ህዝብን ከህዝብ ጋር በማጋጨት ማን ይጠቀማል?

ህዝብን ከህዝብ ጋር በማጋጨት ማን ይጠቀማል? (ዘአማን በላይ)

ይህን ፅሑፍ ለማዘጋጀት ምክንያት የሆነኝ ከመሰንበቻው በአይጋ ፎረምና በአንዳንድ መሰል ድረ ገፆች ላይ የቀረበ አንድ የእንግሊዝኛ ፅሑፍ ነው። ፅሑፉ በቅርቡ በኢትዮጵያ ሶማሌና በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥታት የተወሰኑ አዋሳኝ የድንበር አካባቢዎች የተከሰተን ግጭት መነሻ በማድረግ የተሰናዳ ነው —“SHEDDING LIGHT ON THE RECENT VIOLENCE IN THE BORDER AREAS BETWEEN SOMALI AND OROMIA REGIONS OF ETHIOPIA” በሚል ርዕስ። የፅሑፉ ባለቤት ራሳቸውን “ገለልተኛ አጥኚ ነኝ” በማለት ያስተዋወቁንና ችግሩ በተከሰተባቸው አንዳንድ ቦታዎች ተዘዋውረው ሁኔታውን እንደተመለከቱ እንዲሁም ያገኟቸውን የየአካባቢዎቹን ነዋሪዎች ቃለ መጠይቅ እንዳረጉ የገለፁልን አቶ ኢስማኤል መሐመድ አብዲ የተባሉ ግለሰብ ናቸው።

ፀሐፊው በፅሑፋቸው ላይ ያሰፈሯቸው ሃሳቦች የአገራችን ህዝቦች ላለፉት 26 ዓመታት ያህል የተጎናፀፏቸውን የመቻቻል፣ የመከባበርና በሠላም አብሮ የመኖር ትሩፋቶችን ከመጋፋት ባለፈ፤ የፅንፈኛ ኃይሎች ማራገቢያ ሆኖ ለዘመናት በአንድነት የኖሩትን የሁለቱን ወንድማማች ክልል ህዝቦች በማጋጨት ቅራኔ ለመፍጠር ያለሙ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ። እናም የፅሑፉ አነሳሽ ምክንያትና አገራዊ አንድምታው በቅጡ የተጤነ ነው ለማለት የሚያስደፍር አይደለም። ለዚህም ነው—በፅሑፌ ርዕስ ላይ “ህዝብን ከህዝብ ጋር በማጋጨት ማን ይጠቀማል?” የሚል ጥያቄ ያነሳሁት። ምንም እንኳን የዚህን ጥያቄ ምላሽ በስተመጨረሻ ላይ የምመለስበት ቢሆንም፤ በቅድሚያ ግን የፀሐፊውን ሃሳብ በምን ሁኔታ ለመሞገት እንደፈለግኩ መግለፅ ተገቢ መስሎ ይታየኛል።

