ሠላም ያለሕዝብ ተሳትፎ…

ሠላም ያለሕዝብ ተሳትፎ…

ወንድይራድ ኃብተየስ

ሠላም ከሌለ ስለ ልማትም ይሁን ስለ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ማሰብ አይቻልም። ስለ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ማቀንቀንም ብሎም መናገር ትርጉም አይኖረውም። ያለምክንያት አይደለም። እነዚህን ሦስት መሠረታዊ ጉዳዮች ነጣጥሎ ማየትም አይቻልም። አንዱ ያለሌላው መቆም አይችልም። ይህን እውነታ ለማየት የኢትዮጵያን ያለፉት 27 ዓመታት ነጉዞ መለስ ብሎ መመልከት በቂ ይሆናል። ኢትዮጵያ በመላ አገሪቱ ሠላምን በማስፈን ፈጣንና ተከታታይ ዕድገትን እውን ለማድረግ የተጓዘችበትን ረዥም መንገድ መቃኘት ተገቢ ይሆናል።  

ሆኖም ይህ ጉዞ ብዙ ጋሬጣዎች ነበሩት። ጉዞው አልጋ በአልጋ አልነበረም። በአንድ በኩል ሠላማዊ መስለው በህገ ወጥ መንገድ በሚንቀሳቀሱ፤ በሌላ ወገን ፀረ ኢትዮጵያ በሆኑ ኃይሎች ድጋፍ በተላላኪነት በተሰለፉ፤ በሌላኛው ዘውግ ደግሞ በጽንፈኛ የፖለቲካ አቋማቸው በሚታወቁና አገር ውስጥ ሆነው “በህጋዊ መንገድ እንታገላለን” በሚል ሽፋን አገሪቱ ከምትመራባቸው የህግ ማዕቀፎች ውጭ በመውጣት የተገኘውን አስተማማኝ ሠላም ለማደፍረስ በሚጣጣሩ ቡድኖች በርካታ ያልተሳኩ ጥረቶች ተደርገዋል።  

ይሁንና ሠላምን በፅኑ የሚሹት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ደማቸውን ዋጅተውና አጥንታቸውን ከስክሰው ያገኟቸው የሠላም፣ የልማትና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ውጥኖች እንዳይቀለበሱ በመንገዳቸው ላይ ደንቃራ የሆኑትን እየጠራረጉ ጥሎ ለማለፍ ብርቱ ትግል አድርገዋል። ቀናው መስመር እንዳይጎረብጥ፣ ጉዞውም የኋሊት እንይታጠፍ እነዚህን ኃይሎች በብርቱ ታግለዋቸዋል።  

በተለያዩ ወቅቶች እነዚህ ፀረ ኢትዮጵያ ኃይሎች በህጋዊና በሠላማዊ መንገድ ብቻ ትግላቸውን እንዲያካሂዱ ተጠይቀዋል። ሠላምን አጥብቆ የመሻት ጉዳይ የአገራችን ህዝቦች ፅኑ ፍላጎት በመሆኑ እነዚህ ኃይሎች ቀናውን መንገድ ይከተሉ ዘንድም ተማጽዕኖ ቀቦላቸዋል – ምንም እንኳን ጆሮ ዳባ ልበስ ቢሉም። ሆኖም ግን ዛሬም ድረስ ምኞት ፍላጎታቸው ዳር አልደረሰም። ይልቁንም ዛሬ በመላ አገሪቱ አስተማማኝ ሠላም ሰፍኗል።  በዚህም ማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት ሠላማዊ ትግል ማካሄድ የሚችልበት ምህዳር ሰፍቷል። ይህ ሠላማዊ አውድ ሊገኝ የቻለው ህዝቡ ስለ ሠላም ካለው ቀናዒ ምልከታ አንጻር መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል።

በየትኛውም አገር እንደታየው ህዝብ ሠላም ከሌለው ጥቂቶች መብት ሰጪና ነሺዎች ይሆናሉ። አምባገነንነት ይሰፍናል። ጉልበተኞች የህግ አስፈፃሚ ይሆናሉ። በሠላም ወጥቶ መግባት አይታሰብም። ህግና ሥርዓት በጉልበተኞች ይወሰናል። ጉልበተኞቹ ከሚፈልጉት ጊዜና እውቅና ውጭ ማንም ሰው ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ አይችልም። ህግ የበላይነቱን ይነጠቃል። በአምባገነን ኃይሎች እጅ ይወድቅናም ሁሉም ነገር ምስቅልቅሉ ይወጣል።

