ለፀረ ሙስና ትግሉ መፋፋም…

ethiopia

 

ለፀረ ሙስና ትግሉ መፋፋም…

 

አባ መላኩ

 

መንግሥት ራሱን ከሕዝብ ፍላጎት ጋር ማስተካከል ያስችለኛል የሚላቸውን ርምጃዎች በቅደም ተከተል በመውሰድ ላይ ይገኛል። ከጥልቅ ተሃድሶው ማግሥት ተገቢው ትራክ ላይ ቆሟል። መንግሥት የተሻለ አስፈጻሚ የሚላቸውን ወደ ከፍተኛ አስፈጻሚነት ማምጣቱ ወይም ፈጻሚዎችን ከአንድ ቦታ ወደሌላ የሥራ ኃላፊነት ያሸጋሸገው ህዝቡ በሚፈልገው ፍጥነት ለውጥ ለማስመዝገብ ነው። መንግሥት አዳዲስ አስፈጻሚዎችን ወደ ከፍተኛ የመንግሥት ሥልጣን ማምጣቱ የቀድሞዎቹ አስፈጻሚዎች ህዝብ በሚፈልገው መጠንና ፍጥነት ለውጥ አላመጡም በሚል እንጂ እነዚህ ግለሰቦች ተጨባጭ ለውጦችን ማስገብ የቻሉ እንደነበሩ ማገናዘብ የሚከብድ አይመስልም።

 

ኢትዮጵያ ባለፉት 26 ዓመታት በልማት ብቻ ሳይሆን በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታም ተጨባጭ ለውጦችን ያመጣችው የዛሬ ዓመት ገደማ ከኃላፊነታቸው በተነሱ አስፈጻሚዎች ጭምር መሆኑን ማሰብ ተገቢ ነው። በመሆኑም እነዚህ አካሎች የአገራችን ባለውለተኞች መሆናቸውን መዘንጋት የለብንም። አንዳንድ ጽንፈኛ ግለሰቦችና የዳያስፖራ ፖለቲከኞች የቀድሞዎቹን አስፈጻሚዎች በተመለከተ ይሰነዝሯቸው የነበሩት አስተያየቶች እጅግ የወረዱና ከመንገድ የወጡ ሆነው ታዝቤ አልፌያቸዋለሁ። ለማንኛውም የዛሬ የጽሁፌ ርዕሰ ጉዳይ የእነሱን የወረዱ አስተያየቶች ለመዳሰስ ባለመሆኑ ወደጭብጤ ልመለስ።

ዛሬ የአገራችን ህዝቦች ፍላጎት እጅጉን አድጓል። መብቱን ጠያቂ ኅብረተሰብ መገንባት መቻሉ በራሱ አንድ ስኬት ነው። ጠያቂ ኅብረተሰብ የዴሞክራሲ ሥርዓት ስለመኖሩ አንዱ ማሣያ ነው። በእርግጥ በኢትዮጵያ ዛሬ ላይ የመልካም አስተዳደር ችግሮች መኖራቸው ይታወቃል።

 

መብቱን የሚጠይቅ ዜጋና ምላሽ የሚሰጥ መንግሥት መኖሩ በአገሪቱ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መፈጠሩን የሚያሳይ ነው። መንግሥትን የሚመራው ኢሕአዴግም በኅብረተሰቡ የተነሱ ጥያቄዎችን አምኖ ተቀብሎ ራሱን የማስተካከል ርምጃዎች በመውሰድ ላይ ነው። ከዚህ ውስጥ ቀዳሚውና ዋነኛው አስፈጻሚውን አካል እንደገና የማዋቀር ሥራ ማካሄዱ ነው።

 

በአዲስ የተተኩት አስፈጻሚዎች አገራችን በዓለም ፈጣን ዕድገት የሚባል ለውጥ ማስመዝገብ የቻሉ እንደሆኑ መታወቅ ይኖርበታል። አዲሶቹ ተሿሚዎች የባለፈውን አስፈጻሚዎች መልካም ነገሮች በመውሰድ ደካማ ጎኖችን ደግሞ በማረም አገራችንን ወደተሻለ ከፍታ ማውጣት ይኖርባቸዋል። የቀድሞዎቹን አስፈጻሚዎች በማጣጣል አዳዲሶቹን አስፈጻሚዎች ደግሞ ተዓምራዊ ለውጥ እንደሚያመጡ አድርጎ አስተያየት መሰንዘር በቀድሞዎቹ ላይ ብቻ ሳይሆን በአዳዲሶቹ ላይ ሥነ ልቦናዊ ጫና ያስከትላልና አግባብነት ከጎደለው አስተያየት ልንቆጠብ ይገባል።