እርግጥ የፅሑፉ ባለቤት አቶ ኢስማኤል ያሻቸውን ዓይነት ሃሳብ በመያዝ በፈለጉት ዓይነት የመገናኛ ብዙሃን መንገድ ሃሳባቸውን በነፃነት የመግለፅ ህገ መንግሥታዊ መብት እንዳላቸው እገነዘባለሁ። ይህ መብታቸው ዴሞክራሲያዊ መሆኑን ስለማውቅም ሃሳባቸውን አከብራለሁ። ፅሑፉን በገፆቻቸው ላይ ያሰፈሩት አይጋ ፎረምን ለመሳሰሉ ድረ ገፆች የኤዲቶሪያል አሠራር ነፃነት (Editorial Independence) ያለኝ አክብሮትም የላቀ ነው። አዎ! የፀሐፊውንም ይሁን የድረ ገፆቹን ህገ መንግሥታዊ፣ ተቋማዊና ሙያዊ መብቶችን እየተጋፋሁ አይደለም። በአዲሲቷ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ውስጥ እየኖርኩ መብቶቹን የመጋፋት ቅንጣት ያህል መብትም የለኝም። ያም ሆኖ ግን፤ እኔም እንደ ማንኛውም ዜጋ በአንድ ጉዳይ ላይ የተሰማኝን ሃሳብ የመያዝና የመግለፅ ህገ መንግሥታዊ መብት እንዳለኝ እገነዘባለሁ። ይህን መብቴንም አግባብ ባለው ሁኔታ መጠቀም እንዳለብኝም አምናለሁ። እናም በእኔ እምነት በአቶ ኢስማኤል ፅሑፍ ላይ ‘የተሳሳተ፣ ለአገራችን ሠላምና መረጋጋት ብሎም ለህዝቦች ዘላቂ ሠላም አይጠቅምም’ ብዬ ያመንኩበትን ጉዳይ በዚህ ፅሑፍ ላይ ለማራመድ የምፈልገው ከዚህ መሠረታዊ እውነታ በመነሳት መሆኑን ፀሐፊውም ይሁኑ አንባቢያን ይገነዘቡልኝ ዘንድ እሻለሁ።

ታዲያ በእኔ እምነት ግለሰቡ ያስነበቡን ፅሑፍ ራሳቸውን ካስተዋወቁበት የገለልተኛ አጥኚነት ስብዕናቸው ጋር ፈፅሞ የሚሄድ ሆኖ አላገኘሁትም። ምክንያቱም የአቶ ኢስማኤል ፅሑፍ በአንድ በኩል ኦሮሚያንና ክልሉን በመምራት ላይ የሚገኘውን የኦሮሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (OPDO) የማብጠልጠል፤ በሌላኛው ዘውጉ ደግሞ “የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ”ን በማንቆለጳጰስ ላይ የተመሠረተ ሆኖ ስላገኘሁት ነው። ፅሑፉ አንዱን አወዳሽ፣ ሌላኛውን ነቃሽ ሆኖ በህዝቦች መካከል አለመተማመንን በመፍጠር የግጭት እሣትን ለመለኮስ ያሰበ መሆኑንም ጭምር ተገንዝቤያለሁ።

ከዚህ በተጨማሪ፤ ፅሑፉ ባለፉት ጥቂት ወራቶች ውስጥ በሁለቱ ተጎራባች ወንድም ህዝቦች አንዳንድ የድንበር አካባቢዎች የተፈጠረው ግጭት በፌዴራላዊ ሥርዓታችን ውስጥ በምን ዓይነት መንገድ እልባት ሊያገኝ እንደሚችል በሰከነ ሁኔታ ከማሳየት ይልቅ፤ ኃላፊነት በጎደለው መልኩ ልዩነቶችን በማጎን በህዝቦች መካከል መቃቃርን በመፍጠር ችግሩን ለማባባስ ያለመ ይመስለኛል። በህዝቦች ወቅታዊ ችግር ላይ ተንተርሶ ግጭቱን በአስገራሚ ሁኔታ “የውክልና ጦርነት” (Proxy War) ብሎ እስከ መፈረጅ፣ ያለውን አነስተኛ የስፋት መጠን እጅግ እስከ መለጠጥ እንዲሁም ሁሌም የአገራችንን ሠላምና መረጋጋት ማየት ለማይሹ አንዳንድ ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች፣ የከሰሩ ፖለቲከኞችና ፅንፈኛ ኃይሎች አጀንዳ እስከ መስጠት ድረስ የዘለቀ በመሆኑም፤ በተፈጠረው ጊዜያዊ ችግር ላይ “ቤንዚን የማርከፍከፍ” አካሄድን የተከተለ ነው። ፈረንጆቹ “adding fuel into the fire” እንደሚሉት ዓይነት።