ይህንን የሠላም እጦት ፈተና የየትኛውም አገር ህዝብ ይገነዘበዋል። ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ደግሞ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው። ያለ ሠላም አንዳችም ነገር ሊፈፀም አይችልም። የዓለም ህዝብ ይህንን ጠንቅቆ ያውቃል። አንዳንድ መንግሥታት  ሠላምን ለማስፈን ሲሉ ሠላምን የሚያረጋግጡ አዋጆችን፣ ደንቦችን፣ ሥርዓቶችን ያወጣሉ። ዳሩ ምን ያደርጋል! እነዚህ አዋጆች፣ ደንቦችና ሥርዓቶች በህዝቡ ዘንድ ይሁንታን ካላገኙ ተፈጻሚነታቸው አጠራጣሪ ነው።  

በእርግጥም አዋጅ በለው ደንብና ሥርዓት የታለመለትን ግብ ሊመታ የሚችለው በህዝብ ዘንድ ሙሉ ተቀባይነት ሲያገኝ ነው። የህዝብ ተሳትፎ ሲታከልበት ደግሞ ዘላቂነቱና አስተማማኝነቱ የዚያን ያህል የጠነከረ ይሆናል። ይህም ሁኔታ የሠላም ዋነኛው ምሶሶና ማገር የዚያች አገር ህዝብ እንጂ አዋጅ ሊሆን እንደማይችል በተጨባጭ ያሳያል። ህዝብ ያልተሳተፈበት ጉዳይ ትርጉም የለውም የሚባለውም ለዚሁ ነው። ያለበለዚያ የሚፈለገውንም ዓላማ ማሳካት አይቻልም። ይህም የየአካባቢውን ሠላም ማረጋገጥ የሚቻለው በህዝቡ ተሳትፎ እንጂ በአዋጅ ብቻ እንደማይሆን ጥሩ ማሣያ ነውና።

በየአካባቢው የሚገኘው የአገራችን ህዝብ ያገኘውን አስተማማኝ ሠላም ገለል አድርጎ ሁከትና ግርግር ቦታውን እንዲረከብ ቅንጣት ያህል ፍላጎት የለውም። በትውስታነት የኋሊት የሚሸሸውና ዳግም እንዳይመጣም ዶሴውን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ዘግቷል። የያኔው ችግር ሰቆቃ ተመልሶ እንዳይመጣ አይፈቅድም። ለሠላሙ ሲባል ፀር የሆኑ ቡድኖችን ያወግዛል፤ ያጋልጣል፣ በጽናት ይቆማል። ተገቢውን ትምህርት እንዲወስዱም በባለቤትነት መንፈስ ተነሳስቶ ይታገላቸዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ ላለፉት 27 ዓመታት ገደማ የተራመዳቸው የልማት አባጣና ጎርባጣ ውጣ ውረዶች በአሁኑ ወቅት የሚቀራቸው ተጨባጭ ለውጦች አሉት። ከትናንቱ በተሻለ ቁመና ላይ እንደሚገኙም ያውቃል። ይህንንም በተሻለ ማማ ላይ እንዲወጣ በልማቱ ውስጥ ተዋናይ የሆነው ማንኛውም ዜጋ በየደረጃው ተጠቃሚ እየሆነ መምጣቱን ራሱን ዋቢ አድርጎ ማቅረብ ይችላል። ትክክለኛ ፖሊሲና ስትራቴጂ ከተነደፈ፣ ህዝቡን ከዳር እስከ ዳር የሚያንቀሳቅስ ልማታዊ መንግሥት ካለና በዚሁ መሪ አካል አስተባባሪነት ብሎም በህዝቡ የባለቤትነት መንፈስ የሚዘወር ሠላም እስካለ ድረስ፤ ሰርቶ መለወጥና ማደግ ይቻላል።

አምባገነኑና የዕዝ ኢኮኖሚ መርህን የሚከተለው የደርግ ሥርዓት ከመገርሰሱ በፊት የሀአገራችን ምጣኔ ሀብታዊ አኃዝ ከዜሮ በታች ነበር። ይህ ህዝብ ስለ ሠላም አብዝቶ ቢናገር አይበዛበትም። አምባገነኑ ሥርዓት እንደወደቀም በአንድ በኩል ሠላምን የማረጋጋት፣ በሌላ በኩል ደግሞ የደቀቀውን ምጣኔ ሀብት ለማቃናት የከፈለውን ከባድ መስዋዕትነት ጠንቅቆ ይገነዘባል።

