ሥርዓቱ ልዩነቶች እንዲንሸራሸሩ የሚፈቅድ ነው!

ሥርዓቱ ልዩነቶች እንዲንሸራሸሩ የሚፈቅድ ነው!

ዳዊት ምትኩ

በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሥርዓት ማንኛውም ዜጋ በህገ መንግስቱ የተሰጡትን ዴሞክራሲያዊ መብቶችን በአግባቡ እንዲጠቀም እድል ተመቻችቶለታል። በተለይም ገዥው ፓርቲና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ችግሮቻቸውን ለመፍታት ለወራቶች እያካሄዱ የሚገኙት ድርድር የሥርዓቱ ዴሞክራሲያዊነት ዓይነተኛ መገለጫና ሥርዓቱ ልዩነቶችን በፀጋ ተቀብሎ የሚያንሸራሽር መሆኑን የሚያሳይ ነው።

የኢትዮጵያ ህዝቦች መብታቸውን ለዘመናት ተረግጠው የኖሩባት፣ የዴሞክራሲ ጭላንጭል ያልታየበት፣ልማትና ዕድገት ሊረጋገጥ ያልታሰበባት ሀገር፤ ዛሬ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ዘርግታ ይህን የመሰለ የውይይት መድረክ ማየቷ ማንኛውንም ዜጋ እንደሚያስደስተው ጥርጥር የለውም።

በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ ህዝቦች ሊመሯቸውና ሊያስተዳድራቸው የሚችሉ፣ በተጨባጭ በምረጡኝ የምርጫ ዘመቻ ወቅት ፖርቲዎች ያከናወኑትን ወይም የሚያከናውኑትን ተግባር በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የእገሌ ፖርቲ በቀጣይ ለውጥ ያመጣልናል ብለው ያመኑበት፣ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ያላንዳች ተፅዕኖ ካርዳቸውን በመስጠት ተመራጩን ፓርቲ ለስልጣን ማብቃት ነው። ይህም በህገ መንግስቱ በግልፅ እንደተደነገገውም ስልጣን በሕዝብ ድምፅ እንጂ በሌላ መንገድ የሚገኝ እንዳልሆነ ያስረዳናል።

በመድብለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታ ሂደት ውስጥ ባለፋት ጊዜያት የተከናወኑ አምስት ሀገራዊና በርካታ ክልላዊ እንዲሁም የአካባቢና የአዲስ አበባ የምክር ቤቶች የሟሟያ ምርጫዎች የላቀ ሚና ተጫውተዋል። በእነዚህ የምርጫ ሂደቶች የሕዝቡ ተሳትፎና ዴሞክራሲውን ወደፊት ለማራመድ የነበረው ሚና ከፍተኛ እንደነበር አንዘነጋውም። የሀገሪቱን የፖለቲካ ምህዳር በማስፋት ረገድም የተካሄዱት ምርጫዎች የላቀ ሚና ነበራቸው።

የፖለቲካ ፖርቲዎችም ቢሆኑ በቁጥር ይሁን በአስተሳሰብ ደረጃ የዴሞክራሲን ምንነት በውል ተረድተው በምርጫ በመሳተፍ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደቱ የነበራቸው ድርሻ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ግና እዚህ ላይ ሳልጠቅስ የማላልፈው ዋነኛ ጉዳይ፤ የሀገራችን የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታ ገና 26 ዓመታትን ብቻ ያስቆጠረ ለጋ መሆኑን ነው። ያም ሆኖ ምንም እንኳን የተሟላ ባይሆንም፤ ገዥውም ይሁን ተቃዋሚ ፓርቲዎች የዴሞክራሲያዊ ባህል ግንባታ ሂደቱ ስር እንዲሰድ የተቻላቸውን ያህል ጥረት አድርገዋል። ሰሞኑን በምርጫና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዩች እያካሄዱት ያሉት ድርድርና ውይይት የዚህ ጥረታቸው አካል ነው ማለት ይቻላል። ይህም ለመድብለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታው የበኩሉን አስተዋፅኦ ያበረክታል።

እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ባለፋት ዓመታት የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታን በሂደት እየገነባች መጥታ፣ ድህነትን ለማሸነፍ ባደረገችው ርብርብ አንፀባራቂ ሊባል የሚችል ውጤት አግኝታለች።

ይሁን እንጂ፤ ሁሌም ልዩነታችን አንድነታችን ሆኖ ሳይቀጥል ቀርቶ በመነቋቆርና በመነካከስ እንዲሁም የሌሎች አጀንዳ አስፈፃሚዎች ከሆንን እንደዚህ ቀደሙ ለዘመናት ወደ መጣንበት የድህነት አረንቋላ መመለሳችን የሚቀር አይመስለኝም። ይህ እንዳይሆን ሁሉም ፓርቲዎች ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ ወሳኝ የህልውና ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ ለአተገባበሩ መትጋት ይኖርባቸዋል።

በአሁኑ ሰዓት ገዥው ፓርቲ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር የሚያደርጋቸው አበረታች ውይይቶች እንደተጠበቁ ሆነው፣ ዴሞክራሲውን ለማስፋትና ጥልቀት እንዲኖረው ለማድረግ የተያዘው ቁርጠኝነት በሚፈለገው ፍጥነት መጎልበት ይኖርበታል።

