግ የመሰሉ የፋይናስ ስርዓቶችን በስፋት እየዘረጉ በመሄድ ዝቅተኛ ገቢ ያለውን የህብረተሰብ ክፍል ማግኘት ይቻላል። የፋይናንስ ተደራሽነቱ አብዛኛውን ህዝብ መያዝ ከቻለ በዚያው ልክ ህዝቡ ተጠቃሚነቱን ከፍ እንዲያደርግ ያስችለዋል።

የሚታቀደው የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማት ፋይዳ በዜጎች የሥራ ሥምሪት እና የኑሮ ደህንነት ሁኔታ መገለፅ ይኖርበታል፡፡ በዚህ ረገድ በቀጣይ ልዩ ትኩረት የሚሰጣቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ሴቶችና ወጣቶች ይሆናሉ፡፡ ከዚህ አኳያ ድህነትና ሥራ አጥነት በመቅረፍ ረገድ የእስካሁኑ አፈጻፀማችንና በቀጣይ የዕቅድ ዘመን የምናስመዘግበውን አፈጻፀም በግልፅ መቀመጥ ይኖርበታል፡፡

እስካሁን ድረስ እያስመዘገብነው የመጣው ፈጣንና መሰረተ-ሰፊ ዕድገት ሥራ አጥነትናና ድህነትን በመቀነስ ረገድ ቁልፍ ሚና ተጫውቷል፡፡ አሁንም ግን ድህነቱና ሥራ አጥነቱ ሰፊ በመሆኑ  በቀጣዩ የዕቅድ ዘመንም ፈጣን ዕድገቱን በማስቀጠል ድህነትንና ሥራ አጥነትን በፍጥነት ለመቀነስ መረባረብ የግድ ይኖርብናል፡፡

በአሁኑ ወቅት ደግሞ ዓለም-አቀፉ ማህበረሰብ በድህረ-2015 የልማት አጀንዳ ዙርያ እ.አ.አ በ2030 ድህነትን ከዓለማችን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት ስምምነት እየደረሰ በመሆኑ አገራቸንም ይህንን ግብ ለማሳካት በሚቀጥሉት ዓመታት ፈጣን ዕድገቱን በማስቀጠል በዕቅድ ዘመኑ የድህነት መጣኔው በጉልህ ለመቀነስና ወደ 16 በመቶ ለማውረድ መረባረብ ይጠይቃል፡፡ ዕቅዱም ይህን ገቢራዊ ለማድረግ ግብ ጥሏል።

ከዚህ ጋር ተመጋጋቢ በሆነ መንገድ ኢኮኖሚያችን በፍጥነት በማደጉ ምክንያት በከተሞችና በገጠር የሚታየውን የሥራ አጥነት መጣኔ እየቀነሰ መጥቷል፡፡ በቀጣዩ የዕቅድ ዘመንም ፈጣን ዕድገቱ በከተሞችና በገጠር የሥራ ዕድል በሚፈጥር መልኩ ማስቀጠል ይኖርብናል፡፡ ለዚህ ደግሞ በተለይ ያቀድነው ዘመናዊ የግብርና አመራረትና ፈጣን የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት ትልቅ ሚና ይጫወታሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎንም በሌሎች መስኮች የግል ኢንቨስትመንት ማበረታታት፣ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን ማስፋፋት፣ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና ልማት ሥራዎች ለሥራ ዕድል ፈጠራ ማዋል፣ እና በመንግስት የሚካሄዱ የልማት ፕሮግራሞች አነስተኛ ኩባንያዎችንና የሥራ ዕድሎችን በሚያስፋፉ መልኩ ለመተግበር ታስቧል፡፡

እርግጥ በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን የአርሶ-አደርና የአርብቶ-አደር ምርታማነትን ለማሳደግና የምርት ጥራት ለማረጋገጥ የተጀመረው ሥራ በዘርፉ ትራንስፎርሜሽን እንዲያመጣ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡

በዚህም ከአነስተኛ አርሶ-አደር ማሳ በመኸር ወቅት የሚገኘው የሰብል ምርት በ2007 ከነበረበት 270 ሚልዮን ኩንታል በዕቅዱ የመጨረሻ ዓመት ወደ 406 ሚልዮን ኩንታል ለማሳደግ እየተሰራ ነው፡፡

