ሁሉም በየፈርጁ ይዘከራል!

ሁሉም በየፈርጁ ይዘከራል!

ወንድይራድ ሀብተየስ

 

“…ዋንኛ  ጠላታችን ድህነት ነው፤ ድህነትን ማሸነፍ  ከቻልን ሁሉም ነገር  መፍትሄ ያገኛል”  ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ

ታላቁ መሪ በአንድ  መድረክ ላይ  የተናገሯት ድንቅ አባባል ናት።ኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ በአግባብ ያገናዘበ፣ ለችግሮቻችን  መፍትሄ ያመላከተ  ድንቅ  አባባል ናት። እውነት ነው ድህነታችን  የሁሉም ችግሮቻችን   መክንያትና መነሻ ነው። እንደእኔ እንደኔ ድህነታችን ለመልካም አስተዳደር እጦት፣ ለውስጥ ሽኩቻ፣ ግጭትና ቀውስ፣  ለዴሞክራሲ ስርዓታችን አለመጎልበት፣ ለውጭ ተጋላጭነት፣ እርስ በርስ የመጠራጠር፣ ለኪራይ ሰብሳቢነት፣ ለኋላቀርነት ወዘተ ምክንያት ሆኗል።  አሁን ላይ  ድህነትን መዋጋት ማለት ለአዲሱ ትውልድ የሞት የሽረት ጉዳይ መሆኑን  በኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ዘንድ ከስምምነት በመደረሱ ይህ ትውልድ ከድህነት ጋር ትንቅንቅ ላይ ይገኛል።

ይህ  ትውልድ ወገብ የሚያጎብጡ  እቅዶችን  በማቀድና በመተግበር  ለቀጣዩ ትውልድ መደላድል ለመፍጠር  ጎንበስ ቀና  በማለት ላይ  ነው።  አንዳንድ  አስተያየት  ሰጪዎች ይህን  ትውልድ “የመሰዋዓትነት ትውልድ” እንደሆነ  ይመሰክራሉ። እውነት ነው፤ እርሱ እየተቸገረ፣ እየተራበና እየተጠማ ዘመን ተሻጋሪ  ስራዎችን በቢሊዮን ዶላር ወጪ  እየገነባ ለቀጣዩ ትውልድ እርሾ በማስቀመጥ ላይ ነው። ለአብነት  በርካታ ትላልቅ  ባለብዙ ቢሊዮን ዶላር ወጪን  የሚጠይቁ  አውራ መንገዶች፣ አገር አቋራጭም ሆነ  የከተማ ባቡር ሃዲድ  ዝርጋታዎች፣ የሃይል ማመንጫጨዎች፣ የትምህርትና  የጤና ተቋማት፣ ኤርፖርቶች፣ የስኳር ፋብሪካዎች፣ ወዘተ፣ ተገንብተዋል፤ በመገንባት ላይ ናቸው።  

እነዚህ  የኢኮኖሚ አውታሮች  ለአገራችን ቀጣይ ትውልድ መሰረቶች ናቸው።  ይህ ትውልድ እነዚህን ሁሉ ተጨባጭ ለውጦች ማስመዝገብ የቻለው እዚህ ግባ የሚባል እርሾ  ሳይኖረው እንደሆነም ሊሰመርበት  የሚገባ  እውነታ ነው።   እውነት እንነጋገር ከተባለ  እንደኢትዮጵያ ያለ መንግስትና ህዝብ  መሰረተ ልማትን  ለማስፋፋት ከፍተኛ ወጪ  የሚያደርግ አንድም  የአፍሪካ  መንግስትም ሆነ ህዝብ  የለም። ይህን በተጨባጭ ማረጋገጥ ይቻላል። ኢትዮጵያ ቀደምት እርሾ የሌላት አገር ነበረች። ሁሉ ነገር ከዜሮ የጀመረባት አገር ናት ማለት ይቻላል።  