ግጭቱ በሁለቱም ወገኖች ጥቂት ታጣቂዎችና አመራሮች አጋጣሚዎችን ተገን አድርገው በፈጠሩት ችግር ሣቢያ የተከሰተ እንጂ፤ በሁለቱ ክልል መንግሥታት አሊያም በኢትዮጵያ ሶማሌም ይሁን በኦሮሚያ ህዝቦች መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ምክንያት ያልተከሰተ መሆኑ እየታወቀ፤ ፀሐፊው ጉዳዩን የብሔር ቅርፅ ለማስያዝ መሞከራቸው ምን ያህል አደገኛና ኃላፊነት የጎደለው አቀራረብ መከተላቸውን የሚያሳይ ነው።

ይህን መሰሉ የህዝቦችን መቀራረብና ፍቅር ብሎም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን የሚንድ ፅሑፍ በተለያዩ ወቅቶች ጠንካራ አገራዊና ቀጣናዊ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ገንቢ ዘገባዎችንና ትንታኔዎችን በጥልቀት ከሽነው በማቅረብ በሚታወቁት እንዲሁም የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መገለጫ ሊሆኑ ይችላሉ ብዬ በማስባቸው አይጋ ፎረምን በመሳሰሉ ድረ ገፆች ላይ መቅረቡ ደግሞ፤ ከአቶ ኢስማኤል ፅሑፍ አኳያ ድረ ገፆቹ እንደ ማንኛውም የሚዲያ ተቋም ያለባቸውን ማህበራዊ ኃላፊነት (Social Responsibility) በአግባቡ እንዳይወጡ አድርጓቸዋል። እንዲሁም እንደ እኛ ያለ ከድህነት አረንቋ ለመውጣትና የነገ ህዳሴውን ዕውን ለማድረግ በመታተር ላይ ያለ ህዝብ በአስተማማኝ ሠላም ውስጥ ልማቱን እንዲያፋጥን ከሚደግፈው የሠላም ጋዜጠኝነት (Peace Journalism) መርህ አኳያ ቀደም ሲል በአብዛኛው መልኩ ይከተሉት የነበረውን ሚዛናዊ አሠራር የሸራረፈባቸው ይመስለኛል። እናም ይህን መሰሉ የህዝብንና የአገርን ጥቅም ሊያስጠብቅ የማይችል ፅሑፍን በድረ ገፅ ላይ አትሞ ከማውጣት በፊት አዎንታዊና አሉታዊ ጎኖችን በሚገባ ማጤን ተገቢ ነበር እላለሁ።

ከዚህ ጥቅል እሳቤዬ ወደ አቶ ኢስማኤል ፅሑፍ ስመለስ፤ ግለሰቡ በፅሑፋቸው ላይ “ገለልተኛ አጥኚ ነኝ” ብለው ሲያበቁ፣ በተጨባጭ ሃሳባቸው ግን የክልሎቹን ህዝቦች ቀደምት ትስስር ተገቢ ያልሆነ ቦታ ላይ በማከክ ጭምር የተከተሉትን እንዲሁም ለየትኛውም ወገን የማይጠቅመውንና ውኃ የማይቋጥረውን የአንድ ወገን አራጋቢነት ሚናቸውን አልደግፈውም። እናም ‘ይኼኛው ወገን ትክክል ነው፣ ያኛው ወገን ደግሞ ተሳስቷል’ የሚል ብያኔ ለመስጠት አልሻም። ‘የእገሌ ኃይል እንዲህ ነው፣ የእገሌ ደግሞ እንዲያ ነው’ በማለት ማስረጃ አልባ ጉዳይን ለመግለፅም አይዳዳኝም። ግለሰቡ በፅሑፋቸው ላይ ያነሷቸውንና ‘የተሳሳቱ ናቸው’ ብዬ የማምንባቸውን ጉዳዩችንም በፅሑፌ ውስጥ ለመድገም ፍላጎቱም ይሁን ተነሳሽነቱ የለኝም—በእርሳቸው የሚጎረብጥ መንገድ ላይ ከወዲያ ወዲህ መመላለስ ይሆንብኛልና። እናም የፅሑፌ ዕይታ፤ ‘የፀሐፊው ምልከታ ምን ያህል ለአገርና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ይጠቅማል?’ የሚል መነሻና መድረሻ ብቻ ያለው መሆኑ እርሳቸውን ይሁኑ አንባቢያን ግንዛቤ እንዲይዙልኝ እፈልጋለሁ።