ያም ሆኖ በአሁኑ ሰዓት ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ በህገ መንግስተ መሰረት ተደራጅቶ ሃሳቡን ያቀርባል፤ ይከራከራል፤ የሚወክለውን የህዝብ ድምፅንም ለማግኘት ይችላል። ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ህገ መንግስቱ ባጎናፀፋቸው የመደራጀት መብት መሰረት በህጋዊ መንገድ የተመዘገቡ በርካታ የመንግስት ተቃዋሚዎች ቀጥተኛ እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው፡፡ እነዚህ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ዓላማቸውን ለማሳካት በሚያካሄዱት ማናቸውም እንቅስቃሴ ጣልቃ የሚገባ አንድም የመንግስት አካል የለም፡፡ ፓርቲዎችቹ በሀገራዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ ይሰጣሉ፤ አቋማቸውንም ያንጸባርቃሉ፡፡

ፓርቲዎቹ ተደራሽነታቸውን ለማስፋትም በመገናኛ ብዙሃን ተጠቅመው ዓላማቸውን ለህዝቡ ሲያደርሱ ማየት የተለመደ ነገር ነው፡፡ ታዲያ ለምን ይህን አቋም አንጸባረቅክ ተብሎ የታገደ ፓርቲም ይሁን የታሰረ ግለሰብ እንደማይገኝ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ ከዚህ ባሻገር ገዥው ፓርቲና ተቃዋሚ ድርጅቶችን የሚያቀራርብና በወቅታዊ ጉዳዮች ያላቸውን አቋም የሚያንጸባርቁበት የክርክር መድረኮች እየተበራከቱ መምጣታቸው ሀገራዊው የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት እየዳበረ መሄዱን የሚያመላክት ነው፡፡

የኢፌዴሪ ህገ -መንግስት ለዜጎች ካጎናፀፋቸው ዴሞክራሲያዊ መብቶች መካከል የቡድንና የግለሰብ መብቶች ይገኙበታል፡፡ ከእዚህም ውስጥ የአመለካከትና ሃሳብን በነጻ የመያዝና የመግለጽ፣ የመሰብሰብና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነጻነት እንዲሁም አቤቱታን የማቅረብ መብት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ እነዚህ መብቶች በህግ ካልሆነ በስተቀር በማንኛውም መልኩ ሊገደቡ የሚችሉ አይደሉም፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ማናቸውም መብቶች የሚከበሩት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የዘመናት ትግል ውጤት እንዲሁም የአገሪቱ የመኖርና ያለመኖር ህልውና ጉዳይ መሆናቸውን መንግስት በፅናት ስለሚያምን ብቻ ነው።

በመሆኑም ሀገራችንን የማይገልፅና “ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ” እንዲሉት ዓይነት ጭፍን ዲስኩር ከትዝብት ውጪ የሚያስገኘው ጥቅም ባለመኖሩ ነገሮችን በእርጋታና በሰከነ ሁኔታ መመልከት ይገባል። አገራችን ውስጥ ‘እነ እገሌን ለመጭጥቀም ሲባል የሚሰራ ነው’ የሚባለ ነገር የለም።

በህገ መንግስታችን አንቀፅ 31 ላይ እንዳሰፈረው “ማንኛውም ሰው ለማንኛውም ዓላማ የመደራጀት መብት አለው። ሆኖም አግባብ ያለውን ህግ በመጣስ ወይም ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በህገ ወጥ መንገድ ለማፍረስ የተመሰረቱ ወይም የተጠቀሱትን ተግባራት የሚያራምዱ ድርጅቶች የተከለከሉ ናቸው” በሚል በተደነገገው መሰረት፣ ማንኛውም ዜጋ ባሻው ማህበር ወይም የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ ታቅፎ መንቀሳቀስ እንዲችል በመደረጉ ሀገራዊ ዴሞክራሲው አቅም በፈቀደ መጠን እንዲሰፋ ተደርጓል።

በዚህም ለዴሞክራሲው መጎልበት ወሳኝ ሚና ያላቸው በርካታ ሲቪክ ማህበራትና የፖለቲካ ድርጅቶች ተመስርተው ህጋዊ በሆነ መንገድ ተግባራቸውን ሲያከናውኑ ዛሬ ላይ ደርሰዋል። በአሁኑ ሰዓትም በፓርቲዎች መካከል የሚካሄደው ድርድር ስርዓቱ የመደራጀት መብትን ማረጋገጡንና ማናቸውም ሃሳቦች እንዲንሸራሸሩ ያለውን ምቹ ምህዳር የሚያሳይ ነው። ይህ ሁኔታም የሥርዓቱን ዴሞክራሲያዊነት ከምን ጊዜውም በላይ የሚያሳይና ዴሞክራሲያችን ሳይሸራረፍ እውን እንዲሆን ያለውን ቁርጠኝነት የሚያረጋግጥ ነው።

እርግጥ ዛሬ አገራችን ውስጥ የመደራጀት መብቱን ተከትሎ የየራሳቸው ደጋፊዎች ያሏቸው የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተመስርተውና በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በህጋዊ መንገድ ተመዝግበው ዴሞክራሲውን ለማስፋትና ለማጥለቅ የሚንቀሳቀሱ አገራዊ ፓርቲዎች ተፈጥረዋል። በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል እየተካሄደ ያለው ድርድር የዚህ እውነታ ማሳያ ነው።

 

 

Leave a Comment