ለሀገሪቱ ራዕይ የተጓዝንባቸው መንገዶች

ለሀገሪቱ ራዕይ የተጓዝንባቸው መንገዶች

                                                            ዘአማን በላይ

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ ላይ በተካሄደው 12ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓልን አስመልክተው የአገራችን ህዝቦች አንድ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመገንባት የኢትዮጵያ ህዳሴ ብለው ለጀመሩት የጋራ ፕሮጀክት ስኬታማ ተግባሮችን በማከናወን ረጅም ርቀት ተጉዘዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዕለቱ በፌዴራላዊ ስርዓቱ ሀገራችን የተጓዘችባቸው የስኬት መንገዶችንም አመላክተዋል።

ርግጥ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ ተግባሮች በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና  ማህበራዊ ለውጦች መመዝገብ ችለዋል። መንግስትም በኢኮኖሚያዊና በማህበራዊ መስክ በተለይም የወጣቱን ተጠቃሚነት ማዕከል በማድረግ ፌዴራላዊ ስርዓቱን ያበጀውን የፍትሐዊ ተጠቃሚነት ዕድልን አሟጦ ለመስራት ጥረት እያደረገ መሆኑ ይታወቃል። ያም ሆኖ ባለፉት 23 ህገ መንግስታዊ ዓመታት በሁሉም መስኮች ረጅም ርቀት መጓዛችንን ማንም የሚክደው ጉዳይ አይደለም—“ማየት ማመን ነው” እንዲሉ አበው።

ምንም እንኳን በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች መጠነኛ ግጭቶች ቢከሰቱም ችግሮቹን ፌዴራላዊ ስርዓቱ የፈጠራቸው ካለመሆኑም በላይ፤ በእነዚህ ጥቂት አካባቢዎች የተከሰተው ችግር አጠቃላይ ሀገሪቱን የሚመለከት አይደለም። እናም በእኔ እምነት የዚህ ችግር መፈጠር ሀገራችን ያስቀመጠችውን መካከለኛ ገቢ ያላት ሀገር የመፍጠር ራዕይን የሚያስተጓጉል አይደለም።

ለዚህ አባባሌ ሁለት ምክንያቶችን ማንሳት እችላለሁ። አንደኛው ግጭቶቹን ፌዴራላዊ ስርዓቱ በዘላቂ ሁኔታ የመፍታት አቅምና ብቃት ያለው መሆኑ ነው። ስርዓቱ ላለፉት ዓመታት ግጭቶችን የማስወገድ ተሞክሮን ያዳበረ በመሆኑና የሚፈጠሩ ጊዜያዊ አለመግባባቶችን ማረም የሚችልበት አካሄድ አለው።

እናም ማንኛውም ችግር ቢፈጠር የስርዓቱ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤት የሆኑት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሊፈቱት ይችላሉ— ከህዝብ አቅም በላይ የሚሆን ምንም ዓይነት ጉዳይ ስለሌለ ነው። ሁለተኛው ምክንያቴ ደግሞ ሀገራችን የጀመረችው የሀዳሴ ጉዞ በፅኑ መሰረት ላይ የተገነባ ስለሆነ ነው። የሀገሪቱን ህዳሴ ለማረጋገጥ መንግስትና ህዝቡ ከዛሬ ሰባት ዓመት በፊት የመጀመሪያውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ነድፈው ውጤቶችን ማስመዝገብ ችለዋል። በሁሉም ዘርፎች የተገኙትን አበረታች ውጤቶች ጥቂቶቹን እንዲህ መመልከት እንችላለን።

በመጀመሪያው የዕቅድ ዘመን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገትና የማህበራዊ ልማት ውጤቶችም ተመዝግበዋል። በአጠቃላይ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በየዓመቱ በአማካይ 11 በመቶ አድጓል። መንግስት ይህንን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት በማስቀጠል የምዕተ ዓመቱን የልማት ግቦች ከማሳካት ባሻገር እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር ከ2012 እስከ 2015 ባሉት ዓመታት ሀገሪቱን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ ለማሰለፍ የተቀጠመውን ሀገራዊ ራዕይ እውን ለማድረግ አልሞ ሰርቷል። በዚሁ መሰረት የነበረው ዕቅድ አፈጻጸም በአማካይ ግብርና ስምንት ነጥብ አራት በመቶ፣ ኢንዱስትሪ የ10 በመቶ እና አገልግሎት የ14 ነጥብ ሶስት በመቶ ዓመታዊ ዕድገት አስመዝግበው ኢኮኖሚው 11 በመቶ ዕድገት ማምጣት ችሏል።