ያም ሆነ ይህ፤ አንድ ራሱን “ገለልተኛ አጥኚ ነኝ” በማለት ለአንባቢ ያስተዋወቀ ፀሐፊ፤ እያነሳ በሚጥላቸው የሃሳብ ሰበዞች ውስጥ የገለልተኛ አጥኚ መስፈሪያዎች ሊኖሩት ይገባል። በመሆኑም ገለልተኛው አጥኚ ጥናቱን ሲያካሂድ የተጠቀማቸው ሣይንሳዊ አካሄዶች፣ የወካይ ናሙና አሰባሰብ መንገዶቹ፣ ወካይ ናሙናዎቹን በምን ዓይነት ስብጥር እንደተጠቀመባቸው፣ የጥናቱ ወጥነት፣ ቦታና በግብዓትነት የተጠቀማቸው ሰዎች ስም ዝርዝር ወዘተ… የመሳሰሉ ጉዳዩችን በመግለፅ የጥናቱን ተዓማኒ ማረጋገጥ ይጠበቅበታል። ሆኖም ፀሐፊው እነዚህን ሣይንሳዊ ሁኔታዎች በማሳየት በአንባቢያን አዕምሮ ውስጥ ሚዛናዊ፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ልኬታን የሚያስጠብቅና ከሳች ምስል ለመፍጠር ከመሞከር ይልቅ፤ የራሳቸውን ወገንተኛ ስሜት በአገራዊ ተረትና ምሣሌዎች እየለወሱ ለማቅረብ ነው የሞከሩት። ይህ ደግሞ ‘በገለልተኝነት እወቁኝ’ ካሉ ፀሐፊ የሚጠበቅ ምሁራዊ ተግባር አይመስለኝም። ፀሐፊው የሃሳብ ነቁጦች በአንባቢው ዘንድ ዓይነ-ግቡ እንዳይሆኑና ተዓማኒነትንም እንዲያጣ ምክንያት የሚሆንም ይመስለኛል። የእሳቤው ማኅበረሰባዊ ፋይዳም፤ ዳር ቆሞ ግጭትን ለማባባስ በረጅም የነገር እንጨት እሣት ለመቆስቆስ ታስቦ ካልሆነ በስተቀር ‘እንዲህ ነው’ ተብሎ ሊገለፅ የሚያስችል ፈር ያለው መያዣ የለውም። የፅሑፉ አልፋና ኦሜጋ ግብ አንድን ህዝብ ከሌላው ጋር ማጋጨት የሁለቱን ህዝቦች የዘመናት ግንኙነት በማሻከር ጥላሸት ለመቀባት ያለመ ነው ማለት ይቻላል።