ይህ ትውልድ ከድህነት ጋር ከሚያደርገው ግብ ግብ ባሻገር  ዴሞክራሲያዊ ስርዓትንም እውን ለማድረግ ህይወቱንና አካሉን በመለገስ  ደርግን የመሰለ አምባገነን መንግስትን በትግል በመገርሰስ በህዝቦች ይሁንታ እውን የሆነ  ህገመንግስታዊ ስርዓት እውን አድርጓል፤ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር የሚችሉበት በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተች ጠንካራ ፌዴራላዊ አገር መስርቷል። ዛሬ ጅምር ቢሆንም ሊጎለብት የሚችል ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በአገራችን ተመስርቷል።   

ታላቁ መሪ  መለስ ዜናዊ  የህዳሴውን ግድብ የመሰረት ድንጋይ ባስቀመጡበት ወቅት  “ያቺ ድንጋይ ለእኔ፤ የውርደት ካባን ማራገፍ የጀምርንባት ድንጋይ ነች” ሲሉ ግድቡ ለኢትዮጵያ ህዳሴ ጉዞ  አንዱ  ማረጋገጫ  መሆኑን አብስረዋል።  አዎ ያቺ  ድንጋይ የአንድ የታሪክ ምዕራፍ  መዝጊያና  የአዲስ የመለወጥና የ”ይቻላል” መንፈስ በህዝቦች እንዲሰርጽ ያደረገች ታሪካዊ  ድንጋይ ነች፡፡  ከዚያች ድንጋይ በይፋ መቀመጥ በፊት እና በኋላ ነገሮች በእጅጉ ተቀያይረዋል፡፡  

ታላቁ የህዳሴ ግድብ  ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ብቻ ሳይሆን የስነ-ልቦናም ጥንካሬም  በህዝቦች መካከል ፈጥሯል። ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ  በህዝቦች ውስጥ  የ“እንችላለን”   ስሜት  እንዲፈጠር፣ ከተባበርን የማንችለው ነገር የለም  የሚል አስተሳሰብ እንዲፈጠር ያቺ ድንጋይ ምክንያት ሆናለች።  ያቺ ድንጋይ ዓለምም  ስለእኛ ያለው ግምት እንዲቀየር ምክንያት ሆናለች።  የዚህ ግድብ  ወጪ  በየትኛውም መስፈርት በታዳጊ አገር ሊሸፈን የማይቻል  ሆኖ ሳለ  የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች በራሳቸው ወጪ  ግንባታወን   በማካሄድ  ላይ ናቸው።  ይህ ታሪክ የሚከትበው  እውነታ  ነው።  አሁን ላይ ግንባታው  63 በመቶ ደርሷል። በቅርቡም በተወሰኑ ተርባይኖች  ሃይል ማመንጨት እንደሚጀምር  ባለሙያዎች  ይናገራሉ።  

ታላቁ የህዳሴ ኃይል ማመንጫ ግድብ እየተሰራ ያለው እኩልነትና ፍትህ ተነፍጎት በኖረና ነጻነቱን በሃይል ባስከበረው በዚህ በኛው ትውልድ መሆኑ ትልቅ ኩራት ሊሰማን ይገባል፡፡ ከላይ ለማንሳት እንደሞከርኩት ይህ ትውልድ የመሰዋዓትነት ትውልድ ነው።  ምክንያቱም ይህ ትውልድ  በአገራችን እነዚህን ሁሉ በርካታ ለውጦች በማስመዝገብ ላይ የሚገኘው  ተደላድሎ መኖር ሳያምረው ያገኘውን ነገር ሁሉ በመሰረተ ልማት ማስፋፋት ላይ  በማዋል ነው።

መንግስት  የተከተለው  ትክክለኛ ፖሊሲ ለስኬታችን  ትልቁ  መሰረት  ነው። ኢትዮጵያ በስፋት ያላት ሃብት በቀላሉ ሊሰለጥን የሚችል  የሰው ሃይል፣ መሬትና ውሃ  ነው፡፡ ይህ ትውልድ እነዚህን በማቀናጀት ነው ለውጥ እያመጣ ያለው።  በርካታ የዓለም ታዳጊ አገራት ፈጣን ዕድገት ማስመዝገብ የቻሉት በተፈጥሮ ሃብት በተለይ በነዳጅ ላይ በመመስረት ነው። የአገራችን ዕድገት ከዚህ ፈጽሞ የተለየ ነው። አገራችን ፈጣን እድገት ማስመዝገብ የቻለችው ኢህአዴግ በቀረጻቸው ውጤታማ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ነው። እውነታው ይህ ነው። ኢህአዴግ መመስገን ባለበት ነገር መመስገን  ይገባዋል። ኢህአዴግ ባላከናወናቸው ነገሮች  እንደወቀስነው ሁሉ ላበረከታቸውም ስኬቶች ሙገሳ ሊቸረው ይገባል። ይሁንና የዛሬ ርዕሰ ጉዳዬ ይህ ባለመሆኑ ይህን ጉዳይ  እዚህ ላይ ላቁመው።     