ይህም ለሁለተኛው የልማት ዕቅድ መደላድል የፈጠረ ነበር። የመጀመሪያውና ሁለተኛው የማት ዕቅድ ተመጋጋቢነት ያላቸው በመሆኑም በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የሁለት ዓመታት ትግበራ የተሻለ ውጤት ማምጣት ማምጣት እንደሚቻል ከአፈፃፀሙ መረዳት የሚቻል ይመስለኛል።  

በማህበራዊ መስክም የመልካም አስተዳደር ፕሮግራምን በመተግበር የሰው ሃይል ግንባታ፣ የዴሞከራሲያ ስርዓት ግንባታ፣ የህዝብ ተሳትፎን የማስፋትና የማጠናከር የተቀናጀ የተቋም አቅም ግንባታ፣ ግልፅነትና ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ልምድ በመጀመሪያው የልማት ዕቅድ ወቅት ተገኝቷል።

እነዚህን ልምዶች ይበልጥ ቀምሮ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ በሁለተኛው የልማት ዕቅድ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ነው። ከዚህ አኳያ መልካም አስተዳደርን እንደ አንድ አብነት ብንወስድ፤ በሁለተኛው የልማት ዕቅድ ፖለቲካል ኢኮኖሚው ኪራይ ሰብሳቢነት የበላይነት ከያዘበት ወደ ልማታዊነት የበላይነት ወደ ያዘበት እንዲሸጋገር ጥረት እየተደረገ ነው። በአንድ ወገን ልማታዊነትን የሚያጐለብቱ ድጋፎችን በጥራት በማቅረብ፣ በሌላ በኩል የኪራይ ሰብሳቢነት ዋነኛ ምንጭ ሆነው የተለዩትን ጉዳዮች በልዩ ትኩረት በማድረቅ ኪራይ ሰብሳቢነት፣ ሙስና እና ብልሹ አሰራሮችን በቁጥጥር ሥር በማዋል ልማታዊነት የበለጠ እንዲጐመራና የአንበሳውን ድርሻ እንዲይዝ ለማድረግ መንግስትና ህዝብ እየሰሩ ነው። ይህም መልካም አስተዳደርን ዕውን ከማድረግና በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ እጅግ ወሳኝ ድርሻ ይኖረዋል።

በዚህ መሰረትም በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ መንግስትና ህዝብ በወሰዷቸው የጋራ አቋሞች ጥልቅ ተሃድሶ በመላ ሀገሪቱ እየተካሄደ ነው። ይህ የጥልቅ ተሃድሶ ሂደት ከአንድ ዓመት በላይ ያስቆጠረ ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ በርካታ ጉዳዩች ተከናውነዋል። ህዝብ፣ ገዥው ፓርቲና መንግስት ባካሄዷቸው የተለያዩ መድረኮች ከመልካም አስተዳደር አኳያ አላላውስ ያሉ ማነቆዎችን እየቀረፉ ነው።

ህዝቡ በየደረጃው የመንግስትን ስልጣንን ለግል መጠቀሚያ ያደረጉ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮችን እንዲሁም በህብረተሰቡ ውስጥ የተሰገሰጉ ጥገኞችን በአስተዳደራዊና በህግ አግባብ ጥጋቸውን በማስያዝ ላይ ይገኛሉ። ምንም እንኳን ብዙ የሚቀሩ ጉዳዩች ቢኖሩም፣ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ማህበራዊ ዘርፎች የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ለውጦች የጥልቅ ተሃድሶ ለውጦች መሆናቸውን መገንዘብ የሚቻል ይመስለኛል።   

ርግጥ አሁንም ቢሆን የዕቅዱን ትልም ዕውን ለማድረግ የፖለቲካ አመራሩና የፐብሊክ ሰርቪስ ሠራተኛው ከህዝቡ ጋር በተደራጀ መንገድ በመቀናጀት ይበልጥ መስራት ይጠበቅባቸዋል። ለዚህ ደግሞ ‘ይህ ስራ የእገሌ ነው’ ሳይባል ሁሉም የበኩሉን ገንቢ ሚና መጫወት አለበት። ሀገራችን አረጋግጠዋለሁ ብላ ለተነሳችው የህዳሴ ጉዞ ትልልቆቹ አደጋዎች ከሚባሉት ውስጥ ሙስና እና ኪራይ ሰብሳቢነት በመሆናቸው አደጋዎቹን ለመዋጋትና ትግሉን በልማታዊና ዴሞክራሲያዊ እሳቤ የበላይነት ለመደምደም በርካታ ስራዎችን ማከናወን የግድ ማለቱ አይቀሬ ነው።