እርግጥ ግጭት በየትኛውም ማኅበረሰብ ውስጥ ያለ ነባራዊ ክስተት ነው። ክስተቱ ሰሜን አሜሪካም ይሁን አፍሪካ፣ አውሮፓም ይሁን ላቲን አሜሪካ…የሰው ልጅ ማህበራዊ መስተጋብር እስካለ ድረስ በየትኛውም የዓለማችን ክፍል ውስጥ መኖሩ አይቀሬ ነው። ለነገሩ የሰው ልጅ ከራሱ፣ ከቤተሰቡ፣ ከማኅበረሰቡ አሊያም ከተፈጥሮ ጋር መጋጨቱ ትናንት የነበረ፣ ዛሬም ያለና ነገም የሚኖር ክስተት ነው። እንኳንስ በአንድ ቤተሰብ፣ ቀዬ፣ መንደር፣ አካባቢ፣ አገር፣ አህጉርና ዓለም ውስጥ የተለያዩ የተፈጥሮ ፀጋዎችን በጋራ እየተጠቀመ “አንተ ትብስ፣ አንቺ ትብሽ” በሚል መተሳሰብ ውስጥ የሚኖረው የሰው ልጅ ቀርቶ፤ ወንዝ ውስጥ የሚኖሩ ሁለት ግዑዛን ድንጋዩችም ቢሆኑ በተፈጥሮ ዑደት መዘውር ሂደት ውስጥ ሊጋጩ ይችላሉ። እናም “መጋጨት” ባህሪያዊ የተፈጥሮ ህግ ነው ቢባል ከእውነታው ብዙም መራቅ አይመስለኝም። ዋናው ቁም ነገር የግጭቱን መንስዔ አጥርቶ ከማወቁ ላይ ነው። መንስዔው ምናልባትም ዓለማችንን በአያሌው እየፈተናትና እየናጣት ያለው የተፈጥሮ ሃብቶች እጥረት (Scarcity of Natural Resources) አሊያም በህዝቦች መካከል ለዘመናት ተጠብቆ የቆየውን በሠላም አብሮ የመኖር ውድ እሴትን ጥቂቶች ከራሳቸው ጥቅም አኳያ በመመዘን የሚፈጥሩት ፍላጎት ሊሆን ይችላል።

ታዲያ ይህን እውነታ ወደ አገራችን በተለይም ወደ ከሁለቱ ተጎባራች ክልሎች አኳያ ስንመለከተው፤ ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ግጭቱ በጥቂት ታጣቂዎች ችግር ምክንያት የተፈጠረ ሆኖ እናገኘዋለን። በዚህም ምክንያት በሁለቱም ወገኖች ውስጥ ያሉ ትጥቅ የያዙና ጥቂት የራሳቸውን ፍላጎት ለማሳካት የሚሹ አመራሮች በድንበር ማካለል ሰበብ የሠላም ጠንቅ ሆነዋል።

ምንም እንኳን እንደ እኛ ባለ ራሱን በራሱ በሚያርምበትና የአሠራር ሥርዓት በተዘረጋበት ፌዴራላዊ ሥርዓት አገር ውስጥ ከድንበር ማካለል ጋር ተያይዞ ሊፈጠር የሚችል ግጭት ሊኖር ባይችልም፤ በሁለቱም ወገኖች ውስጥ ያሉ ጥቂት በአመራር እርከኖች ላይ የሚገኙ ግለሰቦች በግጭቱ ውስጥ መሳተፋቸው አይታበይም። ለዚህም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር  ኃይለማርያም ደሣለኝ በቅርቡ “ማርች 8”ን አስመልክተው ከሁሉም የአገራችን ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ከተውጣጡ ሴቶች ጋር ባደረጉት ውይይት፤“…የድንበር መካለል ለግጭት መከሰት መንስዔ ሊሆን አይችልም። በቅርቡ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች ወሰን አካባቢ የሚኖሩ ህዝቦች እሴቶቻቸውን ጠብቀው ለዘመናት በሠላም የኖሩ ቢሆንም፤ በክልሎቹ አንዳንድ የአመራር አባላት የተሳሳተ አመለካከት ምክንያት ግጭት ውስጥ ገብተዋል።…” ያሉትን እውነታ በዋቢነት መጥቀስ የምችል ይመስለኛል። ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ የሚያመላክተው ነገር ቢኖር፤ “ገለልተኛው” አቶ ኢስማኤል እንዳሉት የአንድ ወገን የነገር ቁርቋሶ ሳይሆን፣ ትክክል ባልሆነ አስተሳሰብ ምክንያት ጥቂት በየደረጃው የሚገኙ የሁለቱም ወገን አመራሮች በግጭቱ ውስጥ ተሳታፊ መሆናቸውን ነው። ያም ሆኖ መንግሥት ሁኔታውን በህገ መንግሥቱ መሠረት በመከታተል ግጭቱን በማራገብ በግንባር ቀደም ተዋናይነት ሆነው የተሰለፉ አካላትን ለይቶ ተገቢውን ርምጃ ለመውሰድ ዝግጅት ማጠናቀቁ ተነግሯል።