በ2009 ዓ.ም የተገኘው የ345 ሚለዩን ኩንታል ምርት የዕቅዱን ስኬታማነት ከወዲሁ የሚያሳይ ነው፡፡ ይህም የምርቱ ባለቤት የሆነው አርሶ አደር ተጠቃሚ ከመሆን በላይ ለቁጠባ እንዲተጋ ያደርገዋል። የፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂ ከዚህ አኳያም ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡

ታዲያ እዚህ ላይ የግል ቁጠባ ውጤታማ እንዲሆን ከኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ተግባር በፀዳ እና በግልፅ ቅደም ተከተል ጥቅም ላይ ማዋል ይገባል፡፡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን መጨረሻ ኢንቨስትመንት ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት የሚኖረው ድርሻ 41 ነጥብ 3 በመቶ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። ይህም ከጠቅላላው የሀገር ውስጥ ምርት ያለው ድርሻ በ2007 ከነበረበት 80 ነጥብ 5 በመቶ በ2012 ወደ 70 ነጥብ 5 በመቶ ዝቅ እንደሚል ተተንብዩዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ በዚሁ የዕቅድ ዘመን የወጪ ንግድ ገቢ አገልግሎትን ጨምሮ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ያለው ድርሻ ከፍተኛ ዕመርታ በማሳየት በ2007 ከነበረበት 12 ነጥብ 8 በመቶ በ2012 ወደ 20 ነጥብ 6 በመቶ ያድጋል። የገቢ ንግድ ወጪ አገልግሎትን ጨምሮ በ2007 ከነበረት 29 ነጥብ 6 በመቶ በ2012 ወደ 32 ነጥብ 3 በመቶ ከፍ ይላል፡፡ በዚህ መሠረትም የሃብት ክፍተት ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ያለው ድርሻ በ2007 ከነበረበት 16 ነጥብ 8 በመቶ በ2012 መጨረሻ ወደ 11 ነጥብ 7 በመቶ ዝቅ እንደሚል ትንበያው ያሳያል፡፡

ታዲያ በዕቅዱ ዘመን በቁጠባና በኢንቨስትመንት መካከል ያለውን ሚዛን ለማጥበብ የሚከናወኑ ተግባራት ቢኖሩም ክፍተቶቹን ሙሉ በሙሉ መድፈን ይቻላል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ስለሆነም ጉድለቶቹን ለመሸፈንና የታቀደውን ፈጣን ዕድገት ለማስቀጠል እንዲቻል የውጪ ብድርና ዕርዳታ ማግኘት የግድ ይመስለኛል።

ሆኖም ከመንግስት ቀደም ያሉ ተግባራቶች መረዳት እንደሚቻለው አገሪቷ ለዕዳ ጫና ተጋልጣ ዕድገትዋ እንዳይገታ ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረጉ የሚቀር አይመስለኝም። ለነገሩ እስካሁን ድረስ የአገሪቱ የዕዳ ጫና ሁኔታ የቅርብ ክትትል እየተደረገበት የመጣ ነው።

እናም በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የተያዘው የኢንቨስትመንትና የቁጠባ ትልሞችን ከግብ ለማድረስ ከላይ በመረጃ አስደግፌ የገለፅኳቸውን የውጤታማነት እሳቤዎችንና የተግዳሮቶች መፍትሔዎችን በየደረጃው ተግባራዊ ማድረግ ይገባል።

በተለይ በአሁኑ ወቅት ተግባራዊ የሆነው ብሄራዊ የፋይናንስ አካታችነት እነዚህን ችግሮች የመቅረፍ ሚና አለው። የአካታችነት አሰራሩ ላይ ሊፈጠሩ የሚችሉ ተግዳሮቶችን ከወዲሁ በመለየት ለአገር በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን ይደግፋል የተባለው ስትራቴጂ በአግባቡ ስራ ላይ መዋል እንዳለበት መቆጣጠር የሁሉም ዜጋ ድርሻ ነው።  

 

Leave a Comment