ያም ሆኖ ግን ስለ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ስኬቶቻችን ስናወሳ፤ እዚህ ሀገር ውስጥ አስተማማኝና ዘላቂ ሰላም መፈጠር እንዳለበት ሊዘነጋ አይገባም። ሰላም ከሌለ ስለ የትኛውም የልማት ስኬት ማውጋት አይቻልም— ሰላም የሁሉም ሀገራዊ ጉዳዩች ማጠንጠኛ ነውና። ይህ በመሆኑም መንግስትና ህዝቡ ባለፉት ዓመታት በመላ ሀገሪቱ አስተማማኝና ዘላቂ ሰላምን በማስፈን ረገድ ብዙ ርቀት ተጉዘዋል። ኢትዮጵያ ሰላም በመሆኗም ኢኮኖሚዋ የሌሎች አፍሪካ ሀገራት ምሳሌ ሆኗል፤ በርካታ የውጭ ባለሃብቶችን በመሳብ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እየሆነች ነው፤ የቱሪዝም ሃብቷን በአግባቡ እየተጠቀመች የውጭ ምንዛሬ እያገኘችም ነው። ከሁሉም በላይ የሀገሪቱ ህዝብ የሰላም አየርን መተንፈስ ችሏል። ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በ12ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ላይ “…በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች መጠነኛ ግጭቶች ቢስተዋሉም፤ ህዝቡ የሰላም አየር የሚተነፍስባት ጠንካራ ሀገር መመስረት ተችሏል” በማለት የገለፁት ከዚህ እውነታ በመነሳት ይመስለኛል።

ርግጥ ግጭት በየትኛውም ሀገር ውስጥ ሊኖር ይችላል። ሆኖም ግጭቱ ዘላቂ እንዲሁም የሀገርንና የህዝብን ራዕይ ማስተጓጎል የለበትም። አይገባውም። እስካሁን ድረስ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድም፤ ያለፉት ስርዓቶች ጥለውት በሄዱት ፀረ-ዴሞክራሲያዊ አመለካከቶች፣ ሁለትም፤ የመንግስትን ስልጣን ለግል መጠቀሚያ በማድረግ ህዝቡን በሚያስመርሩ አካላት፣ ሶስትም፤ ኪራይ ሰብሳቢዎች፣ ጠባቦች፣ ትምክህተኞችና ኮንትሮባንዲስቶች በሚፈጥሩት ችግር ሳቢያ የህዝብ ብሶት ገንፍሎ ግጭት ሊከሰት ይችላል። ሆኖም ይህ ግጭት ዘላቂ እንዳይሆን ማድረግ ተችሏል። ያም ሆኖ ግን አሁንም በዚህ ረገድ ጠንክሮ መስራትን ይጠይቃል። ምክንያቱም ግጭትን ይዞ፣ የሀገር ራዕይን ለማሳካት መሞከር ያለንን አቅም በልማት ላይ እንዳናውል ስለሚያደርገን ነው።

ሆኖም እዚህና እዚያ የሚታዩት ግጭቶች በፌዴራላዊ ስርዓቱ መፍትሔ እንደሚያገኙ ታሳቢ ሆኖ፤ አሁንም ቢሆን በኢትዮጵያ ውስጥ አስተማማኝ ሰላም እየተገነባ መሆኑን መካድ አይቻልም። ምክንያቱም በሀገሪቱ እየተመዘገበ ላለው ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት ሰለማችን የማይተካ ሚና እየተጫወተ ስለሆነ ነው።

በጥቅሉ የሀገሪቱን ራዕይ ለማሳካት መንግስትና ህዝብ ረጅም ርቀት ተጉዘዋል። ጉዞው ምንም እንኳን አልጋ በአልጋ ባይሆንም፤ ራዕያችን መሳካቱ ግን አይቀሬ ነው። የትኛውም ሀገር ያለ ችግርና ውጣ ውረድ የስልጣኔ ማማ ላይ እንዳልወጣ ሁሉ፤ ሀገራችንም የችግሮችን ስንክሳሮች አስወግዳ ህዳሴዋን በማጋገጥ እንደምታሳካ በርግጠኝነት መናገር የሚቻል ይመስለኛል።      

Leave a Comment