እርግጥ ፌዴራላዊ ሥርዓቱ በአጎራባች ክልሎች ውስጥ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት የሚከተለው የራሱ መንገድ አለው። ለነገሩ አገራችን ለፌዴራላዊ የመንግሥት ሥልጣን አወቃቀር ጀማሪ በመሆኗና ባለፉት ፊውዳላዊና አምባገነናዊ ሥርዓቶች ውስጥ የግፍ ቀንበር ተጭኖበት የነበረው የአገራችን ህዝብ ከፌዴራላዊ ሥርዓቱ ለጋነት አኳያ ያለው ግንዛቤ በሚፈለገው መጠን ያልዳበረ በመሆኑ በተለያዩ አካባቢዎች ሊፈጠሩ የሚችሉ ተግዳሮቶች መኖራቸው አይቀርም። ሆኖም ተግዳሮቶቹ ሥርዓቱ ራሱን በራሱ እንዲያርም እንዲሁም ከችግሮቹ ትምህርትና ተሞክሮ በመውሰድ እንዲጎለብት የሚያስችለው እንጂ፤ አቶ ኢስማኤል በአገም ጠቀም የአፃፃፍ ዘዴ እንደገለፁት በብሔር ላይ የተመሠረተ ፌዴራላዊ ሥርዓት በመሆኑ ለግጭት መንስኤዔ ስለሆነ አይደለም። ፌዴራላዊ ሥርዓቱ ለአገራችን ህዝቦች የመቻቻልና የአብሮነት ዋስትና እንጂ የልዩነትና የግጭት መንስዔ ሊሆን አይችልም። “ለምን?” ከተባለ፤ ፌዴራላዊ ሥርዓቱን የዛሬ 22 ዓመት ገደማ በራሳቸው ፈቃድ አንድ የጋራ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመገንባት ቃል ገብተው ህገ መንግሥቱን ዕውን ያደረጉት የአገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ስለሆኑ ነው። እናም የአገራችን ህዝቦች በራሳቸው ሙሉ ፈቃድ የመሠረቱትን ፌዴራላዊ ሥርዓት መልሰው የግጭት ምክንያት ሊያደርጉት ይችላሉ ብሎ ማሰብ ጤናማ አስተሳሰብ አይመስለኝም።

ያም ሆነ ይህ፤ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ህዝቦች ከግጭት የሚሰንቁት ምንም ዓይነት ተስፋ የለም። ተስፋቸው የተመሠረተው ከሠላም፣ ከልማትና ከዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ነው። ከግጭት የሚጠቀም ህዝብ ባለመኖሩም እነዚህን “የነገ ሰውነት” ተስፋዎች በማይነቃነቅ ፅኑ መሠረት ላይ ለማኖር አስተማማኝ ሠላም መፍጠር የግድ ነው። ለበርካታ ዓመታት በሠላም የኖሩት የኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ህዝቦችም እንደ ማንኛውም ህዝብ ጥቅማቸው ያለው ከሠላም እንጂ ከግጭት አለመሆኑን ይገነዘባሉ። እናም በሁለቱ ክልላዊ መንግሥታት ህዝቦችም መካከል ግጭት የሚፈጠርበት መሠረታዊ ሁኔታ ሊኖር አይችልም። በሁለቱም ወገኖች ውስጥ ጥቂት በአመራር ላይ ያሉ ግለሰቦች አሊያም ታጣቂዎች የራሳቸውን ፍላጎት ለማራመድ በድንበር አካባቢዎች ግጭት መፍጠራቸው ለዘመናት በፍቅር አብረው የኖሩትን የሁለቱን ተጎራባች ህዝቦች ፍላጎት የሚወክል አይደለም።