መንግሥት የተሻለ አፈጻፀም ሊያስመዘግቡ ይችላሉ የሚላቸውን አስፈጻሚዎች ይሾማል፣ ከቦታ ቦታ ያሸጋሸጋል እንዲሁም ተጠያቂ የሚሆኑ ካሉም በህግ አግባብ ተጠያቂ ያደርጋል። ይህ በኢሕአዴግ ቤት አዲስ አሠራር አይደለም። ከፍተኛ ባለሥልጣኖችን ተጠያቂ በማድረግ እንደ ኢሕአዴግ ያለ ፓርቲ በአፍሪካ ውስጥ ያለ አይመስለኝም። ከወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ታምራት ላይኔ ጀምሮ ታላላቅ አመራር የነበሩ ሚኒስትሮችን እሥር ቤት የወረወረ ፓርቲ ነው – ኢሕአዴግ። ኢሕአዴግ በርካታ የድርጅቱን መሥራች አንጋፋ ታጋዮችን ሳይቀር ለጥፋታቸው ተጠያቂ እንዲሆኑ የማድረግ ልምድ ያለው ፓርቲ በመሆኑ አሁንም ይህ አሠራር የነገሰበት ነው።

አንዳንዶች መንግሥት በላይኛው አስፈጻሚ ላይ እየወሰደ ያለውን ርምጃ ከህዝብ ጋር ቀን ከቀን የሚያገናኙ የታችኛው አስፈጻሚ ድረስ ሊያወርደው ይገባል ሲሉ እየሰጡ ያለው አስተያየት ተገቢነት ያለው እውነታ ነው። መንግሥት ከአገር አጠቃላይ ብሔራዊ ጥቅም ይልቅ የራሳቸውንና የቢጤዎቻቸውን ጥቅም ብቻ በሚያስቀድሙ አንዳንድ ከፍተኛ ኃላፊዎች ላይ እየወሰደ ያለውን ርምጃ አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። በራሳቸው የማይተማመኑና በፅናት የሚቆሙለት ሕዝባዊ ዓላማ የሌላቸው ራስ ወዳዶች፣ ሕዝብን በመከፋፈል፣ የህዝብን ጥቅም ችላ በማለት በየቦታው ችግር ሲፈጥሩ የነበሩ አስፈጻሚዎች በጥልቀት ሊፈተሹ ይገባል።

 

በጥልቀት መታደስ ዋነኛ ዓላማ መነሻና መድረሻ የመንግሥት ሥልጣን ለህዝብ አገልግሎት ብቻ እንዲውል ማድረግ ነው። በጥልቀት መታደስ ስም የሚካሄዱ የግለሰቦች ለውጥ ለጥፋተኞችና ለኪራይ ሰብሳቢዎች መደበቂያ ጉድጓድ መቆፈሪያ እንዲሁም መልካሞችን ማጥቂያ መሣሪያ እንዳይሆንም መንግሥት መጠንቀቅ ይኖርበታል። በየመድረኩ ለህዝብ ጥቅም ዋስ ጠበቃ እንደሆኑ አድርገው ራሳቸውን ለማቅረብ የሚሞክሩ የመድረክ አንበሶችን አካሄድ መንግሥትና ህዝብ ነቅቶባቸዋል። ኅብረተሰቡ በተለይ በቅርበት ያሚያውቃቸውን የታችኛው አስመሳይ ፈጻሚዎችንና አስፈጻሚዎችን በጥልቅ ተሃድሶው ሂደት ለይቷል።  

 

በመንግሥትን የጥልቀት የመታደስ መርህ ኅብረተሰቡም በአግባቡ ተረድቶ በጉዳዩ ላይ በባለቤትነት መንፈስ በቀጥታ ሊሳተፍበት ይገባል። ይህ ካልሆነ በመንግሥት ጥረት ብቻ በጥልቀት የመታደስ ሂደት ውጤት ይመጣል ብሎ ማሰብ ከባድ ነው። መንግሥት ራሱን በቁርጠኝነት ውስጡን ለማፅዳት እንደተነሳ ሁሉ ኅብረተሰቡም ከመንግሥት ጎን መሰለፍ ይኖርበታል። ህዝብና መንግሥት በቅርበት በመሥራት የታዩ ችግሮችን መቅረፍ ካልቻሉ አገራችን ዳግም ወደ ችግር እንደምትገባ እያጠራጥርም፡፡