ያኔ የማይቻል የሚመስለውንና እንደ ተራራ ገዝፎ የሚታየውን የአገሪቱን ድህነት ለመዋጋት የተለያዩ መርሆዎች ቢሰነቅም የሚፈለገው ዓይነት ለውጥ እንዳልመጣ እሙን ነው። ለረጅም ጊዜ በአገራችን ውስጥ ተንሰራፍቶ የነበረውን የድህነት አዙሪት ለመቀልበስ እንዳልተቻለ በመታወቁ ሌላ መንገድ መቀየስ ማስፈለጉ የሚታወስ ነው።

በመሆኑም በአንድ በኩል የአገሪቱን ሠላም ማረጋጋትና የታጠቁ ቡድኖችን ወደ ልማት የማዞር ሥራ፣ በሌላኛው ዘውጉ ደግሞ ፈጣንና ተከታታይ ልማትን የማምጣትና ሁሉንም ዜጋ በየደረጃው ተጠቃሚ የሚያደርግ ፖሊሲና ስትራቴጂን እውን ለማድረግ የወሰደው ጊዜና የጠየቀው ሁሉን አቀፍ መስዋዕትነት ከዚህ ህዝብ አዕምሮ አይጠፋም።

ከዚህም ጋር የተዛቡ አስተሳሰቦች ከሞላ ጎደል በመታረማቸውና መንግሥትም ድህነትን ለመቀነስ በወሰዳቸው ሰፋፊ ርምጃዎች ባለ ሁለት አኃዝ ዕድገት ማስመዝገብ ተችሏል። የኢትዮጵያ ህዝብ የሠላም መኖር ምን ያህል ፋይዳ እንዳለው ጠንቅቆ ያውቃል።  የአገራችን ህዝብ በአምባገነኑ የኤርትራ መንግሥት የተቃጣበትን ወረራ ፈጥኖ በመመከት፣ ውስጠ ድርጅት ሕፀፆችን በአስቸኳይ ፈትቶ ፊቱን ወደ ልማት ባይመልስ ኖሮ፤ ሠላሙን አጥቶ በጦርነትና በንትርክ ወርቃማ ጊዜውን ያጠፋ ነበር። ይህን ደግሞ ከዚህ ህዝብ በላይ ከቶ ማን ሊገነዘብ ይችል ይሆን?

እንዲህ ዓይነቱ ሠላምን የሚያጎሉ፣ ልማትን የሚያፋጥኑና ንትርክን የሚያስቀሩ መንገዶችን መከተል ባይቻል ኖሮ፤ የመጀመሪያውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድን ስኬታማ ማድረግ ይቻል ነበርን? ሁለተኛውን ዕትዕ በጤናማ ሂደት ማስቀጠል ይቻል ነበርን? በአጠቃላይ የተጀመረውን የፀረ ድህነት ዘመቻውን አጠናክሮ መቀጠል ይቻል  ነበርን?። ዛሬ የኢትዮጵያ ህዝብ ከልማት ዕቅዱም በየደረጃው ተጠቃሚ ሆኖ ተፈላጊውን የዕድገት ራዕይ ሰንቆ ባልተጓዘም ነበር። አሁን እያለመ ላለውና ከመጀመሪያው ዕቅድ ጋር ተመጋጋቢ የሆነውን ሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድም ጉዞው ስኬታማ ሆኗል።  

በዚህ ደረጃ ላይ ሆኖ የተጀመረውን ዕድገት ለማስቀጠልና በዚያውም ልክ መሳ ለመሳ ዴሞክራሲው አገር በቀል ፍላጎትን መሠረት ባደረገ መልኩ እንዲጎለብት የተደረገው ጥረት እንዳለ ሆኖ በአንዳንድ የኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች ውስጥ ከመልካም አስተዳደር ጋር ተያይዞ ኪራይ ሰብሳቢዎች እንዲሁም ፅንፈኛ ኃይሎችና የአገራችንን መለወጥ የማይሹ ኃይሎች ጎትጓችነት የተከሰተውን ሁከት ለመቋቋም ህዝቡ በባለቤትነት ስሜት የከፈለው መስዋዕትነት በቀላሉ አይታይም። ይህም ሁኔታ ህዝቡ የየአካባቢውን ሠላም በማስጠበቅ እስካሁን ድረስ ያበረከተው አስተዋፅኦ ዋነኛው የሠላም ተዋናይ እርሱ መሆኑን ያረጋግጣል።

 

Leave a Comment