ህግና የበላይነቱ

ethiopia

የአገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የቃል ኪዳን ሰነድ የሆነው የኢፌዴሪ ህገ መንግስት ከህግ የበላይነት አኳያ መርሆዎችን አስቀምጧል። በዚህም ኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉም ሰው ያለ አንዳች መብለጥም ይሁን ማነስ በህግ ፊት እኩል ሆኗል። እናም በዛሬዋ ኢትዮጵያ ውስጥ የህግ የበላይነት ለድርድር የማይቀርብበት ደረጃ ላይ መድረስ ተችሏል።
በየትኛውም አገር ውስጥ የህግ የበላይነት ልዕልናው ካልተረጋገጠ ስርዓተ አልበኝነት ቦታውን ይረከባል። የህግ የበላይነት ከሌለ ስርዓተ አልበኝነትን የሚፈጥር ከመሆኑም ባሻገር፤ ህጎች ለሁሉም ዜጎች እኩል እንዳይሰሩ ያደርጋል። እናም ‘ሁሉም ሰው በህግ ፊት እኩል ነው’ የሚለውን ህገ መንግስታዊ መርህ ገቢራዊ ለማድረግ የህግ የበላይነት በማያሻማ ሁኔታ መረጋገጥ ይኖርበታል።
የህግ የበላይነት መከበር ለሀገር ሰላምና መረጋጋት ብሎም ልማትን ለማሳለጥ ቁልፍ ሚና ይኖረዋል። የህግ የበላይነት ከሌለ ሰላም የሚባልን ነገር ማሰብ አይቻልም። ሰላም ከጠፋ ደግሞ ስለ ልማትና ዴሞክራሲ ማሰብ አዳጋች ነው፤ ፀረ-ልማትዊነትና ፀረ-ዴሞክራሲያዊነት ቦታውን ይረከባሉ። ይህ ሁኔታ ደግሞ እንደ እኛ ሰላምን፣ ልማትንና ዴሞክራሲን የህልውናው ጉዳይ ላደረገ አገር አሜኬላ እሾህ መሆኑ አያጠያይቅም።
በእርግጥ ኢትዮጵያ የጀመረችው የዕድገትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ባህል ግንባታ ሂደት ስኬታማ ሆኖ እንዲቀጥል፤ አስተማማኝ ሰላም የሰፈነበት ምህዳርን መፍጠር የግድ ነው። ምክንያቱም አገራችን ፈጣን ልማትን ማምጣትና ከተመፅዋችነት መላቀቅ ብሎም ዴሞክራሲን መገንባት የሞት ሽረት ያህል የህልውና ጉዳይ አድርጋ ስለያዘችው ነው። ሰላምን በማረጋገጥ ሂደት ውስጥ ለብሔራዊ ደህንነቷ ስጋት የሆኑ እንቅስቃሴዎችን መከላከልና መቆጣጠር ያስችላት ዘንድ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ይኖርባታል።
“የእኩልነት መብት” በሚለው የህገ መንግስቱ አንቀፅ 25 ላይ፤ “ሁሉም ሰዎች በህግ ፊት እኩል ናቸው፤ በመካከላቸውም ማንኛውም ዓይነት ልዩነት ሳይደረግ በህግ እኩል ጥበቃ ይደረግላ ቸዋል።…” በሚል የተደነገገው ጉዳይም ዜጎች መብቶቻቸው ሳይሸራረፉ በህግ የተጠበቁ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ነው።
በህግ ፊት እኩል መሆን የተቃዋሚንም ይሁን የደጋፊን እንቅስቃሴ አይገድብም። ሁሉም ዜጋ በአንድ ዓይነት እንዲታይ ያደርጋል። ምክንያቱም ህገ መንግስታዊ ድንጋጌ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል የሚመለከት ስለሆነ ነው። እናም እዚህ አገር ውስጥ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ያለአንዳች ስጋት እንዲንቀሳቀስ የሚፈቅድ መሆኑን መገንዘብ ይገባል።
የህግ የበላይነት ልዕልና ካልተጠበቀ በአገሪቱ የሚረቀቁ ማናቸውም ህጎች በሚፈለገው መጠን ገቢራዊ ሊሆኑ አይችሉም። ህጎች በሚፈለገው መጠን ገቢራዊ ካልሆኑና በቸልታ የሚታለፉ ከሆኑ የዜጎች መብቶች ሊሸራረፉ ይችላሉ። የመብት መሸራረፎች ደግሞ ህገወጦች እንዳሻቸው እንዲፈነጩ እድል ይፈጥራል። በዚህም ህግና ስርዓትን የሚያከብረው ዜጋ ህገወጦችን በመመልከት ወደ ተሳሳተ መንገድ ሊያመራ ይችላል። በመሆኑም ይህን ችግር ለመቅረፍም የህግ የበላይነት ልዕልና ገቢራዊ መሆን አለበት። በመሆኑም ህግና ስርዓትን የማስከበር ተግባር በህግ አስፈፃሚው አካል በሚፈፀምበት ወቅት የተለየ ትርጓሜ ሊሰጠው አይገባም።
በህገ መንግስታችን ላይ በግልፅ እንደተደነገገው፤ ማንኛውም ሰው በህግ ፊት እኩል ነው። በመሆኑም ማንኛውም አዋጅ ሲወጣ ሁሉንም ዜጋ ይመለከታል እንጂ ለተለየ የህብረተሰብ ክፍል ተለይቶ አይደለም። እናም ፖለቲከኛውም፣ ሙዚቀኛውም፣ መሃንዲሱም፣ ሀኪሙም፣ ቀዳሹም ሆነ ተኳሹ…አገሪቱ ያወጣችውን ህግ የማክበርና በእርሱም የመመራት ግዴታ አለበት።