 

የጥልቅ ተሃድሶው የሕዝብ ቅሬታና ብሶት መነሻ ማድረጉ መልካም ጅምር ነው። በጥልቅ ተሃድሶው ሂደት የግለሰቦችን የጥቅም ግንኙነቶች በመበጣጠስ የመንግሥት አሠራርን ለሕዝብ ግልጽና ተጠያቂነት እንዲኖረው በማድረግ ተጠያቂነት ያለው አሠራርን ማንገስ ተገቢ ነው። የመንግሥት አሠራር ግልጽና ተጠያቂነት እንዲኖረው ከሚያደርጉት ነገሮች መካከል አንዱና ዋነኛው ደግሞ መገናኛ ብዙኃን ነው። የአገራችን መገናኛ ብዙኃንም በጥልቀት መታደስ ይኖርባቸዋል። የፐብሊክም ሆነ የግሉ መገናኛ ብዙኃን የህዝብንና የአገርን ጥቅም ታሳቢ ማድረግ ይኖርባቸዋል። ሁለቱም መገናኛ ብዙኃን ከሚያራምዱት ጽንፍ ከወጣ አዘጋገብ ሊታረሙና ወደቀልባቸው ሊመለሱ ይገባቸዋል።

በአዲሲቷ ኢትዮጵያ የሚያስፈልጉን መገነኛ ብዙኃን የመንግሥት ጠንካራ ጎኖች የበለጡ እንዲጎለብቱ በማድረግ እንዲሁም ድክመቶቹንም በአግባብ በመተቸት ማስተካከያ እንዲደረግባቸው በማድረግ የአገራችንን የለውጥ ጉዞ ማፋጠን ነው፡፡ ይህ ሲሆን ነው በጥልቀት መታደስ እውን የሚሆነው፣ የህዝብ ተጠቃሚነትም የሚረጋገጠው። አገርም ወደፊት የምትራመደው።

 

መልካም አስተዳደር እንዲጎለብት፣ ኪራይ ሰብሳቢነት እንዲወገድ፣ ፍትሕ እንዲነግስና የተጀመሩ የልማት ሥራዎች እንዲፋጠኑና አገራችን ወደተሻለ የዕድገት ደረጃ መሸጋገር እንድትችል ሁሉም አገር ወዳድ ዜጋ የበኩሉን አስተዋጽዖ ሊያበረክት ይገባል፡፡ መንግሥት ከላይ ወደታች እንዲሁም ኅብረተሰቡ ከታች ወደላይ በማረቅ ብልሹ አሠራርን መዋጋት አስፈላጊ ነው፡፡ ህዝብና መንግሥት ተቀራርበው በመሥራታቸው በአገራችን በየዘርፉ ተጨባጭ ለውጦች ማስመዝገብ ተችሏል። ይህን ለውጥ ቀጣይነት ለማረጋገገጥ አሁንም ህዝብና መንግሥት የበለጠ ተቀራርበው መሥራት ይኖርባቸዋል።

የአገራችን የዴሞክራሲ ሥርዓት እንዲጎለብትና መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን መንግሥት አሁን በሙስና ፈጻሚዎች ላይ የጀመረውን ርምጃ ኅብረተሰቡ እንዲያግዘውና ቀጥታ ተሳታፊ መሆን ይኖርበታል። ምክንያቱም በመንግሥት ጥረት ብቻ ለውጥ ሊመጣ አይችልምና። ለውጥ ቢመጣም ለውጡ ዘለቄታዊነት ሊኖረው አይችልም። መልካም አስተዳደርም የአንድ ወቅት ሥራ ሊሆን አይችልም። የመልካም አስተዳደር ችግሮች ነገም ተነገ ወዲያም የሚነሳ ችግር እንደሚሆን ታሳቢ ማድረግ ተገቢ ነው። ዋናው ህዝብና መንግሥት በቅርበት በመሥራት ለፀረ ሙስና ትግሉ መፋፋም አፋጣኝ መልስ መስጠት መቻል ነው።

Leave a Comment