ይሁንና ምንም እንኳን በሁለቱ ህዝቦች መካከል ግጭት የሚፈጠርበት ነባራዊ አውድ (Context) ባይኖርም ቅሉ፤ “በጥባጭ ካለ ማን ጥሩ ይጠጣል” እንዲሉ አበው፣ እንደ አቶ ኢስማኤል ዓይነት ግለሰቦች ኃላፊነት በጎደለው ሁኔታ ህዝቦችን ለማጋጨት ሲራወጡ ማየት የተለመደ እየሆነ መጥቷል። ታዲያ እዚህ ላይ በይደር ያቆየሁትንና “ህዝብን ከህዝብ ጋር በማጋጨት ማን ይጠቀማል?” ለሚለው የርዕሴ ጥያቄ ምላሽ መስጠት ተገቢ ይመስለኛል። ለመልሱ ግን ሩቅ በመሄድ አንባቢዎቼን ላለፋ አልሻም። አዎ! በእኔ እምነት ካለፉት የአገራችን ልምዶችና ተሞክሮዎች በመነሳት ህዝብን ከህዝብ ጋር በማጋጨት የሚጠቀሙት ሁለት ኃይሎች ይመስሉኛል። እነርሱም አገራችን ሠላም ሆና ልማቷን እንዳታሳልጥ የሚፈልጉ አንዳንድ የውጭ ኃይሎችና ተላላኪዎቻቸው እንዲሁም ፅንፈኛ ኃይሎች ናቸው። እናም ኢ-ሚዛናዊውና በአገራዊ ኃላፊነት መንፈስ ያልተሰናዳው የአቶ ኢስማኤል ፅሑፍ የሁለቱን ተጎራባች ህዝቦች ሳይሆን፣ እነዚህን ኃይሎችና ተላላኪዎቻቸውን የሚጠቅም ነው። ከፌዴራላዊ ሥርዓቱ ነባራዊ እውነታ ውጭ አንዱን አግዝፎ ሌላውን የሚያቀጭጨው ፅሑፉ፤ ለእነዚህ ኃይሎች አጀንዳ በመስጠት በህዝቡና በመንግሥት እየተደረጉ ያሉትን ጥረቶች ሊገዳደር ይችላል።

ይህ ደግሞ በልማታዊውና ዴሞክራሲያዊው መንግሥት መሪነት በልማት ላይ ሌት ተቀን በመሳተፍ ህይወቱን ለመለወጥ የሚያስበውን የየክልሎቹን ህዝብ የሥራ ሞራል ይሰልባል። ኢንቨስትመንታቸው የውጭ ባለሃብቶችን እንዳይስብም ማነቆ ይሆናል። የአገራችንን ህዳሴ ለማረጋገጥ በሚደረገው ሂደት ውስጥ ክልሎቹ ሊወጡት የሚገባቸውን የተናጠልና የአብሮነት ሚናን ያቀጭጫል። በሁለንተናዊ አገራዊ ለውጥ ላይም እንቅፋት ይሆናል። እንዲህ ዓይነቶቹ ከድንበር መካለል ባሻገር የህዝብ ለህዝብ ዘላቂ ፅሑፎችን የሚያኮሰምኑ ፅሑፎች አገራዊ የሠላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ትልሞችን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ሊያበረታቱና ሊደግፉ በሚገባቸው እንደ አይጋ ፎረም ዓይነት ድረ ገፆች ላይ መስተናገዳቸው፤ የኢትዮጵያን ጠላቶችና ፅንፈኛ ኃይሎችን በተዘዋዋሪ መንገድ መጥቀም መሆኑን መገንዘብ ብልህነት ይመስለኛል።

 

Leave a Comment