አንድ ግለሰብ ባለሙያ አሊያም የተቃዋሚ ፓርቲ ስለሆነ ሙያውን ወይም የተቃዋሚ ፓርቲ አባልነቱን እንደ መከላከያ ምሽግ በመጠቀም ህገ ወጥ ተግባርን መፈፀም የህግ የበላይነት ገቢራዊ እንዳይሆን የሚያግድ አይደለም።
እንደሚታወቀው ሁሉ ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ አሁን በስራ ላይ ላለው ህገ መንግስትና አገራችን ለምትከተለው ህገ መንግስታዊ ስርዓት እውን መሆን መታገሉ፤ ማታገሉና በሂደቱም መስዋዕትነት መክፈሉ የሚካድ አይደለም። በዚህም ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ከአምባገነኑ ፀረ- ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የአፈና አገዛዝ አላቅቋል። በአገራችን የፀረ- ዴሞክራሲ ኢኮኖሚያዊ መሰረትን ንዷል፣ የብሔራዊ ጭቆናን ተቋማዊና መዋቅራዊ እንዲሁም ድርጅታዊና ርእዮተ ዓለማዊ መሰረቶች ከመሰረ ታቸው እንዲመነገሉ አድርጓል።
ከዚህ በተጨማሪ የግልና የቡድን መብቶችን ያጣመረ ዴሞክራሲን መገንባት ችሏል። እነዚህና ሌሎች ዓለም አቀፍ የዴሞክራሲያዊና የሰብአዊ መብት እምነቶች ለህዝብ ቀርበው እስከ ታች ድረስ የወረደ ሰፊ ውይይት ተካሂዶባቸው ማሻሻያ ከተደረገባቸው በኋላ፤ በህገ መንግስትነት እንዲፀድቁና ህዝቡ በፍላጎቱ እውን እያደረጋቸው እንዲመጣ አድርጓል።
ይህም ዴሞክራሲያዊው ስርዓት እንዲፈጠር ገዥው ፓርቲ የመሪነት ሚናውን በብቃት ቢወጣም፤ በስተመጨረሻም የህገ መንግስቱ ባለቤት ህዝቡ መሆኑን በግልፅ የሚያስረዳ ዕውነታ ነው።
በህገ መንግስቱ መሰረት በሚካሄዱ ምርጫዎች ህዝቡ ድምፅ የሚሰጠው ህገ- መንግስቱን ለሚንከ ባከብለትና ለሚጠብቀው ኃይል መሆኑ በአምስት ተከታታይ የምርጫ ጊዜያት ታይቷል። ይህም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች አምነውበትና ተስማምተውበት ያፀደቁትን ዴሞክራሲያዊ ህገ መንግስት የትኛውም ኃይል እንዲነካባቸው የማይፈልጉ መሆኑን የሚያሳይ ሃቅ ነው። እነዚህ ሃቆች ገቢራዊ እንዲሆኑ የህግ የበላይነት በአግባቡ ስራ ላይ መዋል ይኖርበታል።
እንደሚታወቀው በህግ ካልተደነገገ በስተቀር በየትኛውም አገር ውስጥ የሚኖር ዜጋ የህግ የበላይነትን በመፃረር እንዳሻው ሊኖር አይችልም። የዜጎች ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ በህግና ስርዓት የሚመራ ካልሆነ የትኛውም ወገን የመኖር ዋስትና ሊኖረው አይችልም። በመሆኑም ማንኛውም ዜጋ የሚንቀሳቀሰው ህግ ባለበት አገር ውስጥ ነውና ህገ-ወጥ ተግባርን ከከወነ የህግ የበላይነት ተፈፃሚ ይሆንበታል።
የትኛውም አካል ህገ መንግስቱ ላይ ከተደነገገው ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ውጪ ነፍጥ አንግቦ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመጣል የሚያደርጋቸው ማናቸውም ተግባራት ህገ ወጥ ናቸው።
በመሆኑም ከህገ መንግስቱ አኳያ በዚህ ተግባር ላይ የተሰለፉ ማናቸውም የፖለቲካ አሊያም የሽብር ድርጅቶች ህገ ወጥ ሆነው በአገራችን የህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት ተፈርጀዋል። ከእነርሱም ጋር የሚደረግ ማናቸውም ግንኙነት ወይም የእነርሱን አጀንዳ በማራመድ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ለመናድ የሚደረጉ ጥረቶች የህግ የበላይነትን መፃረር ነው። ስለሆነም ለህግና ለበላይነቱ መትጋት የራስን ህገ መንግስታዊ መብቶች ማስከበር ስለሆኑ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል።

ዳዊት ምትኩ

Leave a Comment