አባቶቻችን የጥቁር  ህዝቦች መመኪያ የሆነውን የአድዋ ድልን ትተውልን አልፈዋል።  እኛ ደግሞ  ለቀጣዩ ትውልድ  ቅሪት  ሊሆን የሚችል “ታላቁን የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ”  እናስረክባቸዋለን። ሁላችንም በየፈርጁ እንዘከራለን። በአድዋ ድል እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች አሻራ ያረፈበት  ታሪካዊ ክስተት ነበር።  በተመሳሳይ ታላቁን የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ  ፕሮጀክትም የእያንዳንዱ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች  አሻራ ያረፈበት ፕሮጀክት በመሆኑ ነው።  ይህ ትውልድ  ለዘመናት የቁልቁለት ጉዞ  ስትንደረደር የነበረችን አገር በሁለት እግሯ እንድትቆም ማድረግ የቻለ ትውልድ ነው፡፡ ይህ ትውልድ በአገራችን  የአይቻልም መንፈስን መስበር የቻለ ጀግና ትውልድ ነው፡፡

ይህ የእኛ ትውልድ ከቀዳሚው ትውልድ ድህነትና የቁልቁለት ጉዞን የተረከበ ቢሆንም  ለቀጠቀዩ ትውልድ የተሻለች ኢትዮጵያን ለማውረስ እየጣረ ያለ ጠንካራ ትውልድ ነው፡፡  እንደእኔ እንደኔ ይህን ትውልድ ስኬታማ እንዲሆን ያደረገው ለውድቀት የዳረጉ ምክንያቶችን ለይቶ ማወቁ ይመስለኛል። በአንድ ወቅት ታላቁ መሪ  ዋንኛ  ጠላታችን ድህነት ነው፤ ድህነትን ማሸነፍ ከቻልን ሁሉም ነገር ተወጣነው ማለት ነው ብለው ነበር።  ሌሎች ጠላቶቻችን ሁሉ በአንድ ላይ ቢደመሩ  በእርግጥ  ከድህነት የሚበልጡ አይደሉም። እኛ ኢትዮጵያዊያኖች ድህነትን ገጥመናል፤ በርካታም ተጨባጭ ለውጮችን በማስመዝገግብ ላይ ነን። አሁንም እኛ ስራ ላይ ነን። ማንም ከያዝነው ዓላማ አያዘናጋንም።

የጥንት አባቶቻችን በአድዋ ያስመዘገቡት ዘመን ተሻጋሪ ድል  አገራችን ለዓለም ጥቁር ህዝቦች  ኩራት ለመሆን አብቅቷታል። ለምዕራባዊያኖችም ጥሩ ትምህርት ሰጥታቸዋለች።  የእኛ ትውልድ ደግሞ  ለአፍሪካውያንና ለሌሎች መሰል አገራት  ኢትዮጵያችን በራሷ የልማት መንገድ ተጉዛ ያለምንም የውጭ እርዳታና ብድር ባለብዙ ቢሊዮን ዶላር ፕሮጀክቶችን  መስራት እንደሚቻል አሳይታለች። አባቶቻችን  ኢትዮጵያችንን ለዓለም ታዳጊ አገራት የነጻነት  ተምሳሌት  እንድትሆን እንዳደረጓት ሁሉ  የእኛ  ትውልድ ደግሞ  ኢትዮጵያችንን  ለዓለም  የልማት አብነት እንድትሆን  እናደርጋታለን።

 

Leave a Comment